1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መከከለኛው ምስራቅና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት

ሰኞ፣ ሐምሌ 23 1999

የጦር መሳሪያ ዕርዳታውና የሽያጩ ዓላማም ወደ ምዕራቡ የሚያዘነብል አስተሳሰብ የሚያራምዱትን አጋሮች ከኢራን ሊደርስ ከሚችል ጥቃት አንፃር ማስታጠቅ ነው ።

https://p.dw.com/p/E87r

ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያላት ተፅዕኖ በተጠናከረበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በአአካባቢው ለሚገኙ አጋሮችዋ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የጦር መሳሪያ ለማቅረብ አቅዳለች ። በዚሁ መሰረት እስራኤል ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው የጦር መሳሪያ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጣት ሲሆን ለሳውዲ አረቢያና ለሌሎች የባህረ ሰላጤው አገራት ደግሞ አማኤሪካን አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች ። የጦር መሳሪያ ዕርዳታውና የሽያጩ ዓላማም ወደ ምዕራቡ የሚያዘነብል አስተሳሰብ የሚያራምዱትን አጋሮች ከኢራን ሊደርስ ከሚችል ጥቃት አንፃር ማስታጠቅ ነው ። የአሁኑ ስልት ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ ጠላቶችዋ ላይ የወሰደችውን የከዚህ ቀደሙን ዕርምጃዋን ያስታውሳል ። የዋሽንግተን አስተዳደር በፀረ ኢራኑ ትግል የሳዳም ሁሴንን መንግስት እንዲሁም በፀረ ሞስኮው ትግል ታሊባኖችን አስታጥቋል ። ፔተር ፊሊፕ እንዳተተው ዩናይትድ ስቴትስ ኢራንን እንደገና ለመጫን የቀየሰችው የአሁኑ ስልቷ ግን የሚያዋጣ መንገድ የተከተለ አይመስልም ።
ከኢራቅ ጋር በሚካሄደው ጦርነትና በዓለም ዓቀፉ የፀረ ሽብር ዘመቻ ዋሽንግተን በሳውዲ አረቢያ ሚና ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደስተኛ አይደለችም ። ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ አሁን ለሪያድ መንግስት ዋጋው ወደ ሀያ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ትፈልጋለች ። ይህ ደግሞ ከጥቂት ወራት በፊት ለሳውዲ አረቢያ ለመሸጥ ከታሰበው የጦር መሳሪያ መጠን በዕጥፍ የላቀ ነው ። ሌሎች የባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራትም አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ይታጠቃሉ ። ግብፅም እንዲሁ ወደ አስራ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ይሰጣታል ። እስራኤል ደግሞ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የሰላሳ ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ታገኛለች ። “በጦር መሳሪያ ብዛት ሰላምን ማምጣት “ የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት አዲስ ስልት አይደለም ። ይፋ የተደረገው የጦር መሳሪያ ሽያጭ በአንድ በኩል የዋሽንግተን መንግስት ያጋጠመው የፖለቲካ ሀፍረት መሸፈኛ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኢራንን ይበልጥ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ነው ። ይህ ዕቅድም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ “እየጨመረ የመጣውን የኢራን አደገኝነት ለመከላከል የሚወሰድ ዕርምጃ ተብሎ ነው በይፋ የሚገለፀው ። በሌላ በኩል ለባህረ ሰላጤው አገራት የታቀደው የጦር መሳሪያ አቅርቦት ግን አትራፊ ንግድም ነው ለዩናይትድ ስቴትስ ። ከእስራኤልና ከግብፅ በስተቀር የተቀሩት ነዳጅ ዘይት አምራች አገራት የጦር ማሳሪያ ግዥ ነው የሚያከናውኑት ። እዚህ ላይ ምናልባት የሚያስገርመው ነገር የሳውዲ አረቢያውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እስራኤል ያለ አንዳች መጉረምረም መቀበሏ ነው ። ከአካባቢው አገራት የአሜሪካን የረዥም ጊዜ የጦር መሳሪያ ደንበኛ የሆነችው እስራኤል ምናልባትም የተጠበቀውን ወቀሳ ያላቀረበችው በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት ረክታ ይሆናል ። ወይም ደግሞ እንደ ሳውዲ አረቢያ ያሉት አገራት ለእስራኤል አስጊ አለመሆናቸውን በመገንዘቧ ብቻ ሳይሆን ሳውዲ አረቢያ እስካሁንም የገዛቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በአካባቢው ግጭቶች በደረሱበት ወቅት ስትጠቀም ባለመታየቷም ነው ። እንደ ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት እስራኤልም ራስዋን ለመከላከል የውጭ ኃይሎችን ማለትም የአሜሪካኖችን እገዛ ታገኛለች ። ለእስራኤል ብቸኛው አደጋ ሆኖ የሚታየው አንዳንድ የሳውዲ የጦር ኃይሎች ለምሳሌ አንድ ፓይለት በራሱ ተነሳሽነት ጥቃት ቢያደርስ ወይም ደግሞ የጦር መሳሪያዎቹ ሊደርሳቸው በማይገባ ሰዎች እጅ የሚወድቁ ከሆነ ነው ። ሁለቱ እንደምሳሌ ይቀርቡ እንጂ ሌሎች መላ ምቶችም ሊሰነዘሩ ይችላሉ ። ዩናይትድ ስቴትስ ለአረብ አገራት የጦር መሳሪያ መሸጧ እስራኤልን እንደማያሰጋት ሁሉ በኢራንም ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ። ሆኖም ግን አሜሪካ ለተግዋዳኞችዋ የጦር መሳሪያ እንደምታቀርብ ማስታወቋ በኢራን ላይ ተጨማሪ ትንኮሳ ማካሄድ መሆኑ ቴህራን ቢሰማት አግባብ ነው ።ይህ በመሆኑ ደግሞ ኢራን ህራን ተጨማሪ ዕክል ይገጥማታል ማለት አይደለም ። ለሳውዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ የታቀደበት ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ጠቀሜታ ያለው ነው ። በአንድ በኩል ኢራንን ማናደድ በሌላ በኩል ደግሞ የተግዋዳኞቹን የአረቦቹን ስሜት ለማርካት ነው ። አሜሪካን ለእስራኤል የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ በሀያ አምስት በመቶ በማሳደግ አሜሪካን ለእስራኤል እንደምታደላ ያስገነዝባል ። ይሁንና የአረብ ሀገራት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማድረግ አይችሉም ።