1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

«መንግሥት የት ወደቃችሁ አላለንም» ለገጣፎ ቤት የፈረሰባቸው

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2011

በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ በ8 ቀናት 1800 ቤቶች እና 1700 ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ፈርሰዋል። ከፈረሱት መካከል ከ250 ሺሕ እስከ 900 ሺሕ ብር የሚገመት ወጪ የወጣባቸው ቤቶች ይገኙበታል። ቤታቸው ፈርሶ ቤተ-ክርስቲያን የተጠለሉ «መንግሥት የት ወደቃችሁ፤ ምን እየበላችሁ ነው? ምን ላይ ተኛችሁ?» አላለንም ይላሉ።

https://p.dw.com/p/3EDDK
Karte Sodo Ethiopia ENG

በለለገጣፎ 1800 የመኖሪያ ቤቶች ፈርሰዋል

የመኪና አሽከርካሪው አቶ ለገሰ ሙላት ከባለቤታቸው እና ሦስት ልጆቻቸው ጋር ለገጣፎ በሚገኘው የቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለዋል። የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከመቋቋሙ በፊት በ1997 ዓ.ም. ከገበሬ ላይ መሬት ገዝተው የገነቡት መኖሪያ ቤት ከፈረሰ በኋላ ኑሯቸው ተቃውሷል።  «አሁን ሠርተን የምናመጣው ነገር የለም። ቁጭ ብለን ነው ያለንው። የአካባቢው ሰው ራትም፣ ምሳም ቁርስም እያመጡ ያከፋፍሉናል፤ ያበሉናል፤ ያጠጡናል። የሕሊና መቁሰል እና የሞራል ውድቀት ካልሆነ በስተቀር አልራበንም። እንደ መንግሥት ግን የት ወደቃችሁ፤ ምን እየበላችሁ ነው? ምን ላይ ተኛችሁ ያለን አካል የለም» አቶ ለገሰ ሲሉ ያሉበትን ኹናቴ ይገልጻሉ። 

አቶ ለገሰም ሆኑ አብረዋቸው በቤተ-ክርቲያን የተጠለሉ የለገጣፎ ነዋሪዎች ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኞች አይደሉም። አብዛኞቹ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው የመኖሪያ ቤታቸውን የገነቡ ናቸው። በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በቤት ሠራተኝነት ያገለገሉ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ከአዲስ አበባ ከተማ ለመውጣት የተገደዱ በድንኳን ከተጠለሉ መካከል ይገኙበታል። ወደ ቤተክርስቲያኑ ብቅ ብለው የመኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ያሉበትን ኹናቴ የተመለከቱ የዐይን እማኝ «ቤት የፈረሰባቸው ሰዎች አሁን በድንኳን ነው ያሉት። ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ይባላል። እዚያው አካባቢ ያለ ቤተ-ክርስቲያን ነው። ተፈናቅሎ ያለው በጣም ብዙ ሰው ነው። በጣም ብዙ ብሶት የተሰማው ሰው አለ። ያለው ኹኔታ በጣም ይደብራል። ብዙ የመቀዛቀዝ ኹኔታ አለ» ሲሉ የታዘቡትን ለDW አስረድተዋል። 

ቅዳሜ ምን ተፈጠረ?

አቶ ለገሰ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤታቸው በከተማ አስተዳደሩ ሕገ-ወጥ ተብሎ እንዲፈርስ መታዘዙን የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሳቸው የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር። አቶ ለገሰም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በተሰጣቸው ቀናት አማራጭ ለማማተር የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። በዕለተ ቅዳሜ የካቲት 12 ቀን የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው አፍራሽ ግብረ-ኃይል ከፍተኛ ቁጥር ባለው ጸጥታ አስከባሪ ታጅቦ ከቦታው ደረሰ።  «የአካባቢው ሕዝብ እዬዬ ይል ነበር። ከቤት ሬሳ እንደሚያወጣ ያለውን የያቅሙን፤ ሶፋም፤ ወንበርም የቻሉትን ከግሬደር እና ከስካቫተር ጋር እየተጋፉ የተወሰኑ እቃዎች አወጡ። መመገቢያችንን ትሪ፣ የዕለት ግብዓት የሆኑ የቤት እቃዎችን አውጥተውልናል። ከዚያ ውጪ ቆርቆሮው፤ ቤቱ የተሠራበት እንጨት ሁለተኛ እንዳይሰራበት እየተመላለለሰ እንደ እህል ተፈጨ። የእልህ የእልህ ነበር የሚሠራ የነበረው» ሲሉ ኹኔታውን አቶ ለገሰ ያስታውሱታል። 
የመኖሪያ ቤታቸውን የሠሩበትን መሬት ሲገዙ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ገና አልተመሰረተችም ነበር። አቶ ለገሰ በ1996 ዓ.ም. በ15 ሺሕ ብር በገዙት ቦታ ላይ 80 ቆርቆሮ የፈጀ የመኖሪያ ቤት ገንብተዋል። እንዳልነበር ኾኖ የተደረመሰው ቤታቸው በአኹኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ሊያወጣ ይችል ነበር የሚል ግምት አላቸው። 

«100 ሺሕ ብር ያወጣ የመኖሪያ ቤት እዛው ቦታ ላይ ሠርቼበታለሁ። ባሁኑ ሰዓት የቀበሌ መታወቂያ አለኝ። ውኃ እና መብራት አስገብቼበታለሁ። የግብር ወረቀቶች አሉኝ። በቦታው ምክንያት ለአባይ ግድብ እየተባለ በየዓመቱ 1000 ሺሕ ብር ከግብር ጋር እያያዝን እንከፍል ነበር። ለሰፈሩ መንገድ እንዲወጣ፣ የውኃ መፍሰሻ እንዲሠራ፤ መንገዱ ላይ ጠጠር እንዲፈስ ለልማት የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ እያደረግን ነበር የኖርንው። በዛ ሰዓት ይኸ ቦታ ለሌላ ግልጋሎት ይፈለጋል ያሉን ነገር የለም። ቤቱ በአሁኑ ሰዓት 500 ካሬ ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን ያወጣል» የሚሉት አቶ ለገሰ ሐዘን ተጭኗቸዋል። 

የመኖሪያ ቤቶቻቸው የፈረሰባቸው ዜጎች እንደሚሉት በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ በኖሩባቸው ዓመታት መንግሥት የጠየቃቸውን የአፈር ግብር ሲከፍሉ ቆይተዋል። የከተማ አስተዳደሩም በየመኖሪያ ቤቶቻቸው የመብራት እና የውሐ አገልግሎት ሲያቀርብ ቆይቷል። 

በከተማዋ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚተዳደሩ አንድ ባለሙያ እንደሚሉት ከ250 ሺሕ እስከ 900 ሺሕ ብር ወጪ የተደረገባቸው ቤቶች በአስተዳደሩ ርምጃ ፈርሰዋል። በዚያው በለገጣፎ የሚኖሩት እና ስማቸው እንዳይገለጹ የሚሹት ባለሞያ አብዛኞቹ የቤት ባለቤቶች አነስተኛ ገቢ ያላቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። ለአንድ ወር የቤት ኪራይ መክፈል የሚሳናቸው፤ ለእቃዎቻቸው ማጓጓዣ በእጃቸው ገንዘብ ያልነበረ ነዋሪዎች ጭምር ቤቶቻቸውን አጥተዋል። የግንባታ ባለሞያው የከተማ አስተዳደሩ ለሚፈርሱ ቤቶች በቂ ጊዜ እንዳልሰጠም ይናገራሉ። የግንባታ ባለሙያው «በለገጣፎ የፈረሱት ብዙ ቤቶች ናቸው። ብዙ ብር ወጥቶባቸዋል። ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ቢያንስ እስከ 900 ሺሕ ብር የወጣበት የሚያምር ቤት ይገኝበታል። አሁን የፈረሰባቸው ሰዎች ቦታውን ከገበሬ ላይ ነው የገዙት። ዐሥርም ቆርቆሮ ይሁን፤ 20ም ቆርቆሮ ይሁን 30 ቆርቆሮ ሠርተው ይሸጡላቸዋል። በዛ መልክ ነው የተገኘው እንጂ ከመንግሥት የተገኘ አይደለም። ከአርሶ አደሮች ላይ ነው የተገዛው። የከተማ ማስተር ፕላኑ ሲመጣ ለአረንጓዴ ቦታ ተፈልጓል በሚል ነው እያፈረሱ ያሉት። በዚህ ጊዜ ተነሱ አልተባለም። ሰባት ቀን ጊዜ ተሰጣቸው። በሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ ካላነሳችሁ ርምጃ ይወሰዳል ተባለ። ይጨከንብናልም ብለው አላላሰቡም። ግን ያው ድንገት መጥተው ፈረሳ አከናውነዋል» ሲሉ አስረድተዋል። 

1998 ዓ.ም. የተመሰረተው የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ የተገደደው ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር ባለመጣጣማቸው እንደሆነ ይሞግታል። በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አድርገን ያላገኘናቸው የከተማዋ ከንቲባ ሐቢባ ሲራጅ የፈረሱ መኖሪያ ቤቶች ለመናፈሻ፣ ለትምህርት ቤት፣ ለጤና ጣቢያ እና ለስታዲየም በተዘጋጁ ቦታዎች ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው የሚል ማብራሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ሰጥተዋል። ከንቲባዋ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ሕገ-ወጥ የተባሉ ግንባታዎችን ስንመዘግብ ቆይተናል ብለዋል። 
የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ የኮምዩንኬሽን ቢሮ በዛሬው ዕለት በፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው መረጃ በስምንት ቀናት ውስጥ 1800 ቤቶች እና 1700 አጥሮች መፍረሳቸውን አስታውቋል። በዚሁ መረጃ መሰረት ከፈረሱት ቤቶች ውስጥ 800ዎቹ መኖሪያ ቤቶች ሰዎች ነበሩባቸው። «ሕገ-ወጥ» ተብለው የፈረሱት ቤቶች ለግንባታ በርካታ ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ናቸው።

የሠብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከስድስት ዓመታት በፊት ባወጣው መግለጫ በለገጣፎ ለገዳዲ ሕገ-ወጥ የመሬት ሽያጭ ተስፋፍቷል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። የሠብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ በለገጣፎ ለገዳዲ የተፈጠረው ቀውስ በሒደት እዚህ ደርሷል ሲሉ ይናገራሉ። በጉዳዩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት ሚና ሊጠና ይገባል የሚሉት አቶ ቢኒያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቶች መፍረሳቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ