1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖችን ዕድሜ ሊገድብ ነው

ረቡዕ፣ ጥር 8 2011

ኢትዮጵያ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ገበያዋ እንዳይገቡ የሚገድብ ሕግ በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች። በአንድ አመት ውስጥ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ያግዳል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/3Bfko
Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

ጫን ያለ ታክስ እና ቅጣት በአማራጭነት ቀርቧል

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተመረቱ አምስት አመት ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገሪቱ ገበያ እንዳይገቡ ሊያግድ የሚችል ሕግ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሶስት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት በትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል ለኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር አቅርቧል። ኮሚቴው ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።

በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ የሚገጣጥሙ ተቋማትን መደገፍ፣ የትራፊክ አደጋን እና የከባቢ አየር ብክለትን መቀነስ እንዲሁም በታክስ አማካኝነት አገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ማሳደግ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው።

መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ዕድሜ ሊገድብ ዝግጅት ላይ ነው የሚለው መረጃ ይፋ ባይደረግም እንደ አቶ እዮብ ከበደ ካሉ ሰዎች ግን የተደበቀ አይደለም። በድለላ ሙያ የተሰማሩት እና ተሽከርካሪ የሚያገበያይ ድረ-ገጽ ባለቤቱ አቶ እዮብ መንግሥት "ከተሰሩ አምስት አመት ያለፋቸው ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ እንዳይገቡ ጥናቱ ቀርቦ ውይይት ላይ ነው ያለው። እየተነጋገሩበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

DW ለመረዳት እንደቻለው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ስለሚገቡበት አግባብ በመደንገግ ረገድ በመንግሥት ተቋማት መካከል ግልፅ የአቋም ልዩነት አለ።  “በአንድ ወገን ያሉት ረዥም ዓመት ያገለገሉ መኪናዎች ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ሊታገዱ ይገባል” የሚል አቋም አላቸው። ሌላኛው ወገን “መኪኖቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከፍ ያለ ታክስ እና ቅጣት መጣልን” በአማራጭነት አቅርበዋል። ጉዳዩ ገና በውይይት ላይ በመሆኑ መንግሥት የትኛውን መንገድ እንደሚከተል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

በተሽከርካሪ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ኑረዲን ሬድዋን የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ስላለው ዝግጅት በተባራሪም ቢሆን መረጃ ደርሷቸዋል። ከአውሮጳ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚስገቡት ነጋዴ "ቪትዝ አለ። ቪትዝ መኪኖች ከዱባይ የሚመጡ ናቸው። ያሪስ የሚባሉት ደግሞ ከአውሮጳ የሚመጡ ናቸው። ከዚያ ዶልፊን ተብለው የሚጠሩት ሚኒባሶች አሉ። ሌላኛው ደግሞ እንደ ቪትዝ ሁሉ ከዱባይ [ወደ ኢትዮጵያ] የሚመጡ 5L እና 3L መኪኖች አሉ። እና ኮሮላ ማለት ነው። ዕድሜያቸው ገፋ ያለ እና በብዛት እኛ አገር ያሉት እነዚህ ናቸው" ሲሉ መንግሥት የሚያደርገው ውይይት በቀጥታ የሚመለከታቸው ተሽከርካሪዎች የትኞቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የመጨረሻ አስተያየት እንዲሰጡበት የቀረበውን ጥናት በቅርበት የሚያውቁ ባለሙያ ከአምስት አመት በላይ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዳይገቡ የማገድ ሐሳብ መቅረቡን ለDW አረጋግጠዋል። በጉዳዩ ላይ ቃለ-መጠይቅ የመሥጠት ፈቃድ እንደሌላቸው የተናገሩት ባለሙያው ጉዳዩን በሕግ ለመገደብ ጥናት ከተሰራ ረዘም ያለ ጊዜ እንዳስቆጠረ እና ውይይት ሲደረግበት እንደቆየም አስረድተዋል።

ባለሙያው እና እርሳቸው የሚመሩት የሥራ ክፍል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የሚያግድ ጥብቅ ሕግ ሥራ ላይ እንዲውል ፍላጎት አላቸው። አሁን በሶስቱ ተቋማት አማካኝነት እየተደረገ ባለው ጥናት ይኸው እንደሚሆንም እርግጠኛ ናቸው። ጉዳዩ ከገቢ አኳያ የሚኖረውን አንድምታ የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲያጠና መታዘዙን DW አረጋግጧል። የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ በእርግጥም ውይይት እየተደረገ ስለመሆኑ ቢያረጋግጡም ተጨማሪ ማብራሪያ ለመሥጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። አቶ ሐጂ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል ያሉት የጉሙሩክ ኮሚሽንም ምላሽ ለመስጠት አፈግፍጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአምስት አመት በላይ ያገለገሉ መኪኖች እንዳይገቡ ማገዱን ችላ ብሎ ጫን ያለ ታክስ እና ቅጣት ወደመጣሉ ካዘነበለ የተሽከርካሪ ዋጋ በገበያው ጭማሪ ሊያሳይ ይችላል።

Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

አሁን በጥናት ደረጃ ውይይት የሚደረግበት ሐሳብ ሕግ ሆኖ ከጸደቀ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖች ዕድሜያቸው ከፍ ባለ ቁጥር የሚጣልባቸው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ጭማሪ ይደረግበታል።

በኢትዮጵያ የግብር ሥርዓት መሰረት "ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እንዲሁም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ እቃዎች እና የኅብረተሰቡን ጤና በሚጎዱና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ እቃዎች ላይ አጠቃቀሙን ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ታክስ አይነት ነው፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ አገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የተወሰኑ እቃዎች ላይ የሚጣል ሲሆን የክፍያ መጠኑም ከአስር እስከ መቶ ከመቶ" ይደርሳል። 

ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቧል በተባለው ጥናት መሠረት ከተመረቱ እስከ ሁለት አመት የሆናቸው ተሽከርካሪዎች 5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸዋል። ይኸው የታክስ አይነት ከተመረቱ ከሁለት እስከ ሶስት አመታት ላስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች አስር በመቶ፤ ከሶስት እስከ 5 አመት ለሚሆናቸው ደግሞ 20 በመቶ እንዲሆን ይደረጋል። የመኪኖቹ ዕድሜ ከፍ ባለ ቁጥር የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔውም ከፍተኛ ጭማሪ ያሳያል። ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ አስር አመታት የሆነ ተሽከርካሪዎች የሚጣልባቸው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን 100  ፐርሰንት ይሆናል።

አሁን ሥራ ላይ በሚገኘው ሥርዓት መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 100 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው የሞተር ጉልበታቸው ከ3000 ሲሲ በላይ የሆኑት ብቻ ናቸው። የሸቀጣ ሸቀጥ እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ግን ይኸ የኤክሳይዝ ታክስ አይመለከታቸውም።

ከዚህ ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ዕድሜያቸው በገፋ ቁጥር ቅጣት የማስከፈል ሐሳብ ጭምር መኖሩን ለመረዳት ችለናል። ይኸ እንዴት ሊሰላ እንደታቀደ ግን ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

በኢትዮጵያ ጎዳናዎች የሚሽከረከሩ መኪኖች ቁጥር ከዓመት አመት ጭማሪ ቢያሳይም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ ግን አሁንም ዝቅተኛ የሚባል ነው። መኪና ለኢትዮጵያውያን ከመሠረታዊ አገልግሎቱ ይልቅ እንደ እሴት እንደሚቆጠር ገበያውን በቅርብ የሚያውቁ ያስረዳሉ። አቶ እዮብ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን መኪና ሲገዙ የነዳጅ አጠቃቀምን፣ ተመልሶ የመሸጥ ዕድሉን እና ያለበትን ኹኔታ ይገመግማሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀደው የአሰራር ለውጥ ግን ከሸማቾች አቅም አኳያ በግብይቱ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አቶ እዮብ ሥጋት አላቸው። አቶ እዮብ "አንዳንድ ሰው በአቅሙ አነስ ያለ መኪና ገዝቶ መንዳት ይፈልጋል። የቅንጦት መኪና ገዝቶ መንዳት የሚፈልግም አለ። አነስ ያለ ገንዘብ ኖሮት ለቤት መጠቀሚያ ከ250 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ እና ከዚያም በታች በሆነ መጠን መኪና ገዝቶ ለመጠቀም ትንሽ ከባድ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ኑረዲን በበኩላቸው ለአዲስ ተሽከርካሪዎች የሚከፈለው የታክስ መጠን ሳይስተካከል የታቀደውን አሰራር ገቢራዊ ማድረግ ገበያውን ሊረብሽ እንደሚችል ያምናሉ። ሸማቹም ቢሆን አዲስ ተሽከርካሪ ይመርጣል የሚሉት ኑረዲን የታክሱ ነገር ግን ሊታሰብበት ይገባል ባይ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከባቢ አየር ጥበቃ መርኃ-ግብር ባለፈው መጋቢት ወር ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ መኪኖች 80 በመቶው ያገለገሉ ናቸው። አገሪቱ የምታስገባቸው ተሽከርካሪዎች ቁጥርም በየዓመቱ በ10 በመቶ ጭማሪ ያሳያል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ