1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፍትሄ ያላገኘዉ የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ መጣያ 

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ መጋቢት 4 2009

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ በሚገኘውና በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከትናንት ወድያ የተከመረ ቆሻሻ በመደርመሱ እስካሁን 62 ሰዎች መሞታቸዉን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለዶቼ ቬሌ ተናግራዋል።

https://p.dw.com/p/2Z6uw
Äthiopien Erdrutsch in einer Mülldeponie in Addis Abeba
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Landslide at AA rubbish dump - MP3-Stereo

ከ50 ዓመት በላይ አግልግሎት ሲሰጥ በቆየዉ በዚህ የየደረቅ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ላይ ከከዚህ ቀደሙ የተለየ ክስተት እንዳልነበረ የገለጹት ሃላፊዋ አደጋው ያልተጠበቀ እንደነበር ተናግረዋል።

በሰሜን ምስራቅ አዲስ አበባ 27 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል በሰንዳፋ ጫቤ ዋራጋኑ ተብሎ የሚጠራ አከባቢ 1.5 ቢሊዮን ብር የወጣበት የደረቅ ቆሻሻ መጣያ መገንባቱ ሲዘገብ ቆይቷል። በጥር ወር 2008 ስራ የጀመረው ይህ አዲስ የቆሻሻ መጣያ ከአካባቢው ነዋሪዎች ተቃዉሞ ገጥሞት እንደነበር ከዚህ ቀደም ዘግበናል።

የማህበረሰቡን ተቃውሞ ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮምያ ክልል ውይይት ቢያካሂዱም፣ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው በመጨረሻም አዲስ አባባ ከተማ መስተዳድር ሌለ አማራጭ ቦታ ለመፈልግ መገደዱንም በዘገባችን ጠቅሰን ነበር።

በግል ተደራጅተው ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በደረቅ ቆሻሻ ማንሳት አገልግሎት ላይ የተሰማሩትን የ«ሰርካለም እና አስቻለዉ የደረቅ ቆሻሻ ማንሳት ማህበር» ስራ አስካያጅ አቶ አስቻለው ባዬ አየር ማረፍያ እንድገነባና የስራ እድል ይፈጥራል በምል ሰበብ መሬቱ መወሰዱ የአከባብ ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ጠቅሰዉ ነበር።

ለተቃዉሞዉ ሌላዉ መንስኤ ተብሎ የሚነገረዉ ተፈናቃዮች በቂ ካሳ አለማግኝታቸዉ እንዲሁም ቆሻሻዉ የጤና ችግር ያስከትላል ብለው መስጋታቸዉ ነዉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሬና የዳይናሚክ ሳንቴሪ አጋልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብቴ ወልደማርያም ከትናንት በስተያ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋ መንስኤ በሰንዳፋ የተገነበዉ የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ቦታ መዘጋቱና ቆሻሻዉን በቆሼ መድፋት መቀጠሉ ነዉ የሚባለዉ ትክክል አይደለም ከሚሉት አንዱ ናቸው።

በሰንዳፋ የተገነባዉ አድሱ የደረቅ ቆሻሻ መጣያን ዳግም ለመክፈት ጥናት እየተካሄደ ነዉ የሚሉት ወ/ሮ ዳግማዊት የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንደሌለ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

ኂሩት መለሰ