1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ጥር 5 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ፀረ ሙስና ትግልን አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ መሰረትም በሙስና  የተጠረጠሩ በመቶዎች የምቆጠሩ የመንግስት አመራር አባላት ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለዋል።

https://p.dw.com/p/2VmWK
Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images

Corruption in Ethiopia - MP3-Stereo

ኢትዮጵያ ሙስናን ካሁን በተሻለ ዘዴ ለመታገል መነሳሳቷን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድጋሚ አስታውቀዋል። በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችንና ተቋማትን የሚመረምር አዲስ የሙስና ጉዳይ መርማሪ ኮሚሽን መከፈቱንም ገልፀዋል። በሙስና የተጠረጠሩ አንዳንድ የገቢዎችና ግምሩክ፣ እንዲሁም፣ የኢትዮ ቴሌኮም አመራር አባላት  በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ አመልክቶዋል። ይሁንና፣ በቁጥጥር የዋሉት ከፍተኛ የአመራር ባለስልጣናት አይደሉም በሚል ብዙዎች ቅሬታቸውን ከማሰማት አልተቆጠቡም።  ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫ ወቅት እንደገለጹት ፣ ከፍተኛ የአመራር አባላት በሙስና እስካሁን ተጠያቂ ያልሆኑበት ምክንያት  ይህን ማድረግ የሚያስችል የቀረበ «ማስረጃ ስለሌለ ነው»።  በመንግስት ኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚንስቴር ደኤታ ፣ አቶ ዛድግ አብርሃ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ አማራ ፣ትግራይ እንድሁም በሌሎች ክልሎች ማስረጃ በተገኘባቸዉ ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ይናገራሉ። 

መንግስት ጥልቅ ታሃድሶ አደረግሁ ማለቱን ተከትሎ ስልጣናቸዉን ያለአግባብ የተጠቀሙት ባለስልጣናት ላይ ርምጃ እንደምወስድ ማሳሰቡ ይታወሳል። በዚህም መሰረት፣ በመቶ የምቆጠሩ የመንግስት ባለስልጣናትን ማሰሩን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ይጦቁማሉ። አንዳንዶች ግን ይህ  ርምጃ  በሙስና ተዘፍቀዋል በሚሉዋቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት  ላይ ሳይሆን በዝቅተኛ የአመራር አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው ይላሉ። «ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ሙስና አፀያፊ ነገር ነዉ» የሚሉት አቶ ዛድግ፣ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ላይ ርምጃ እየወሰደ እንደምገኝም ተናግረዋል።

በአገሪቱ ተስፋፍቶዋል ለሚባለው ሙስና በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ያለዉ የስረዓት ፣ ማለትም የክትትልና ቁጥጥር ጉድለት ተጠያቂ መሆኑን በአድስ አበባ ዩንቨርስቲ በልማትና ፖሊስ ጥናት ተቋም መምህር ደክተር ተገኘ ገብረኢግዝሃቤር ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት የባለስልጣናቶች ግልፅነት ለማጠናከርና ሙሲናን ለመከላከል ሃብታቸዉን ወይም ንብረታቸዉን እንድያስመዘግቡ የምደነግግ ህግ በ2002 ዓ/ም አዉጥቶዋል። ይህን ህግ እንድያስፈፅም አላፍነት የተጠዉ የፌዴራል ስነመግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሺን ባጠቃላይ የ45,000 ግለሰቦች ሃብት ለመመዝገብ አቅዶ ፣ በዝህም መሰረት ከ20,000 በላይ የሚሆኑ ባለስልጣናት  ንብረታቸውን ቢያስመዘግቡም ፣ የምዝገባውን ዉጤት በተመለከተ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

በሙስና ላይ ጥናት የሚያካሂደው ትራንስፓሬንስ ኢንተርናሽናል የተባለው  ተቋም በ2007 ዓም ባደረገው ጥናቱ፣  ኢትዮጵያን ከ168 አገሮች 103ኛ ደረጃ ላይ ማስመጡ ይታወሳል። ጉቦን ጨምሮ ህገወጥ የገንዘብ ዝዉውርና የመንግሥት ግዥ ዋና የሙስና መንስዔ መሆኑንም የተቋሙ ዘገባ ጠቁሟል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ