1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መነኮሳትን ጨምሮ ክሳቸው የተቋረጠ ተጠርጣሪዎች ተፈቱ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 5 2010

ኢትዮጵያ መነኮሳት እና የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ የቀረበባቸው ክስ የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎችን እየፈታች ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ክሳቸውን ካቋረጠላቸው 114 ተጠርጣሪዎች መካከል ወደ 89 ሰዎች እስካሁን ተፈተዋል። ከጃዋር መሐመድ ጋር ትገናኛለህ በሚል የታሰሩ የዩኒቨርሲቲ መምህር ይገኙበታል

https://p.dw.com/p/2w1c5
Symbolbild Handschellen
ምስል picture-alliance/chromorange/R. Tscherwitschke

የዋልድባ መነኮሳት ተፈተዋል

የቀድሞው የመዳወላቡ የዩኒቨርሲቲ የባዮ ኬሚስትሪ መምህር አቶ አባቴ አራርሶ ቱሳ ከነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ እስር ላይ ነበሩ። "የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለትምህርት እንደሚያመለክቱ ሁሉ እኔም ለፒ.ኤች.ዲ መርኃ-ግብር ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመልክቼ ነበር። የትምህርት ክፍሉ ተቀብሎኝ ከስፖንሰር ጋር ሊያገናኘኝ ከባሌ ጎባ ተነስቼ ወደ አዲስ አበባ እየሔድኩኝ ሳለ ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ሞጆ መነሐሪያ አካባቢ በደሕንነቶች በቁጥጥር ሥር ዋልኩ" ሲሉ አቶ አባቴ የታሰሩበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ስፖንሰር ፍለጋው ተቋረጠ። ያልተጀመረው ትምህርታቸውም ተስተጓጎለ። ሞጆ የታሰሩት መምህር ራሳቸውን በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ይጠራ ከነበረው የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ አገኙት።

ቢሮው መርማሪዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ስቅየት ይፈፅሙበታል እየተባለ የሚወቀስ በቅርቡም እንዲዘጋ የተወሰነበት የምርመራ ማዕከል ነው። አቶ አባቴ በማዕከሉ የገቡ ተጠርጣሪዎች "ጥፍር መንቀል፣መኮላሸት፣ መሰቀል፣ በረዶ ውስጥ ማደር" እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው መምህር "ድብደባ ደርሶብኛል። ለአራት ወር ከግማሽ በላይ የከረምኩት በጭለማ ቤት ውስጥ ነበር። በሽብር አዋጁ ለአራት ወር ነው ምርመራ ሊያካሒዱ የሚችሉት። ነገር ግን ምርመራውን ከጨረሱ በኋላ ፈቃደኛ አልነበሩም። ለቀጠሮ አራዳ ፍርድ ቤት በየ28 ቀኑ ያመላልሱን ነበር። ሳይቤሪያ ጭለማ ቤት ከሚባለው ወደ ሸራተን እንድወጣ የተደረገው አመልክቼ ነው" ሲሉ የገጠማቸውን ያስረዳሉ።

ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአቶ አባቴን ጨምሮ የ114 ተጠርጣሪዎች ክሶች እንዲቋረጡ ወስኗል። ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ከተፈቱት መካከል አባ ገብረ እየሱስ ኪዳነ ማርያም እና አባ ገብረ ስላሴ ወልደ ሃይማኖት የተባሉት የዋልድባ መነኮሳት ይገኙበታል። አቶ ሔኖክ አክሊሉ የተባሉ የህግ ባለሙያ ጥብቅና ከቆሙላቸው ተጠርጣሪዎች መካከል መርጌታ ዲበኩሉ ከእስር ተፈተዋል። ጠበቃ ሔኖክ "የእኔ ደንበኛ ከሆኑት ውጪ ታደሰ ወልደሐና ተፈቷል። እንደዚሁም ደግሞ አንድ ሌላ ተከሳሽ ተፈቷል። ከዛ በተረፈ ባሕታዊዎቹ ተፈተዋል። በአጠቃላይ የተፈቱት ትናንትና 57 ነበር። ዛሬ የተፈቱት 28 አካባቢ ናቸው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ የመሰረተባቸው ሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች በባሕር ዳር ከተማ መፈታታቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ጋዜጠኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተከሳሾች ጥብቅና የቆሙት አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው ዘጠኝ ደንበኞቻቸው መፈታታቸውን አረጋግጠዋል።

"በቁጥር ዘጠኝ ናቸው አሁን በትክክል ያወኳቸው። ነገር ግን የእኔ ደንበኞች ከ600 በላይ ስለሆኑ ካሁኑ ከ114 ቢያንስ ከ30-50 ይኖረኛል ብዬ ነው የማስበው። አሁንም አላወኩም እንጂ በርካታዎቹ ደንበኞቼ እንደተፈቱ ነው የምገምተው"

አቶ አባቴ የቀረበባቸው የሽብር ክስ ተቋርጦ ትናንት ከእስር ሲፈቱ ብቻቸውን አልነበሩም። ነፍጥ አንግቦ ኤርትራ በርሐ የመሸገው የግንቦት ሰባት ንቅናቄ አባል ናችሁ በሚል ተጠርጥረው ከአማራ ክልል የታሰሩ ሶስት ሰዎች አብረዋቸው ከቂሊንጦ እስር ቤት ከተፈቱ መካከል እንደሚገኙበት አስረድተዋል። ከወለጋ እና ከአምቦ አካባቢዎች ተይዘው የታሰሩ ሰዎችም አብረዋቸው ተፈተዋል። አብዛኞቹ በማዕከላዊ ታስረው የነበሩ እና የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ያቋረጠው እና በአቶ አባቴ ላይ ቀርቦ የነበረውም የሽብር ክስ ነበር።

"ሽብር ነው የሚሉት። በውጩ ሀገራት ካሉ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ሞክረሐል፤ በፌስቡክ መልዕክት ትለዋወጣለህ፤ በኢ-ሜይል ልትገናኛቸው ሙከራ እያደረክ ነው። እያደራጀህ ነው፤ ቅስቀሳ እያደረክ ነበር፤ ከጃዋር መሐመድ ጋር ግንኙነት ነበር የሚል ነው ያቀርቡ የነበረው"

አቶ አባቴ ሲታሰሩ የተቋረጠ የመምህርነት ሥራቸውን ለመቀጠል ያስባሉ። የዶክትሬት ትምህርታቸውንም የመቀጠል ፍላጎት አላቸው። ፍላጎታቸው የሚሰምረው ግን ከአንድ አመት ከስምንት ወር በላይ ታስረው የከረሙትን መምህር የቀድሞ ቀጣሪያቸው ከተቀበላቸው ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ