1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቅዲሹ፤ በሶማሊያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ አሸነፉ

ረቡዕ፣ የካቲት 1 2009

ሶማሊያ በዛሬዉ ዕለት በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ሥር ሆና አዲስ ፕሬዝደንቷን መረጠች። ለምርጫ ከቀረቡት 20 እጩ ተፎካካሪዎች 4ቱ ወደ ቀጣዩ ምርጫ ተሻግረዉ በተካሄደዉ ሁለተኛ ዙር ምርጫ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት የቀድሞዉ ጠቅላይ መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ምርጫዉን አሸንፈዋል።

https://p.dw.com/p/2XBv6
Somalia | Mohamed Abdullahi Farmajo
ምስል REUTERS/F. Omar

 ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ሁሴን ሼኽ መሐመድ የመጀመሪያዉን ዙር በ89 ድምጽ እየመሩ የነበረ ሲሆን፤ አብዱላሂ ፎርማጆ በ72 ድምጽ ሲከተሉ ቆይተዋል። ሁሴን ሼኽ መሐመድ ሽንፈታቸዉን መቀበላቸዉም ተገልጿል። የቀድሞዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሸሪፍ ሼኽ አኽመድ 49 ድምጽ ፤ የአሁኑ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊ ሻርማርኬ ደግሞ 37 ድምጽ አግኝተዋል።   ተንታኞች እንደገመቱት በመጀመሪያዉ ዙር ምርጫ የመራጩን ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማንም ባለማግኘቱ ነበር ሁለተኛ ዙር ምርጫዉ የቀጠለዉ። ዘገባዎች እንደሚያሳዩትም ሻርማርኬ «ወዴት እንደሚያመራ ያስታዉቃል» በማለት ከፉክክሩ ራሳቸዉን አግልለዋል። አዲስ የተመረጡት የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት በመቃዲሹ አዉሮፕላን ማረፊያ ነዉ ድምፃቸዉን ሲሰጡ የዋሉት። ምርጫዉ የሚካሄድበት ስፍራ ከሌሎች ይበልጥ ደህንነትና ፀጥታዉ አስተማማኝ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ። የዛሬዉ ምርጫ ባለፈዉ ነሐሴ ሊካሄድ የታቀደ ነበር። 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ