1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብ

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 4 ከትዕይንት 1 እስከ 4)

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

ወንጀል ተፋላሚዎቹ! አዲስ ተከታታይ ድራማ ጽሑፍ በፌስ ቡክ። በፈጣን የሴራ ፍሰት፥ በአጫጭር ትእይንቶች የተገነባው ድራማ በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ይኽ የድራማ ጽሑፍ በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገፅ የሚቀርብ ሲኾን፤ ለሽልማት የሚያበቃ ነው። ስለ ተሳትፎ እና ውድድሩ ፌስቡክ ገጻችን ላይ በዝርዝር ይገኛል።

https://p.dw.com/p/2fTSc
09.2015 Crime Fighters MQ amharisch

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 4 ትዕይንት 1)

ሉሲ የወንጀል ምርመራ ክፍል ውስጥ ጠረጴዛው ፊት ለፊት አቀርቅራ ተቀምጣለች። መርመሪ ዓለሙ በቅርብ የሚያውቃት ልጅ እንዲህ አጣብቂኝ ውስጥ ኾና አይቷት አያውቅም።                                                

«ሚስተር ጂ ማን ነው?»

«ሚስተር ጂ? እኔ ምን አውቃለኹ! ደግሞስ ስለሱ ማን ያውቅና ነው?»

«አንድ ሰው ግን ያውቅ ነበር። ያ ሰው ደግሞ ጳውሎስ ነበር። ኮምፒውተሩ ውስጥ ለሚስተር ጂ የተጻፈ መልእክት አግኝተናል።»

«ምንድን ነው የምታወራው ዓለሙ?»

ሉሲ ሟች ባለቤቷ ሚስተር  ጂን እንደሚያውቀው  በአንድ ወቅት እንደነገራት ታስታውሳለች። ኾኖም አሁን መርማሪ ዓለሙ የሚያወራው ግራ አጋብቷታል።

«ጳውሎስ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንደነበረው ታውቂያለሽ። ለዚህም ነበር አይደል እንደምትገድዪው ስትዝቺበት የነበረው?»

«እኔ አልገደልኩትም ዓለሙ! አልገደልኩትም! ይገባኻል?» 

ዓለሙ ሉሲን ወደ እስር ክፍሏ እንዲመልሷት መመሪያ አስተላልፎ ይወጣል።

***  

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 4 ትዕይንት 2)

ይኽ በእንዲህ እንዳለ የዱር እንስሳት ፎቶግራፍ አንሺው ሙሳ እጅግ የሚፈልገው ዕቃ ጠፍቶበት ግራ ተጋብቷል። ፍቅረኛው ቤቲ ገላዋን እየታጠበች ነው።

«ቤቲ ቤቲ! ኮምፒውተሩ አጠገብ አስቀምጨው የነበረውን ሀርድ ድራይቭ አይተሽዋል?»

ቤቲ ድንገት ስለጠየቃት በጣም ደንግጣለች።

«ወይኔ ጉዴ! መልሼ ቦታው ሳላስቀምጠው… ምን አልከኝ? ኧረ እኔ አላየሁም።»

«ውስጡ ባለፈው ወደ ጫካ ሄጄ የቀረጽኳቸው እና ሌላ ሰው እጅ ውስጥ መግባት የሌለባቸው ቪዲዮዎች ነበሩበት።»

«እኔ እንጃ። ግን እዛ ውስጥ እንዳስቀመጥከው እርግጠኛ ነኽ?»

«በጣም እርግጠኛ ነኝ ቤቲ። እባክሽ እጅግ አደገኛ እና በሌላ ሰው እጅ ውስጥ መግባት የሌለባቸውን መረጃዎች የያዘ ነው። ወስደሽ ከሆነ መልሽልኝ»

«ኡፍ! አንተ ደግሞ። የአንተ ዝባዝንኬዎች ምን ያደርጉልኛልና ነው የማነሳው?»

ድንገት በሩ ከውጭ ተበርግዶ፦ መርማሪ ዓለሙ ከባልደረቦቹ ጋር ዘው ይላል።

***  

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 4 ትዕይንት 3)

መርማሪ ዓለሙ አኹን ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን አግኝቷል። ቤቲ እና ሙሳ። ሙሳ በጳውሎስ እና በፍቅረኛው ቤቲ መካከል የነበረውን ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ደርሶበት ተቀናቃኙን ገድሎት ቢሆንስ?

ዓለሙ፦«እሺ ቤቲ ጳዉሎስን እንዴት ተዋወቅሽው?»

«ጓደኛዬ ነበር።»

«ጓደኛ ብቻ? ሌላ ጉዳይ የለም በመካከላችሁ?የፍቅር ጓደኝነት?» (ቤቲ ትንሰቀሰቃለች።)

«እኔ እና ጳዉሎስ? አልነበረንም!»

« ቤቲ ለምንድነው እስካሁን የዋሸሽኝ? በጳዉሎስ ስልክ ውስጥ አንድ መልዕክት አግኝተናል፤ ምን ይላል መሰለሽ (ያነብላታል) «ቤቲ ከዛሬ በኋላ መገናኘት አንችልም፡፡ ሚስቴን እወዳታለሁ እናም ከእርሷ ጋር መሆን እፈልጋለሁ፤ አዝናለሁ፡፡ ጳዉሎስ።  ስለዚህስ ምን ትያለሽ?» (ቤቲ በድጋሚ  ትንሰቀሰቃለች።)

«ስለ ሚስተር ጂም ነግሮሽ ያውቃል አይደል?»

«ምን?!»

***  

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 4 ትዕይንት 4)

ቤቲ ለጊዜው ከእስር ቤት ተፈትታለች። ነገር ግን ነጻ የምትሆነው ለምን ያህል ጊዜ ይኾን? ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ሕገ-ወጥ አዳኞቹ በደኑ ውስጥ የተለመደው ተግባራቸውን እያከናወኑ ነው።

ሕገ-ወጥ አዳኝ ( በሹክሹክታ) «ሽሽሽ…!»

ጓደኛው (ዝቅ ባለ ድምፅ)  «ምንድነው?»

ዛፍ ላይ ግዙፍ ነብር ተጋድሟል። መሣሪያ በዝግታ ይቀባብላል። ከዚያም ይተኮሳል። ነብሩ ከዛፉ ላይ እንዘጭ ብሎ ይወድቃል።

«ገደልከው እኮ! አንተ ሰውዬ ምን ሆነሃል?»

 የእጅ ስልኩ ያቃጭላል።

«ሄሎ? አቤት ሚስተር ጂ... አዎ ዝሆኖቹን አግኝተናቸዉ ነበር፤ ግን አመለጡን፡፡ አዎ... ዱካቸውን እያነፈነፍን ነው፡፡ ምን? አላውቅም! አዎ... ሚስተር ጂ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ሚስተር ጂ ይቅርታ እሺ!»

ስልኩ ይቋረጣል።

«ብሽቅ!»

« ምንድነው? ምን  ተፈልጎ ነው?»

« ለሚስተር ጂ ሌላ የማስፈራሪያ ደብዳቤ ደርሷል፡፡ ምን እንደሆነ አልገባኝም! »

*** 

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር1 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ሁለተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 2 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ሦስተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 3 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን አምስተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 5 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 6 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 7 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 8 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

ጀምስ ሙሃንዶ

ማንተጋፍቶት ስለሺ