1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

መማር፣ ማስተማር በኦሮሚያ ክልል 

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ኅዳር 26 2010

በኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት በሚታይባቸዉ ቦታዎች የመማር ማስተማር ሒደት መስተጓጎሉ እየተሰማ ነዉ። ለምሳሌ በቀለም ዋላጋ ዞን በበዳምቢ ዶሎ ከተማ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማይታወቅ ጊዜ መዘጋቱ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ-ሶማሊ ድንበር ላይ የነበሩ ትምህርት ቤቶችም በስጋት ምክንያት መዘጋታቸዉን ለማወቅ ተችለዋል።

https://p.dw.com/p/2oo8K
Äthiopien Oromiya MBO Universität
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

አምቦ ዩኒቨርሲቲ

ትምህርት በተፈጥሮዉ ሰላማዊ የማስተማርና መመር ሁኔታ እንደሚፈልግ የሚናገሩት የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ኤፍሬም ተሰማ ላለፉት አምስት ወራት አካባቢ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር አከባቢ ያሉት ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ይናገራሉ።

ማህበረሰቡ የትምህርት አሰፈላጊነት ስለሚረዳዉ የሚያነሳቸዉ ጥያቄዎች ትምርትን በማቆም ሳይሆን በዉይይት እንዲፈታ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም   አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ።

በምስራቅ ሃራርጌ ዞን በሃሮማያ ከተማም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማርዎች ወላጆችም በልጆቻችን ላይ አደጋ ይደርሳል ብለዉ ስለሚሰጉ ልጆቻቸዉን  ወደ ትምህርት ቤት እንደማይልኩ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ።

የመማርና ማስተማር ሒደት በአለመረጋጋት መዋጡ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የተወሰነ ሳይሆን የዩኒቨርስትዎችንም ሥራ እና አሰራር እያወከ መሆኑን ተማርዎች ይናገራሉ። በሃሮማያ ዩኒቬርስቲ ተማሪ የሆነዉ ግን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ተማሪ፤ ተማሪዎች ለወራት ትምህርት ማቆማቸዉን ይናገራል። ዩኒቨርስቲዉ ተማርዎች እስከ ዛሬ ባለዉ ጊዜ ወደ ትምህርት ገበታቸዉ  እንዲመለሱ ማስታወቅያ ቢያወጣም እሱን ጨምሮ ሌሎች ተማርዎች ለመመለስ ስጋት እንዳላቸዉ ይናገራል፣ «እኔ የወሰንኩት ነገር የለም። ከሸዋ፣ ከዋላጋ፣ ከቦረና እንድሁም ከሩቅ ቦታዎች የመጡ ተማርዎች በየቤታቸዉ ነዉ ያሉት። ስለዝህ የመመለስና አለመመለስ ጉዳይ ላይ ሁሉም ተወያይቶ ካልተስማማ ለየብቻ የምደረግ ነገር የለም።»

ከትናንት ወድያ ጀምሮ በጅማ ዩኒቬርስቲ ያለዉ አለመረጋጋት በተመለከተም ጓደኞቹ እስካሁን ከዩኒቨርስቲዉ ግቢ ሸሽተዉ ዉጭ እንደምገኙ ማወቁን ተማሪዉ ይናገራል። 
በተመሳሳይም በዋላጋ፣ በአዳማና በአምቦ ዩኒቬርስትዎች ትምህርት መስተጓጎሉን ተማርዎች ይናገራሉ። በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነዉ ስሙም እንዳይጠቀስ የፈለገ ከባለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ትምህርት እንዳቆሙ ጠቅሰዋል።

የመማርና ማስተማር ጉዳይ አስመልክቶ በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ገፅ ላይ ለዉይይት አቅርበን ነበር። ሰምራ ማሃዲ የተባለችዉ «ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከ5ቀን በፊት ለቀው ወጥተዋል» ስትል፣ አስቻለ አረፋይኔ «ጅማ ዩኒቬርስቲ ትምህርት ካቆምን ሁለት ሳምንት ሆኖናል» ብሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከትምህርት ሚንስቴር  ማብራርያ ለማግኘት ያደርግነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሀመድ