1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ ያጣው የኤውሮ ቀውስ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 11 2004

የአውሮፓ ሕብረት የኤውሮ ዞንን የበጀት ቀውስ ለመግታት በሚያደርገው ጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም ችግሩ መፍትሄ ማግኘቱ አሁንም በግልጽ አይታይም።

https://p.dw.com/p/15ZF2
ምስል picture-alliance/dpa

የአውሮፓ ሕብረት የኤውሮ ዞንን የበጀት ቀውስ ለመግታት በሚያደርገው ጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም ችግሩ መፍትሄ ማግኘቱ አሁንም በግልጽ አይታይም። ቀውሱ ከአየርላንድና ከፖርቱጋል እስከ ግሪክ፤ እንዲሁም ከስፓን እስከ ኢጣሊያና ቆጵሮስ ዓባል ሃገራቱን ሲያዳርስ አሁን ደግሞ ከቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ አብራክ አወጣችው ስሎቬኒያም የድጎማ ጥገኛ እንዳትሆን በጣሙን እያሰጋ ነው።

ግሪክን የመሳሰሉት በቀውሱ የተወጠሩት ሃገራት በሕብረቱና በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ማረጋጊያ ድጎማ መልሶ ለማንሰራራት የቁጠባ ለውጦችን እያካሄዱ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች ደግሞ ባለፈው ሣምንት የስፓኝን ችግር ለማቃለል ትልቅ ዕርምጃ ወስደው ነበር። ሕብረቱ ዕዳ ለተጫናቸው የስፓን ባንኮች 100 ሚሊያርድ ኤውሮ ለማቅረብ ወስኗል።

ዕርምጃው አገሪቱ የበጀት ኪሣራዋን ቀደም ሲል እንደተወሰነው በመጪው 2013 ሣይሆን አንድ ዓመት ዘግየት ብሎ በ 2014 ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር ወደ ሶሥት ከመቶ ዝቅ እንድታደርግ ፋታ የሚሰጥም ነው። የስፓኙ የፊናንስ ሚኒስትር ሉዊስ-ዴ-ጉዊንዶስ ሕብረቱ ያላንዳች ተጨማሪ ግዴታ የበጀት ማረጋጋጊያ ዕርምጃውን ተፈጻሚነት በማሸጋሸጉ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የተናገሩት።

Madrid - Proteste in Spanien
ምስል dapd

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራሆይም የአገሪቱን ከባድ የበጀት ሁኔታ ለማለዘብ አጠቃላይ የቁጠባና የለውጥ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስታውቀዋል። ራሆይ በፓርላማ ያስተዋወቁት የግብር ጭማሪና የወጪ ቁጠባ በሚቀጥለው ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መንግሥትን 65 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያስገኝ ነው። የግብሩ ጭማሪ ዜጎችን ይብስ የሚያስቆጣ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቃዋሚ እንደራሴዎች ጩኸት በጋረደው ሁኔታ ባሰሙት ንግግር እንደጠቀሱት ዕርምጃው ችግሩን ለመቋቋም የግድ አስፈላጊ ነው።

«እነዚህ ዕርምጃዎች እርግጥ ደስ የሚሉ አይደሉም። ግን ደግሞ መቅረት የሌለባቸው ናቸው። በወቅቱ የምንገኘው በተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሲሆን ይህም የግድ መሻሻል ይኖርበታል»

በሌላ በኩል የስፓኝ መንግሥት ተጨማሪ ሚሊያርዶችን ለመቆጠብ የያዘው ውጥን ለተቃዋሚዎቹ ሶሻሊስቶች አልተዋጠላቸውም። ለምሳሌ የሶሻሊስቱ ፓርቲ ጠቅላይ ጸሐፊ አልፍሬዶ-ፔሬስ-ሩባልካባ ተጨማሪው ቁጠባ ችግሩን እንደሚያባብስ እርግጠኛ ናቸው።

«የአዲሱ የበጀት ዕቅድ ችግር ያለው በሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች ላይ ነው። እነዚሁም የባሰ የኤኮኖሚ ቀውስ፣ የሥራ ቦታዎች እጦትና ሕዝቡ በአገሩ ላይ ያለው ዓመኔታ ይበልጥ መመንመን ይሆናሉ»

የአውሮፓ ሕብረት የፊናንስ ሚኒስትሮች ለስፓን ባንኮች ዕርዳታ እንዲቀርብ የቀለጠፈ ዕርምጃ ነው የወሰዱት። ይሁንና ባንኮቹ ከመድህኑ ካዝና በቀጥታ ዕርዳታ እንዲያገኙ ባንኮችን የሚቆጣጠር የጋራ የአውሮፓ ታዛቢ አካል መኖሩ ግድ ነው። እርግጥ ይሄው አካል እንዲቋቋም የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሰኔ ወር ጉባዔያቸው መወሰናቸው ይታወሳል።

የሕብረቱ የምንዛሪ ኮሜሣር ኦሊ ሬህን ከዚህ ተሃድሶ ትልቅ ለውጥ ነው የሚጠብቁት። ባንኮች የመንግሥታት ቢሮክራሲዎችን ማለፍ ሳይኖርባቸው ከመድህኑ ካዝና ቀጥተኛ ዕርዳታ ማግኘታቸው በኤውሮ ዞን መንግሥታት ላይ የሰፈነውን ግፊት ለማለዘብ እንደሚረዳ ዕምነታቸው ነው። ሆኖም ችግሩ አውሮፓ ውስጥ ነገሮች ብዙ ጊዜ እንደሚታሰበው ፈጥነው አለመራመዳቸው ላይ ነው።

ለምሳሌ በሰኔው የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተላለፈው አንድ የባንክ ተቆጣጣሪ አካል የማቆም ውሣኔ ዕውን ሲሆን አይታይም። ጉዳዩን የሚያቀናብሩት የሕብረቱ የውስጥ ገበያ ኮሜሣር ሚሼል ባርኒዬር ገና ብዙ ጥያቄዎች እንዳልተፈቱ በማስገንዘብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ሲያሳስቡ የመጀመሪያውን ጽንሰ-ሃሣብ ምናልባትም በመስከረም ወር ሊያቀርቡ ቢችሉ ነው።

Brüssel - Treffen der Euro-Finanzminister
ምስል dapd

የሆነው ሆኖ የፊናንስ ሚኒስትሮቹ የስፓኝን ባንኮች በ 100 ሚሊያርድ ኤውሮ ለመደጎም በመሠረቱ ቢስማሙም የዕርዳታው ፓኬት መሰጠት ለዘለቄታው የሚጸድቀው በሣምንቱ ማብቂያ ላይ በሚካሄድ ልዩ ስብሰባ ነው። የመጀመሪያው 30 ሚሊያርድ ኤውሮ ግን የያዝነው ወር ከማብቃቱ በፊት ይተላለፋል።

ለማንኛውም የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች ስፓኝ ተገቢውን የቁጠባ ዕርምጃ በመውሰድ ችግሯን እንደምትቋቋም ተሥፋ ሲጥሉ በሌላ በኩል በወቅቱ ግሪክ ውስጥ ችግሩን ለመፍታት በተያዘው ጥረት ያን ያህል የረኩ አይደሉም። አዲሱ የግሪክ መንግሥት በፊናው በሁለተኛው የዕርዳታ ፓኬት ላይ ከተጣሉት ቅድመ-ግዴታዎች ለማምለጥ ባለው አቅም ሁሉ እየጣረ ነው።

ከብራስልስ የመነጩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግሪክ በወቅቱ የገባችውን የለውጥና የቁጠባ ጥረት ቃል ጊዜውን ተከትላ ስታራምድ አይታይም። ሂደቱ ተጎታች መሆኑ ነው የሚነገረው። ይሁን እንጂ ሕብረቱ በመሠረቱ ከዕርዳታ ዕቅዱ ገሸሽ የማለት ሃሣብ የለውም። የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ሣማራስም በፓርላማ የአመኔታ ድጋፍ ሲያገኙ መንግሥታቸው እርግጥ የሚፈልገው ከሕብረቱ ለሚጠበቅበት አስቸጋሪ ለውጥ የበለጠ ጊዜ እንዲሰጠው ነው።

« ነገሮች ሁሉ ከአሁን ወዲያ እንዲያውም እየከበዱ ነው የሚሄዱት። ስለዚህም አንድ ወጥ ዕርዳታ የግድ ያስፈልገናል። ይህም የተለየ አመለካከት ያላቸውን ጨምሮ ከሁሉም በኩል ማለት ነው»

የኤውሮው ምንዛሪ ክልል ቀውስ አያያዝ ፍቱንነት በብዙዎች ታዛቢዎች ዘንድ የስጋት መንስዔ እንደሆነ ቢቀጥልም የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ፕሬዚደንት ማሪዮ ድራጊ በአንጻሩ በተሥፋ የተሞሉ እንደሆኑ ነበር ባለፈው ሣምንት በአውሮፓ ፓርላማ የምንዛሪ ኮሚቴ ፊት የተናገሩት። ድራጊ «ኤውሮ በሕልውናው ይቀጥላል፤ ኤውሮ ዞንም ለዚህ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል» ነበር ያሉት።

Treffen EU Finanzminister Mario Draghi EZB-Präsident
ምስል AP

ይሁን እንጂ የማዕከላዊው ባንክ ፕሬዚደንት እንዳሉት ሁኔታው ከመንፈቅ በፊት ከነበረው ለዘብ ቢልም ችግሩ የሚመለከታቸው ሃገራት ከፍተኛ የሆነውን የብድር ወለድ ለመቀነስ ይበልጥ ለገበያ የፉክክር ብቃት፣ ለኤኮኖሚ መረጋጋትና ለበጀት ቁጥጥር መጣር ይኖርባቸዋል።

«ዕርምጃ መኖሩ ግልጽ ነገር ነው። ስለሆነም ሂደቱን እንግታ ወይም አንድ ዕርምጃ ወደ ኋላ ተመልሰን ሁሉንም ነገር እንደገና እናጢን ከማለት መቆጠቡን እመርጣለሁ። ምክንያቱም አሁን በብዙዎች አገሮች ከሁሉም በላይ ደግሞ በአየርላንድና በፖርቱጋል የወደፊት ዕርምጃ ምልክቶችን እያየን ነው»

ሆኖም ይህ አዝማሚያ መታየቱ ባይቀርም የኤውሮ ዞን የበጀት ቀውስ መስፋፋት ሊገታ መቻሉ ገና ብዙ አጠያያቂ ነው። በቀውሱ የተወጠሩት ሃገራት ችግር ሳያንስ በወቅቱ እንዲያውም ስሎቬኒያ ተጨማሪዋ ተደጓሚ እንዳትሆን ስጋት መፍጠሩ አልቀረም። ተማኝ ድርጅቶች በተለይም የአገሪቱን ባንኮች ስርዓት አሮጌነት እንደ ዋና ምክንያት በመጥቀስ የመበደር ብቃቷን በማሳነስ ላይ ናቸው።

ከቀድሞዎቹ የዩጎዝላቪያ ሬፑብሊኮች አንዷ ስሎቬኒያ ከስምንት ዓመታት በፊት በአውሮፓ ሕብረት ወደ ምሥራቅ የመስፋፋት ሂደት የስብስቡ ዓባል ስትሆን እንደ ጥሩ ተማሪ በጣም ነበር በአርአያነት የተወደሰችው። በጊዜው ፖላንድን፣ ቼክ ሬፑብሊክንና ሁንጋሪያን ጨምሮ አሥር ሃገራት ሕብረቱን ሲቀላቀሉ አዋቂዎች የተናገሩት የስሎቬኒያን ያህል ለትስስሩ በሚገባ የተዘጋጀ ሌላ አገር እንዳሌለ ነበር። ግን ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በሌሎች ሃገራት እንደታየው የስሎቬኒያን ሂደትም ለውጦታል።

Angela Merkel und Janez Jansa in Berlin
ምስል dapd

ዛሬ ጋዜጦችና ታዛቢዎች አገሪቱን የሚመለከቱት ለየት ባለ ዓይን ነው። እርግጥ አገሪቱ የሕብረቱ ድጎማ ጥገኛ እንዳትሆን ማስጋቱ እስካሁን ከመንግሥት በኩል በይፋ አይነገርም። ሆኖም ግን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያኔሽ ያንሣ በቅርቡ በአገሪቱ ፓርላማ ባሰሙት ንግግር ስሎቬኒያ የግሪክ ዕጣ እንዳይገጥማት ጠንካራ ቁጠባ አስፈላጊ መሆኑን ነበር ያስገነዘቡት። የአገሪቱ የፊናንስ ባለሥልጣናትም በወቅቱ ዕርዳታ አስፈላጊ እንዳልሆነ ከመግለጽ አልፈው የወደፊቱን ለመተንበይ አልደፈሩም።

ከስሎቬኒያ ችግሮች አንዱ የአገሪቱ ባንኮች በቂ የራስ ካፒታል የሌላቸው መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በመንግሥት ዕጅ ያለውን የአገሪቱን ታላቅ ባንክ ኖቫ ሉብሊያንካ ባንካን ይመለከታል። የቀድሞዎቹ የአገሪቱ መሪዎች በባንኩም ሆነ በኤኮኖሚው ዘርፍ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ በሰፊው እንዲፈስ ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይህ ደግሞ በተለይም ታላቁ የአገሪቱ ባንክ በየጊዜው ሥልጣን ለጨበጠው ወገን የፖለቲካ መሣሪያ ወይም መጠቀሚያ እንዲሆን ነው ያደረገው።

ይህ ሁሉ ታዲያ ዛሬ አገሪቱን ከባድ ከሆነ የፊናንስ ችግር ላይ መጣሉ አልቀረም። የሉብሊያናው መንግሥት የወቅቱን ሂደት ለመግታት አንድ የቁጠባ ዕቅድ ሲያወጣ ይህም በዋናነት የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደሞዝ በመቀነስ ላይ ያለመ ነው። በዚሁ ዘንድሮ 500 ሚሊዮንና በሚቀጥለው ዓመትም 750 ሚሊዮን ኤውሮ ለመቀጠብ ይታሰባል። ይሄው ከተሣካ የአገሪቱን የበጀት ኪሣራ በሚቀጥለው ዓመት ከአሁኑ 6 በመቶ ወደ 3 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል ነው።

ስሎቬኒያ በቁጠባ ዕቅዷ አማካይነት ድጎማ ከማመልከት ለማምለጥ ተሥፋ ጥላለች። ይሳካላት ይሆን? የሚሆነውን ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። በጥቅሉ የኤውሮ ዞን ችግር ግን በቀላሉ መፍትሄ የማያገኝ ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ