1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙጋቤ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2011

ሥራ ወዳድ፣አንባቢ፣ምሑር፣መጠጥ እና ትንባሆን ተጠያፊ፣ አጥባቂ ካቶሊክ፤ሱፍ፣ኮት ከራባት አዘዉታሪ፣ ሽቅርቅር፣ ደግሞም ልጆች አፍቃሪ ናቸዉ።የመጀመሪያ ልጃቸዉ በ3 ዓመቱ ሲሞት እስር ቤት ነበሩ።በ1992 የመጀመሪያ ባለቤታቸዉ አረፉ።የካቲት፣ 2017፣ 93ኛ ዓመት ልደታቸዉን ሲያከብሩ «ብቻየን» ቀረሁ ብለዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/3PJLx
Robert Mugabe 1980
ምስል Getty Images/APF/Allen Pizzey

እንደሰዉ ብርቱ አንባቢ፤ ልጆች አፍቃሪ፣ እንደ ፖለቲከኛ ብልጥ፣ ጨካኝም ነበሩ

የደቡብ ሮዶሺያ ትባል የነበረችዉን ሐገር ከነጭ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ለማዉጣት ከታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመሪያዉ መስከረም ተመሰረተ።1957 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) መስከረም 1962 እሳቸዉና የቅርብ ጓዶቻቸዉ ታሰሩ።መስከረም 27, 1963 የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸዉ ተወለደ።መስከረም 6፣ 2019 አረፉ።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።ላፍታ እንዘክራቸዉ።
የሕይወት ታሪክ ፀሐፊዎቻቸዉ ዴቪድ ብሌየር እንደሚሉት እንደ ሰዉ ሥራ ወዳድ፣አንባቢ፣ምሑር፣መጠጥ እና ትንባሆን ተጠያፊ፣ አጥባቂ ካቶሊክ፤ሱፍ፣ኮት ከራባት አዘዉታሪ፣ ሽቅርቅር፣ ደግሞም ልጆች አፍቃሪ ናቸዉ።የመጀመሪያ ልጃቸዉ በ3 ዓመቱ ሲሞት እስር ቤት ነበሩ።በ1992 የመጀመሪያ ባለቤታቸዉ አረፉ።የካቲት፣ 2017፣ 93ኛ ዓመት ልደታቸዉን ሲያከብሩ «ብቻየን» ቀረሁ ብለዉ ነበር።
 «እንዲያዉ ያለፉኩትን ሳስበዉ፣ አሕ፣ ፈጣሪ ሆይ!! እኒያን ዉዶቼን ወስደሕብኝ እኔን ለዚሕን ያሕል ረጅም ጊዜ ብቻዬን እንድኖር ያደረክዉ ለምድነዉ እያልኩ እጠይቃለሁ።----መመለስ አልችልም።» 
እንደ ፖለቲከኛ ኩሩ፣ ደፋር፣ ቆራጥ፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱ፤ አፍሪቃዊነትን አቀንቃኝ፣ ለወዳጃቸዉ ሙት፣ ለጠላቶቻቸዉ ምሕረት የለሽ ናቸዉ።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።እንደ ሰዉ «ብቻዬን ቀረሁ» ያሉት አዛኙ ሙጋቤ፣ እንደ ፖለቲከኛ ግን ለምን ብለዉ ነበር።መጋቢት 2016።
«ለምንድ ነዉ? አለሁኝ።ለምድነዉ ተተኪ የምትፈልጉት? መኖሬን እንድታዉቁ በቡጤ እንዳገጫግጫችሁ ትፈልጋላችሁ?»
ኩሩ ናቸዉ።ደፋር።ቆራጥ፣ ጀግና አፍሪቃዊ።ይቅርባይም ናቸዉ። «መከረኛዋ ሐገር» የሚል ስም የሰጡት የመጀመሪያ ልጃቸዉ የሞተዉ ከናቱ ጋር እናቱ ሐገር ጋና በተሰደዱበት ነበር።1966።ሙጋቤ ለቅሶ ለመድረስ ላጭር ጊዜ ከእስር እንዲፈቱ ቢጠይቁ የእስር ቤቱ አዛዦች ሳቁባቸዉ።«ለነዚያን የእስር ቤት ኃላፊዎች ምንጊዜም ይቅርታ አላደርግም» ብለዉ ነበር።
በ1980፣ ኋላ ዜምባቡዌ ያሏት ሐገር ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ ግን የተሸነፈን እንበቀልም አሉ።ጀግና መሐሪ ነዉና። «ልጠላ አልችልም።ከልቤ የሁሉም ወዳጅ መሆን ነዉ የምፈልገዉ።የፈለገዉን ያሕል ቢበድለኝም ማንንም አልጠላም።ሁሉም አልፏል።የታገልንለትን አግኝተናል።ተሸናፊዎችን በምን ምክንያት ትጠላቸዋለሕ?»
የፖለቲካ ሁ-ሁን የቆጠሩት፣ የአፍሪቃ ብሔረተኝነትን ያደበሩት፣አብዮተኝነትን ያወቁት፣ ፋኖን የተገነዘቡትም እነ ኦሊቨር ታቦ፣ እነ ዎልተር ሲሲሉ፣ እነ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉንም እንደ አንድ ለማቀለጣጠፍ አንድ ሁለት በሚሉበት ሐገር እና ዘመን ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ።
1949።ምስራቃዊ ኬፕ ታዉን በሚገኘዉ ፎርት ሐሬ ዩኒቨርስቲ የመማር እድል አገኙና ሔዱ።በመደበኛዉ ትምሕርት ታሪክና ቋንቋ እያጠኑ፣ የአፍሪቃ ብሔረተኝነትን ትግል በቅርብ ያዩ፣የማርክስን ቲዎሪ ያነቡ፣ ቀድመዋቸዉ ካነበቡ ይማሩ ገቡ።
የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃዉያን ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) አባልም ሆኑ።«የሕይወቴ ጉዞ የተቀየረዉ እዚያና ያኔ ነዉ» ይሉ ነበር።ይሁንና ከማርክሲዚም ይልቅ ደቡብ አፍሪቃ የኖሩት የመሐተመ ጋንዲ አስተምሮ ይበልጥ ይማርካቸዉ እንደነበር አልሸሸጉም።
ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰዉ በሚያስተምሩበት ዘመን ሁለት ዲግሪዎችን ጨምረዋል።በ1958 በአስተማሪነት ተቀጥረዉ ጋና ሔዱ።የክዋሚ ንኩሩማ ዝና በናኘበት በዚያ ዘመን ከቅኝ አገዛዝ የተላቀቀች የመጀመሪያዋን አፍሪቃዊት ሐገር በቅርብ ማየታቸዉ ለወደፊት ትግላቸዉ መሰረት ሳይሆን አልቀረም።
ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸዉ በንኩሩማ አስተሳሰብ ሲሞረድ፣ ልባቸዉ በጋናዊቷ ወጣት ፍቅር ተማረከ።ሳራሕ ፍራንሲስካ ሳሊይ ሐይፍሮን።አገቧት።ሙጋቤና ባለቤታቸዉ በ1960 ወደ ደቡብ ሮዴሽያ ለእረፍት ሲሔዱ ጆሽዋ ንኮሞ የመሰረቱት የደቡባዊ ሮዴሽያ የአፍሪቃዉያን ብሔራዊ ኮንግረስ (SRANC በምሕፃሩ) ታግዶ፣ NDP የተባለ ሌላ ፓርቲ ተመስርቶ ጠበቃቸዉ።
እዉቁ የጥቁር መብት ታጋይና ጓዳቸዉ ሊዮፖልድ ታካዊራን ጨምሮ በርካታ የፓርቲዉ አባላት በመታሰራቸዉ ሙጋቤ ባለቤታቸዉን ወደ ጋና ልከዉ እሳቸዉ ፖለቲካዊ ትግሉን ለመቀጠል ደቡብ ሮዴሽያ ቀሩ።የፓርቲዉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነዉ ተመርጡም።ረጅሙን፣ አድካሚዉን፣ ከነፍጥ ዉጊያ እስከ ድርድር፣ ከእስር እስከሞት ከባድ መስዋዕትነት የሚያስከፍለዉን ትግል ከፊት ሆነዉ ያቀለጣጥፉት ያዙ።
እንደ ወታደር ሸማቂዎችን እያዘመቱ፣እንደ ፖለቲከኛ ሕዝብ አስተባብረዉ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ጋና፤ ከታንዛኒያ እስከ ሊቢያ፣ ከይጎዝላቪያ እስከ ቻይና የሚገኙ መንግስታትን ትብብር ጠይቀዉ፣ እንደ ዲፕሎማት ከብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች፣ ኋላ ደግሞ ኢያን ስሚዝ ከሚመሩት የነጮች መንግስት ጋር ተደራድረዉ ለዚምባቡዊያዊዉ ነፃነት አቀዳጁ።1980።
ከ1960ዎቹ እስከ 1980 የተደረገዉ ትግል የብዙ ሺዎችን ሕይወት አጥፍቷል።እነ ጆሽዋ ንኮሞን አሰድዷል።ሙጋቤን ራሳቸዉን ወሕኒ ቤት እንዲማቅቁ አድርጓል።የዚምባቡዌ ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በቀደም እንዳሉት የዚምባቡዌ የነፃነት ትግል ታሪክ የሙጋቤ ታሪክ ነዉ።
«ሐገራችን ዛሬ ነፃ ናት።ከ1960ዎቹ ጀምሮ መስዋዕትነት ለከፈሉት ለቁርጠኛ የነፃነት ታጋዮች ምስጋና ይግባቸዉና ሐገራችን ከ1980 ጀምሮ ነፃ ነች።ለዚሕ ካበቋት ብዙ ታጋዮች አንዱ ሟቹ ጓድ ሮበርት ሙጋቤ ናቸዉ።» 
በ1992 ማብቂያ  የያኔዉ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝደንት መለስ ዜናዊ ሐራሬን ሲጎበኙ ከሙጋቤ ጋር በር ዘግተዉ ለረጅም ጊዜ ተነጋግረዉ ነበር።ከነበሩበት ክፍል ሲወጡ አንድ አፍሪቃዊ ጋጠኛ «የቀድሞዉን የኢትዮጵያ መሪ አሳልፈዉ ይሰጣሉ?» የሚል  ይዘት ያለዉ ጥያቄ ጠየቃቸዉ።ሙጋቤ መለሱ ረጋ ብለዉ።«ኢትዮጵያ ለዚምባቡዌም፣ ለሌች የአፍሪቃ ሐገራት ነፃነትም ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገች ሐገር ናት።----ጓድ መንግስቱ (ኃይለማርያምን ወደ ሐገራቸዉ) በመመለስ ይሕቺ ሐገር ሰላም እንድታጣ ማድረግ አንፈልግም----የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪቃም-----» እያሉ። ቀጠሉም።
ኢትዮጵያ ለአፍሪቃዉያን ነፃነት በፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ መስክ ከሰጠችና ከምትሰጠዉ ድጋፍ በተጨማሪ እንደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የዚምባቡዌ ሽምቅ ተዋጊዎችን አዋሽ አርባ ላይ ታሰለጥን  ነበር።የዚምባቡዌ፣የናሚቢያ እና የደቡብ አፍሪቃ የነፃነት ታጋዮች ዓላማ ትግላቸዉን በኢትዮጵያ ራዲዮ (አለም አቀፍ አገልግሎት) ያሰራጩ ነበር።
በ1990ዎቹ ሙጋቤ የኢትዮጵያን ዉለታ ለጋዜጠኞች ሲነግሩ እንደ ሽግግር ፕሬዝደንት ያደምጡት መለስ ዜናዊ በ2000ዎቹ መጀመሪያ እንደ ጠቅላይ ሚንስትር አፍሪቃዉያን ፖለቲከኞች ፊት በግልፅ አረጋገጡት።
«ኢትዮጵያን የሚገዙት መንግስታት ምንም ሆኑ ምን፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪቃዉያን ነፃነት ምንግዚም የማይናወጥ አቋም ነዉ ያለት።ለመሆኑ ማንዴላን ያሰለጠነዉ ማነዉ?ነጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ ናቸዉ።አድሐሪዉ ኃይለስላሴ አብዮተኛዉን ማንዴላን አሰልጥነዋል።ማንዴላ ኢትዮጵያ ነበር የሰለጠኑት።ሙጋቤ ከሮዴዢያ ጋር ሲፋለሙ የረዳቸዉ ማነዉ? መንግስቱ።መንግስቱ ሐገር ዉስጥ አራጅ ነበሩ።በአፍሪቃ ጥያቄ ግን መንግሥቱ ልክ ኃይለስላሴ እንደነበሩት ሁሉ አቋማቸዉ ጠንካራ ነበር።»
ሮዴዢያ ነፃ ከወጣች በኋላ ሙጋቤ የደቡብ አፍሪቃዉያንን ጥቁሮች ዉለታ አልረሱም።ወይም አፍሪቃዊ ብሔረተኝነታቸዉ የነማንዴላን ትግል እንዲያግዙ ግድ ይላቸዉ ነበር።የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚንስትር ናሌንዲ ፓዶር በቀደም እንዳሉት ሙጋቤ ለደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ታጋዮች ባለዉለታ ናቸዉ።
«እንደሚታወቀዉ ሮበርት ሙጋቤ እና ዛኑ-ፒኤፍ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ተባባሪዎችና ወዳጆች ነበሩ።በፕሬዝደንት ሙጋቤ የምትመራዉ ነፃይቱ ዚምባቡዌ ለፖለቲከኞቻችንና ለካድሬዎቻችን በተለይም ኡምኮንቶ ዌ ሲዚዌ መሸሸጊያ ሐገርም ነበረች።»
የነ ሚንስትር ፓዶር ደቡብ አፍሪቃ ግን የኢትዮጵያ፣ የዚምባቡዌና የሌሎች አፍሪቃዉያን ሐገራት ደሐ ስደተኞች መዘረፊያ፣ መደብደቢያ፣ሲከፋ መደፈሪያ፣ መገደያ ሐገር የመሆንዋ ነዉ ሐቅ ነዉ-ቁጭቱ።
ሙጋቤ የደሐ ልጅ ናቸዉ።አባትዮዉ አናፂ፣ እናትዬዋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነበሩ።የዉልደት እድገታቸዉን ትክክለኛ ታሪክ በአፈ-ታሪክ ካልቀየሩ ጥቂት የአፍሪቃ መሪዎች አንዱ ናቸዉ።አባትዬዉ ወደ ሌላ አካባቢ በመሰደዳቸዉ እናት ሮበርትን ጨምሮ ስድስት ልጆቻቸዉን ብቻቸዉን ለማሳደግ ተገድዋል።
በልጅነቱ ከሰፈር ልጆች ጋር ከመጫወት፣ከመራወጥ ይልቅ እቤት ዉስጥ መቀመጥን፣ እናቱ ታሪክ ሲያወሩለት ማድመጥን፣ የሚነበብ ካገኘ ደግሞ ማንበብ ይመርጥ፣ ያዘወትርም ነበር።በዚሕም ምክንያት የዕድሜ አቻዎቹ «የናቱ ልጅ» እያሉ ያበሽቁት ነበር።የዚምባቡዌ አባት መሆናቸዉን ስንቶቹ አይተዉ ይሆን?
 ለጠላቶቻቸዉ ምሕረት የለሽ ጨካኝ ናቸዉ ይሏቸዋል።በተለይ ከ2010 በኋላ የወሰዷቸዉ እርምጃዎችና ባደባባይ የሚያስተላልፏቸዉ መልዕክቶች አምባገነን መሪ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ በማለት የሚወቅሷቸዉ ብዙ ናቸዉ።
ነጭ የሐገሪቱ ዜጎች የሚቆጣጠሩትን ሰፋፊ መሬት ለነፃነት ታጋዮች ማከፋፈላቸዉ የምዕራባዉያን መንግሥታትን በተለይም የብሪታንያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ጥርስ እንዳስነከሰባቸዉ ነበር።መሬቱን ለደሐ ገበሬዎች ያከፋፈሉት በ1980 በተደረገዉ የላንካስተር ሐዉስ ስምምነት መሰረት የብሪታንያ መንግስት መስጠት የሚገባዉን ድጎማ ባለመስጠቱ እንደሆነ ሙጋቤና ደጋፊዎቻቸዉ ደጋግመዉ መናገራቸዉ አልቀረም።
ሰሚ ግን አላገኙም።እንዲያዉም ዚምባቡዌ በብሪታንያ ግፊት ከጋራ ብልፅግና ሐገራት ማሕበር አባልነት ስትባበረር፣ በዩናይትድ ስቴትስ ትብብር ማዕቀብ ተጥሎባታልም።በ2008 በተደረገዉ ምርጫ MDC በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ያገኘዉ ዉጤት የዚምባቡዌ ሕዝብ ሙጋቤን በቁኝ የማለቱ ግልፅ ምልክት ነበር።ሽማግሌዉ አልበቃቸዉም።
በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወታ ካጠፋ ግጭት፤ዉዝግብ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ለተቃዋሚዉ መሪ ለሞርጋን ሽቫንግራይ ለመስጠት ተገደዋል።በ2017 ከራሳቸዉ ፓርቲ ከዛኑ-ፒኤፍ የተነሳባቸዉን ተቃዉሞ መቋቋም ግን አቅሙም፣እድሜዉም አልነበራቸዉም።ሕዳር 2017።«እኔ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ፣ በዚምባቡዌ ሕገ-መንግስት ምዕራፍ አንድ፣ አንቀፅ 96 መሰረት፣የዚምባቡዌ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንትነቴን ከዛሬ ጀምሮ መልቀቄን አስታዉቃለሁ።»
ከ1960 እስከ 1980 እንደ የነፃነት ታጋይ መሪ፣20 ዓመት፤ ከ1980 እስከ 2017 እንደ ጠቅላይ ሚንስትር፣ እንደ ፕሬዝደንትም 37 ዘመን ከቆዩበት ስልጣን ተሰናበቱ።አርብ ደግሞ የ95 ዓመት ረጅም የሕይወት ጉዟቸዉ አበቃ።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።

Mugabe feiert 92. Geburtstag
ምስል picture-alliance/AP Photo
Bildergalerie Robert Mugabe Simbabwe Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/R. Cooper
Robert Mugabe und Grace Mugabe
ምስል Getty Images/J.Njikizana
Bildergalerie Robert Mugabe Simbabwe Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/Keystone Pictures USA
Bildergalerie Robert Mugabe Simbabwe Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/U. Baumgarten

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ