1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጌላ ሜርክል የአሜካንን ጎበኙ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2009

የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዲሱ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር  ዋሽንግተን ውስጥ ፊት ለፊት ተገናኙ። ለመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይህ የዩኤስ አሜሪካ ጉብኝት ከምንጊዜዉም ሁሉ ከባዱ መሆኑ እየተዘገበ ነዉ። ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሃገራት ግንኙነትና በዓለም አቀፋዊ ቀዉሶች ላይ ተነጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/2ZRtr
USA Merkel und Trump - PK
ምስል Getty Images/AFP/S. Loeb

 

በጋዜጣዊ መግለጫዉ ላይ ሁለቱም ፖለቲከኞች የጋራ መግባብያ ነጥቦችን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።  ከዚህ በተጨማሪ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ዋነኛ የመነጋገርያ ርዕስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።  መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል  ዛሬ ዋሽንግተን የገቡት የ«ሲመንስ» የ«ቢ ኤም ደብሊዉ» እና  የ «ሼፍለር»  ኩባንያዎችን  ዋና ተጠሪዎች አስከትለዉ ነዉ። ሜርክል በዚህ ጉብኝታቸዉ የነፃ ንግድ ልዉዉጥ እና ክፍት ገበያዎችን እንደሚያስተዋዉቁ ከመንግሥት አካባቢ የወጣዉ መረጃ ያመለክታል።

USA Merkel und Trump
ምስል Reuters/J. Bourg

ይህ  ጉብኝት ከእስከ ከዛሬዉ የዩኤስ አሜሪካ ጉብኝታቸዉ ሁሉ ፈታኝ ሳይሆን እንደማይቀር እየተነገረ ነዉ። የፊታችን ሐምሌ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ የቡድን -20 ጉባዔን የሚያስተናfዱት ሜርክል ፤ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ከሚወያዩባቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የዩኤስ አሜሪካ እና የአዉሮጳ ግንኙነት እንዲሁም የሩስያ ጉዳይ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።  የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከአትላንቲክ ባሻገር ስላለው ግንኙነት እና ስለ አሜሪካን ፕሬዝዳንቶች  ብዙ አይተዋል ብዙም ያዉቃሉ ማለት ይቻላል። እጅግም የማይወደዱትን የቀድሞዉ የዩኤስ አሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽን በስልጣን ላይ ሳሉ ጀርመን  ባልቲክ ባህር አቅራብያ «ባርቢኪዉ»  ጋብዘዋቸዉ ነበር። በጣም ተወዳጅን ባራክ ኦባማንም  በባቫርያ አልፐን ተራራ ግርጌ የጀርመንን ባህላዊ ምግብ እና ቢራ  ጋብዘዋቸዋል።ሜርክል በነዚህ ሁለት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የስልጣን ዘመን ከአትላንቲክ ባሻገር ያለው ግንኙነት በኢራቁ  ጦርነት  እና በአሜሪካዉ ብሔራዊ የስለላ ተቋም የ« NSA» ስለላ ያሳደረው ቅሪታ  ከባድ ቀዉስ ቢያስከትልም ሜርክል ከዋሽንገተኑ መንግሥት ጋር በጣም የተቀራረበ ግንኙነት በማድረግ በቡሽም ጊዜ ሆነ በኦባማ ጊዜ በአዉሮጳ ጉዳይ የመጀመርያ የቅርብ አማካሪ ሆነዉ ቆይተዋል። ይሁን እና በበርሊን የዉጭ ግንኙነቶች ጉዳይ ላይ የአዉሮጳ ም/ቤት ቢሮ ሊቀመንበር ዮሴፍ ያኒንግ እንደሚሉት ሜርክል ከአሁኑ የዋሽንግተን መንግሥት ጋር ፈታኝ ሁኔታ ነዉ የሚገጥማቸዉ።

«የአሜሪካንን ፖለቲካ በተመለከተ እንደ አሁኑ ዉስብስብ ሆኖ አያውቅም።» በኢጣልያ ቦለኛው የጆን ሆፒኪንስ ዩንቨርስቲ የአሜሪካዊዉ የዉጭ ጉዳይ ተመራማሪ ዶን ሃርፐር እንደገለፁት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር አዲስ መንገድን መፈለግ ይኖርባቸዋል። ትራምፕ ከኦባማም ሆነ ከቡሽ ፈፅሞ የተለዩ ሰዉ ናቸዉ።  ትራምፕ  ከነዚህ ከሁለት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሆነ ከሜርክል የሚለዩት ምንም አይነት የፖለቲካ ልምድ ስለሌላቸዉ ፤ ከዚህ በተጨማሪ ትራምፕ ስለማንኛዉም ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ርዕሶች ላይ በቅጽበት ጠብ አጫሪ የሆኑ አስተያየቶችን በትዊተር መገናኛ መረብ በማሰራጨት ነዉ የሚታወቁት ። ሌላዉ ትራምፕ ከብዙኃን መገናኛዎች የግል ጸብ ላይ ናቸው። ትራምፕ ይህን ሁሉ ነገር ይዘዉ  ዋይት ሃዉስ መገኘታቸዉ ብቻ ሳይሆን ልዩ የሚያደርጋቸዉ ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፍፁም ተቃራኒ መሆናቸዉም ነዉ። ሜርክል ረጋ ያሉ እና  ቁጥብ በመሆናቸዉ ይታወቃሉ። የትራምፕ እና የሜርክል የሕይወት ታሪክና መንግስታዊ አመራር ስልት የተለያየ በመሆኑ በሁለቱ መካከል ሊኖር የሚችለዉን ግንኙነት አስቸጋሪ ያደርገዋል። መራሂተ መንግሥትዋ በዓለም ላይ የጋራና በርካታ ሃገራትን ያካተተ ፖለቲካን  ማራመድ ነዉ የሚፈልጉት። ትራምፕ በተቃራኒዉ ለአንድ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች  የአንድ ልዕለ ኃያል መንግሥት መፍትሄን ነው የሚደግፉት ። ብዙ ሃገራትን ያካተተ የአሰራር ዘይቤንም ይንቃሉ ። ትራምፕ እና ሜርልክ እንዲሁም ደጋፊዎቻቸዉ እስከዛሬ ያካሄዱት የቃላት ግጭት በአሁኑ ግንኙነታቸዉ ላይ ይህን ነዉ የሚባል ለዉጥን አያመጣም ሲሉ ያኒግም ሆነ ሃርፐር ይገምታሉ።

USA Angela Merkel und Ivanka Trump
ምስል Reuters/J. Ernst

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ