1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቅዲሹ፤ የተመድ ከፍተኛ ርዳታ ለሶማሊያ ጠየቀ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2009

የተመድ በሶማሊያ ላይ ያንዣበበዉን የረሃብ አደጋ ለመቀልበስ የሚረዳ ከፍተኛ ድጋፍ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠየቀ። በዛሬዉ ዕለት ለመጉብኝት ድንገት መቃዲሹ የገቡት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ በከፋ ድርቅ በተጠቃችዉ ሶማሊያ መጥፎ ነገር እንዳይከሰት ተማጽነዋል።

https://p.dw.com/p/2Yn6q
Somalia Mogadischu - U.N. Generalsekretär Antonio Guterres bei Pressekonferenz
ምስል Reuters/F. Omar

 የማዳኑ ዕድል መኖሩን በመጠቆምም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከሰባት ዓመት በፊት የተከሰተዉ እንዳይደገም ባፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፈዋል።  ሶማሊያ በ25 ዓመታት ጊዜ ዉስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በድርቅ የተመታች ሲሆን የዛሬ ሰባት ዓመት የተከሰተዉ ድርቅ 260 ሺህ ሰዎችን መፍጀቱን የፈረንሳይ የዜና ወኪል አመልክቷል። ጉተሬዥ በመቃዲሾ ቆይታቸዉም አዲስ ከተመረጡት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት መሐመድ አብደላ መሐመድ ጋር ተነጋግረዋል። ሶማሊያ የብዙዎች ድጋፍ እንዳላቸዉ የሚነገርላቸዉ ፕሬዝደንት መሐመድ ከተመረጡ ወዲህ ወደመረጋጋት እያመራች ነዉ ቢባልም ድርቁ የከፋ ርሃብ ያስከትላል የሚል ስጋት አለ። አንድ ሀገር ከጠቅላላ ህዝቧ 20 በመቶዉ ምግብ የማግኘት ዕድል ከሌለዉ በይፋ ለርሃብ መጋለጡ ይታወጃል። ሶማሊያ በአሁኑ ይዞታዋ 5,5 ሚሊየን የሚሆን ሕዝቧ በድርቁ ምክንያት በተከሰተዉ የዉኃ እጥረት ለዉኃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጧል። የተመድ ሶማሊያን ጨምሮ  በድርቅ ለተጎዱ አራት የአፍሪቃ ሃገራት 4,4 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገዉ አመልክቷል። ድርጅቱ እንደሚለዉ በእነዚህ ሃገራት በጠቅላላዉ ከ20 ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎች ለከፋ ርሃብ ተጋልጠዋል።