1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚስጥር አጋላጮች

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2008

ሚስጥር አጋላጮች (Whistelblowers) የመንግሥት፤ የባለሥልጣናት፤ የድርጅት፤የኩባንያ እና የመሳሰሉትን ከሕዝብ የተደበቁ ሚስጥሮችን በማጋላጣቸዉ በየሐገሩ አንዳዴም በዓለም ሕዝብ ዘንድ ይወደዳሉ።የዚያኑ ያክል የሚያጋልጡት ሚስጥር በሥልጣናቸዉ ወይም በገንዘባቸዉ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ወገኖችን በመሆኑ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1Ih90
Symbolbild Pfeifen Whistleblower
ምስል LVDESIGN - Fotolia.com

በብዙዎቹ ሐገራት የሕግ ከለላና ጥበቃ አይደረግላቸዉምም።በዚሕም ምክንያት፤ የዶቸ ቬለዉ ማቲያስ ፎን ሐይን እንደዘገበዉ፤ ሚስጥር አጋላጮች በብዙ ሐገራት ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል ይገደዳሉ።

ብዙዎች ይወዷቸዋል። ሐይለኞች ይጠሏቸዋል።ፍትሕ ትፈልጋቸዋለች። ሕግ ግን ያሳስር፤ ያሳድናቸዋል።ዩናይትድ ስቴትስን የጦር ግፍ ያጋለጠዉ ወታደር ቼልሲ ማንኒንግ 35 ዓመት እስራት ተከናንቧል።ከማንኒግና ብጤዎቹ የሚያገኘዉን መረጃ ዊኪሊክስ በተሰኘ አምደ መረቡ ለሕዝብ የሚያቀርበዉ ጁሊያን አሳጅ በለንደኑ የኤኳዶር ኤምባሲ እንደተዘጋበት ነዉ።

Italien Bronzeskulptur in Perguia
ምስል DW/M. Bierbach


ዩናይትድ ስቴትስ በድፍን ዓለም የምትፈፅመዉን ሥለላ ያጋለጠዉ የቀድሞ የአሜሪካ ሠላይ ኤድዋርድ ስኖደን ሩሲያ ዉስጥ ስደተኛ ነዉ።የተገደለ፤ደብዛዉ የተጠፋ፤ ከሥራዉ የተባበረዉን ቤቱ ይቁጠረዉ።


ጀርመን ዉስጥ የማይበላ እንስሳ ሥጋን ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ኩባንያን አጋልጦ የነበር አንድ ሾፌር በ2007 እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ከያኔዉ የኢኮኖሚ ሚንስትር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሞ ነበር።ሾፌሩ ከሥራ ሲባረር ግን ዞር ብሎ ያየዉ የለም።ሒሳብ መርማሪ ኤርቪን ቢክሲለር የሠራተኛ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች የተዛቡ ስታቲስቲክስ ማወጣታቸዉን በማጋለጡ መስሪያ ቤቱ ሐላፊ ስልጣን ለመልቀቅ ተገድደዋል።ቢክሲለር ግን ባልደረቦቹ «አይንሕ ላፈር» ሥላሉት ታሞ ያለ ዕድሜዉ ጡረታ ወጣ።


ሔሰን ግዛት የግብር ሠብሳቢ መስሪያ ቤት ሙሰኛ ሐላፊዎችን ያጋለጠዉ ሩዶልፍ ሽሜንገር የተከፈተበትን የሥም ማጥፋት ዘመቻ ለማስቆም ክስ መስርቶ ከዓመታት ሙግት በኋላ ፍርድ ያገኘዉ ባለፈዉ ታሕሳስ ነበር።የ2009ኙን (እጎአ) የሚስጥር አጋላጮች ሽልማት ያገኘዉ ሽሜንገር እንደሚለዉ እዉነትን ለማጋለጥ የሚከፈለዉ ዋጋ ቀላል አይደለም።

«የተጭበረበሩ ሰነዶችን ወይም ሚስጥሮችን የሚያጋልጡ ዉስጥ አዋቂዎች እኛ ሐገር ከለላ እንደሌላቸዉ ማወቅ አለብን።አጋላጮቹ ሥማቸዉ ይጠፋል፤ ይገለላሉ፤ይኪያኪያሳሉ ከሥራ ይባረራሉም።ማሕበረሰቡ ምን እንደሚፈልግ መጠየቅ አለብን።»

Jahresrückblick September 2006 Deutschland Gammelfleisch
ምስል AP


የሚስጥር አጋላጭ-መረብ የተሰኘዉ ማሕበር ሊቀመንበር አነግሬት ፋልተር እንደሚሉት ደግሞ ሚስጥር አጋላጮች እነሱን የሚደግፍና ከለላ የሚሰጥ ሕግ በሌለበት ሐገር መጠንቀቅ አለባቸዉ።

«ለሚስጥር አጋላጮች በቂ የሕግ ከለላና ድጋፍ በሌለበት ሐገር ሚስጥርን ማጋለጥ የሚገጥመዉ አደጋ ከፍተኛ ነዉ።እንዲሕ ከማስጠንቀቅ ሌላ የምናደርገዉ የለም።በሌላ በኩል ግን ለማሕበረሰባችን በጣም ጠቃሚ የሆኑ (የተደበቁ) መረጃዎች አሉ።መረጃዎቹ እንዲጋለጡ ብዙ ሚስጥር አጋላጮች እንዲኖሩ መመኘታችን አይቀርም።ግን በቂ ድጋፍ የላቸዉም።»
የጀርመን ምክር ቤት የሚስጥር አጋላጮችን መብት የሚያስከብር ሕግ እንዲያወጣ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴዎች የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ለምክር ቤቱ ረቂቅ-ሕግ አቅርበዉ ነበር።የፓርቲዉ እንደራሴ ሐንስ-ክርሲቲያን ሽትሮቤለ እንደሚሉት ረቂቁ ሰወስት ክፍሎች ነበሩት።

Hans-Christian Ströbele Bundestag NSA Debatte 15.01.2014
እንደራሴ ሐንስ-ክርሲቲያን ሽትሮቤለምስል picture-alliance/dpa/Uli Deck

«የመጀመሪያዉ፤ሚስጥር አጋላጮች የምጣኔ ሐብት ችግር እንዳይገጥማቸዉ የሚጠይቅ ነዉ።ሁለተኛዉ፤-የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጣሪዎችን (ደሕንነት) ለማስጠበቅ ያለመ ነዉ።ሰወስተኛዉ እና በጣም አስፈላጊዉ ሚስጥር በማጋለጣቸዉ ቅጣት እንዳይጣልባቸዉ መከላከል ነዉ።ይሕ ክፍል የስለላ፤የመከላከያ፤የፀጥታ ሰራተኞችንም ይጨምራል።»
ረቂቁ እስካሁን አልፀደቀም።ለነገሩ ሕግ ባለባቸዉም ሐገራት ሚስጥር አጋላጮች ከፈተና አያመልጡም።ዩናይትድ ስቴትስ የሚስጥር አጋላጮችን መብት የሚያስከብር ሕግ አላት።የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ መስተዳድር ግን ሚስጥር አጋላጮችን እያደነ ነዉ።

ፎን ሐይን / ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ