1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙርሲ የተወገዱበት 1ኛ ዓመት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2006

በግብፅ የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር የቀድሞው ፕሬዚደንት መሀመድ ሙርሲ ከሥልጣን የተወገዱበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ግዙፍ ተቃውሞ ተካሄደ። የሴቶች ዓለም አቀፍ የምክር ቤት መድረክ አባላት ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያጋጥማቸው የፀጥታ ችግር አንፃር ጠንካራ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አስተላለፈ።

https://p.dw.com/p/1CWMY
Pro-Mursi Proteste in Kairo 04.11.2013
ምስል Khaled Desouki/AFP/Getty Images

በዚሁ ጊዜ በሀገሪቱ የፀጥታውን ጥበቃ አጠናክሮ የነበረው የግብፅ ፖሊስ አደባባይ የወጡትን የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር ደጋፊዎች በሚያስለቅስ ጢስ በመበተን ብዙዎችንም በቁጥጥር አውሎዋል።የግብፅ ጦር ኃይል በሀገሪቱ ታሪከ ውስጥ የመጀመሪያውን የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር ፕሬዚደንት መሀመድ ሙርሲን ከሥልጣን ካወረደ ከሁለት ቀናት በፊት እአአ ሀምሌ 2014 ዓም ልክ አንድ ዓመት ሆነው።

Ägypten Präsident Abdel-Fattah al-Sisi Vereidigung 08.06.2014 QUALITÄT
ምስል Reuters

እአአ ሰኔ 2012 ዓም ፕሬዚደንት ሆነው የተመረጡት ሙርሲ በተከተሉት ፖለቲካ አንፃር በሰኔ 2013 ዓም ለብዙ ቀናት ግዙፍ ተቃውሞ ከተካሄደ በኋላ ያኔ የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ የነበሩት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ሀገሪቱ ስለገጠማት ውዝግብ ከፖለቲካ እና ከሲቭሉ ማህበረሰብ ጋ ሰፊ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ሙርሲ ከሥልጣን መወገዳቸውን አስታውቁ። ሙርሲ ከሥልጣን የተወገዱበትን አንድኛ ዓመት መንሥዔ በማድርግ አለ ሲሲ ባሱት ንግግር ያኔ ግብፃውያን ያደረጉትን ተቃውሞ አሞግሰዋል። «የሀገራችን ታሪክ እንዳሳየው ግብፅ ለመላው ዐረባውያት ሀገራት እና ለእሥልምና ከለላ ሆናለች። አክራሪ ሙሥሊሞች የወጠኑትን ከአሸባሪነት ጋ ተዛማጅ የሆነውን ዕቅዳቸውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ ግብፅ እንቅፋት ሆናባቸዋለች»

የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር ይህንን አነጋገር ውድቅ በማድረግ ሙርሲ ሕጋዊው ፕሬዚደንት መሆናቸውን በማሰታወቅ ሙርሲ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፡ የጦር ኃይሉ ባካሄደው መፈንቅለ መንግሥት አንፃር ተቃውሞአቸውን ቀጠሉ። በዚሁ ወቅት ከፀጥታ ኃይላት ጋ በተፈጠረ ግጭት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የሙርሲ ደጋፊዎች ተገድለዋል። ብዙዎችም ቆስለዋል። እአአ ታህሳስ 2013 ዓም የጦር ኃይሉ የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበርን የአሸባሪዎች ድርጅት ነው በሚል በሕግ አገደ። ፕሬዚደንት ሙርሲን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር ደጋፊዎቻችውን አሰረ።

Ägypten Proteste gegen Massenurteil 529 Muslimbrüder 27.03.2014
ምስል Mandel Ngan/AFP/Getty Images

የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው፡ የጦር ኃይሉ የሙርሲን ደጋፊዎች ዝም ለማሰኘት በጀመረው ዘመቻ ባለፈው ዓመት ቢያንስ አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ታስርዋል። ከነዚህም መካከል ስምንቱ በወህኒ ሞተዋል። ባጠቃላይ በግብፅ ሁኔታዎች እየተበላሹ መሄዳቸውን አምነስቲ አሰታውቆዋል።« የዘፈቀደ እስራት እና በፖሊስ ቁጥጥር በዋሉ ግለሰቦች ላይ የቁም ስቅል እየተፈፀመ መሆኑን ያመለከተው የአምንስቲ ዘገባ ፕሬዚደንት ሙርሲ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲሀ የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ እየተበላሸ መሄዱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነወ። »

እንደሚታወሰው፡ በግብፅ የሚንያ ከተማ እአአ በ 2013 ዓም የበጋ ወራት በተካሄደ እና አንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን በተገደለበት ተቃውሞ ተሳትፋችኋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው እና የጅምላ ችሎት ከተካሄደባቸው አንድ ሺህ ሁለት መቶ የሙርሲ ደጋፊዎች መካከል ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉት የሞት ቅጣት ተበይኖባቸዋል። ይህም ቢሆን ግን የሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበር እና ደጋፊዎቹ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ከሁለት ቀናት በፊት ባድረጉት ተቃውሞ ወቅት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የሴቶች ዓለም አቀፍ የምክር ቤት መድረክ ምክክር

የሴቶች ዓለም አቀፍ የምክር ቤት መድረክ አባላት ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚኢኣጋጥማቸው የፀጥታ ችግር አንፃር ጠንካራ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አስተላለፈ። ባለፈው ሀሙስ በርዋንዳ መዲና ኪጋሊ በተጠናቀቀው የሦስት ቀናት ስብሰባ ላይ ከሀምሳ ከሚበልጡ ሀገራት የተውጣጡ የምክር ቤት እንደራሴዎች ተሳታፊዎች ነበሩ።

ዓለም አቀፉ መድረክ ሴቶች ፀጥታ ለሚሰፍንበት እና የኤኮኖሚ ተሀድሶ ገሀድ ለሚሆንበት ተግባር ወሳኝ ሚና መጫወት እንዲችሉ ለማድረግ የተቋቋመ ነው። ከዓለም ሀገራት በጠቅላላ በምክር ቤትዋ ብዙ ሴቶች እንደራሴዎች በተወከሉባት ርዋንዳ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ የተሳተፉት እንደራሴዎች የሴቶች ማህበራዊ፡ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ በድጋሚ በአፅንዖት አሳስበዋል። እንደ የሴቶች ዓለም አቀፍ የምክር ቤት መድረክ መሥራች ወይዘሮ ዚልቫና ኮህ ሜሪን እምነት፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ሴቶች ዘንዳ በባህላዊ ልማዶች የተነሳ የታፈነ እጅግ ብዙ ያልተነካ ችሎታ አለ።

Silvana Koch-Mehrin FDP Archiv
የሴቶች ዓለም አቀፍ የምክር ቤት መድረክ መሥራች ወይዘሮ ዚልቫና ኮህ ሜሪንምስል dapd

ሴቶች ሰላም፡ ዕርቅ እና ፀጥታ በማውረዱ ተግባር ላይ ሊጫወቱት ስለሚገባው ሚና የመድረኩ አባል ሴቶች በሰፊው ከተወያዩ በኋላ የየሀገራቸው መንግሥታት በዚሁ የሰላም ማውረድ ሂደት ውስጥ ለሴቶች ማዕከላይ ቦታ እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፈዋል። ወሲባዊ ጥቃትን ለመከላከል የተቋቋመው የተመድ መስሪያ ቤት ልዩ ልዑክ ዘይናብ ባንጉራ ለእንደራሴዎቹ በቪድዮ ባስተላለፉት መልዕክት ባይጀሪያ ፅንፈኛው የሙሥሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም ከአስራ ሁለት ሳምንት በፊት ከሁለት መቶ የሚበልጡ ልጃገረዶች ያገተበት ድርጊት የሴቶች መብት አሁንም የሚጣስበትን ወንጀል ያሳየ ብለውታል። በተመድ የደህንነት እና የፀጥታ መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ ክሎቲልድ ምባራጋ ጋዛርቡዌም በሕግ ማውጣቱ ሂድት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ከፍ እንዲል ጠይቀዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ