1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ እና ያልተሻሻለው የፖለቲካ ሁኔታዋ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 15 2010

ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ማሊ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። አክራሪ ቡድኖችም በዚሁ ሁኔታ በመጠቀም ተፅዕኖአቸውን ለማስፋፋት እየሞከሩ ነው። የማሊ መንግሥት ሀገሩ አሁን የምትገኝበት ቀውስ በማብቃት እና መሻሻል በማስገኘት ውጤታማ እንዲሆን ግፊት አርፎበታል ።

https://p.dw.com/p/2usqF
Nigeria Ibrahim Boubacar Keita in Abuja
ምስል Reuters/A. Sotunde

የፊታችን ሀምሌ በሀገሪቱ በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታም ይህን እውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ፣ መንግሥት እና ተቀናቃኞቹ ወገኖች በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም በአልጀሪያ መዲና አልዥየ የተፈራረሙትን የሰላም ውል ተግባራዊ የማድረጉ ስራ አሁንም እክል እንደገጠመው ይገኛል።

የማሊ መንግሥት ከሀገሩ ሸሽተው ስደት የገቡ ዜጎቹ እንዲመለሱ ጥረቱን ቢያጠናክርም፣ በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ ዩኤንኤችሲአር ዘገባ መሰረት፣ የማሊ ስደተኞች  ቁጥር ከ134,000 በላይ ደርሷል፣ ይኸው ቁጥር የመቀነስ ሳይሆን የመጨመር አዝማሚያ ማሳየቱንም ነው የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት መስሪያ ቤት ያስታወቀው። የመንግሥት ተቃናቃኝ ቡድኖች አባላትን እና ተዋጊዎችን በህብረተሰቡ ውስጥ እንደገና ለማዋኃድ በወቅቱ ጥረቱ እንደቀጠለ ነው ትጥቅ የማስፈታት እና መልሶ የማዋኃድ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሳሃቢ ኡልድ ሲዲ መሀመድ የገለጹት። 

« የሰላም ስምምነቱን በተግባር የመተርጎሙ ነገር፣ ማለትም፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በህብረተሰቡ ውስጥ የማዋኃዱ ስራ እውን የሚሆንበት ጊዜ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር፣ ከዚሁ ሂደት ውጭ የሆኑ ቡድኖች፣ ይህ ስራ እንዳይሳካ የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህ ቡድኖች በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ምስቅልቅል ሁኔታ ተጠቃሚ ናቸው። » 
ያም ቢሆን በማሊ የቀጠለው ምስቅልቅል ሁኔታ በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል። ፍሪድሪኽ ኤበርት የተሰኘው የጀርመናውያን የፖለቲካ ጥናት ተቋም ከጥቂት ጊዜ በፊት በመላ ማሊ ያካሄደው የሕዝብ አስተያየት መዘርዝር ይህንን አረጋግጧል። ተቋሙ ባለፈው ህዳር ወር ካነጋገራቸው  ከ2,000 የሚበልጡ የማሊ ዜጎች መካከል ብዙዎቹ  የሰላሙ ውል በስራ ላይ የሚውልበትን ድርጊት ዋነኛው ቁልፍ አድርገው እንደሚመለከቱት የተቋም ጥናት መሪ ፊሊፕ ጎልድቤርግ አስታውቀዋል።

Friedrich Ebert Stiftung | GMF 2018 Sponsoren/Partner

«  ከተጠየቁት መካከል ብዙዎቹ በማሊ መረጋጋት፣ ሰላም እና ፀጥታ ለማስገኘት የሰላሙ ውል ተግባራዊነት ውሳኝ ነው ብለው ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪም የግል ደህንነታቸው ዋስትና በንዑሱ ብቻ የተረጋገጠ ወይም ከናካቴው አልተረጋገጠም ነው የሚሉት። »

ቀውሱ ውስብስብ እና ግራ አጋቢ እየሆነ መሄዱንም ነው ጎልድቤርግ ለዶይቸ ቬለ ያስረዱት። በ2012 ዓም የማሊ ጦር ኃይል ካካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሰሜናዊ ማሊ ላጭር ጊዜ በቱዋሬግ ዓማፅያን ቡድኖች እና በአንዳንድ አክራሪ ዎች ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። ይኸው ቁጥጥራቸው ከፈረንሳይ ጦር ኃይል አባላት ጣልቃ መግባት በኋላ ቢያበቃም፣ እንደ ጎልድቤርግ ትዝብት፣ ሰሜናዊው የሀገሪቱ ከፊል ዛሬም አስተማማኝ ያልሆነ ቦታ ነው። ማዕከላዩ የማሊ አካባቢም ቢሆንም እንዲሁ። ከዚሁ በተጨማሪ በሀገሪቱ  በቂ ሰብል ያልተሰበሰበበት ድርጊት ያስከተለው የመሰረታዊ ምግቦች ዋጋ ንረት በተለያዩ የሕዝቡ ክቡድኖች መካከል ውዝግቡ እንዲካረር ምክንያት ሆኗል ብለዋል ጎልድቤርግ። እንደ ጎልድቤርግ፣ የማሊ ዜጎች በሀገሪቱ በተሰማሩት ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ጓዶች ላይ ያላቸው እምነትም ከፍተኛ አይደለም። የጀርመን መከላከያ ሰራዊት ከ50 ሀገራት የተውጣጡ 11,000 ወታደሮች በተጠቃለሉበት በማሊ በተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህፃሩ በሚኑስማ ውስጥ ተሳታፊ ነው። የጀርመን መንግሥት በማሊ ያሉትን 1,000 የሀገሩን ወታደሮች ቁጥር ወደ 1,100 ከፍ ለማድረግ ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት ሰሞኑን በዚሁ ጉዳይ ላይ ምክክር አካሂዶበታል። ፈረንሳይ ከሚኑስማ  ጎን ሌላ የራሷ የሆነ የጦር ተልዕኮ አላት። ማሊን ለማረጋጋት የተሰማሩት የውጭ ኃይላት ግን ተልዕኳቸውን በሚገባ እየተወጡ አይደለም በሚል ከሕዝቡ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። 
« በማሊ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ ሚኑስማ ሕዝቡን ከኃይል ተግባር እና ከአሸባሪዎች አልተከላከለም፣  እንዲያውም፣  አልፎ አልፎ፣ ከጦር ኃይሉ ጋር በመተባበር በማሊ የኑሮ ዋጋ እንዲወደድ ድርሻ አበርክተዋል ሲሉ ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል ብዙዎቹ ወቅሰዋል። »

Mali Timbuktu - Tuareg
ምስል Getty Images/AFP/E. Feferberg

በኒዠር መዲና ኒያሜ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ኢሱፉ ያህያ እንደሚሉት፣ በማሊ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ተልዕኮ አንድ ዋነና የሚባል ችግር አለበት። የተመድ ሰላም አስከባሪ፣ ሚኑስማ እና የፈረንሳይ ጦር ተልዕኮዎች የየራሳቸውን የተለያዩ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚንቀሳቀሱት፣ በዚህም የማሊን መንግሥት ስልጣን እያዳከሙ በመሆኑ ፣ ይህን አሰራራቸውን ሊያበቁ ይገባል ፣ ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ያህያ።  

« ሁሉም የማሊን መንግሥት ስልጣን ለመቀበል እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቢስማሙ፣ ይህ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚያመራ አንድ ርምጃ ይሆናል። »
 ማሊ የጎረቤት ኒዠርን አርአያ በመከተል፣ በኃይል ተግባር ብቻ ሳይሆን በድርድርም አክራሪነትን መታገል እንደምትችል ኢሱፉ ያህያ ይናገራሉ።  
« እውነት ነው፣ አሸባሪዎችን መዋጋት አስፈላጊ ነው።  ይሁንና፣ የኃይል ርምጃ በመጠቀም ብቻ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ለማስገኘት አይቻልም። ውይይት በማካሄድ ሀገሪቱን ለማረጋጋት ተጨማሪ ሙከራ መደረግ አለበት። የማሊ መንግሥት ይህን የማድረግ አቅም ሊኖረው ይገባል። » 
ይህን አቅም በተመለከተ ኢሱፉ ያህያ በማሊ እና በሀገራቸው ኒዠር መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ያስረዳሉ። ከማሊ ጋር በ800 ኪሎ ሜትር ርዝመት የምትዋሰነዋ ኒዠር በማሊ ቀውሱ ጎልቶ በታየባቸው ዓመታት  ውስጥ እንኳን የግዛቷን ቁጥጥር አረጋግጣ ቆይታለች። የኒዠር ዜጎች በሀገራቸው የተከሰቱትን የተለያዩ ውዝግቦች ገንቢ በሆነ ድርድር አብቅተው፣ የተደረሱ የሰላም ውሎችንም እንዳከበሩ ያህያ በመግለጽ፣  ብዙዎቹ የማሊ ተቀናቃኝ ቡድኖች የአካባቢያቸውን መልሶ ግንባታ ለማራመድ በሰላሙ ውል የተስማሙ በመሆኑ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚያዋጣቸው ጠቁመዋል።

Infografik Kampf gegen Terror in der Sahel-Region Französisch

« ከነሱ መካከል ብዙዎቹ በትውልድ ግዛታቸው ባሉ ያካባቢ መስተዳድሮች ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ ይገኛሉ። የአካባቢው ሕዝብ ጥያቄ ሲኖረው በመጀመሪያ ደረጃ የሚያነጋግረውም እነሱን ነው።  ውጊያውን፣ የኃይሉን ተግባር እርግፍ አድርገው ትተው አሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ቦታቸውን መልሰው በማግኘት ሙሉ በሙሉ ተዋህደዋል። »

ይሁን እንጂ፣ በኒዠር አንፃር በማሊ የሰላሙ ውል የተደረሰው እና ምርጫ የተካሄደው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  ግፊት ነው። በ2015 ዓም የሰላም ውል መሰረት የሀገሪቱ መንግሥት ስልጣን  ያልተማከለ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል፣ ይሁንና፣ በፖለቲካ ጠበብት ግምት፣ ይህ እንደሚገባው እውን አልሆነም ወይም ፈፅሞም ተግባራዊ አልሆነም። የሀገሪቱ ወጣቶችም ወደ አክራሪነት የሚሳቡበት ሁኔታም አልቀነሰም። እንደ ኢሱፉ ያህያ አስተያየት፣ ማሊ የሰላሙን ውል በተግባር እንዲተረጎም እና የወጣቶች አክራሪነት እንዳይስፋፋ በማድረጉ ረገድ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ያካባቢ ባለስልጣናት የሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና ለውጤት ሊያበቃ ይችላል።  

አርያም ተክሌ/ፊሊፕ ዛንድነር

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ