1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማንዴላ፤ በትግል ተወልደዉ በክብር ያረጁ

ሰኞ፣ ሐምሌ 11 1997

የስልጣን ፍቅርና በዘረኞች የተፈፀመባቸዉ ሁሉ በጭካኔ በቀል አሳዉሮ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ነጮችን ለመፍጀት አልገፋቸዉም። ይልቁንም በዳይና ተበዳይን በሮቢን ሁድ ደሴት ለ25 ዓመታት የግዞት ዘመን መስዋዕትነት አማካኝነት አቀራርበዉ በማስታረቅ በአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ ነጭንም ጥቁርንም የሚያሳትፍ የጋራ መንግስት ለመመስረት አበቃቸዉ።

https://p.dw.com/p/E0jl

ኔልሰን ማንዴላን ያስከበራቸዉ ዛሬም በቁማቸዉ እንደ ጀግና ባለታሪክ ለሁሉም በዓርዓያነት የሚያስጠቅሳቸዉ ከራሳቸዉ በፊት የታገሉለትን ህዝብ በማስቀደም በምጣኔ ሃብቱም ሆነ በጤናዉ ረገድ ለተጋረጠበት ችግር ሳይቦዝኑ መፍትሄ ለማፈላለግ መጣራቸዉ ነዉ።
ለደቡብ አፍሪካ ህዝብ የኤችአይቪ ኤድስን ሁኔታ ለማስተማር ሲወጡ የችግሩን ክፋት ከቤታቸዉ ነዉ የጀመሩት።
ከ5ሚሊዮን በላይ የሆነዉን የአገሪቱን ህዝብ እያሰቃየ የሚገኘዉ ይህ ቫይረስ የ54 ዓመት ትልቅ ልጃቸዉን ማክጋቶን እንደቀማቸዉ በይፋ ገለፁ።
በዚህና ከበፊት ጀምሮ ለህዝባቸዉ ባሳዩት ግልፅና ቀጥተኛ መቆርቆር ዛሬ ልደታቸዉን ለማክበር ህዝባቸዉ ቀስቃሽ የሚይፈልገዉ እንዳልሆነ ነዉ የሚነገርላቸዉ መወላዳቸዉ የአፓርታይድ የጭካኔ በትር ላንገፈገፋቸዉ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ትርጉም አለዉና።
የማንዴላ ፋዉንዴሽን ባለስልጣናት እንደሚሉት የዘንድሮዉን በዓል የኖብል ሎሬት የሽልማት ማዕረግ ያገኙት እኝህ የአፍሪካ ብርቅዬ ልጅ በፊልም ተዋናዮች፤ በባለስልጣናትና በሚወዷቸዉ ህፃናት ተከበዉ የሚታዩበት ብቻ አይሆንም።
ይልቁንም ይህ የ87ኛ ዓመት የልደት በዓላቸዉ የኔልሰን ማንዴላን የፓለቲካ ተሳትፎ በማጉላት ለሰብዓዊ መብት ያላቸዉን አክብሮት፤ ካለፉበት ህይወት በላቀ ለሰዉ ልጅ ያላቸዉን ክብር አጉልቶ በማዉጣት ሌሎችም ከእሳቸዉ እንዲማሩ ለማድረግ ታቅዷል።
በሮቢን ደሴት በግዞት በቆዩበት ወቅት አብረዋቸዉ ለ12 ዓመታት የታሰሩት የቀድሞዉ የመጓጓዣ ሚኒስትር ማክ ማሃራጅ እንደገለፁት ማንዴላ እንደማንኛዉም ሰዉ ደካማና ጠንካራ ጎን አላቸዉ።
እሳቸዉን ለየት የሚያደርጋቸዉና ሁሉም ሊረዳ የሚገባዉ እንዲደረግ የሚፈልጉት ተደርጎ ለማየትና በበኩላቸዉም ለማድረግ ዕልህ አስጨራሹን ጊዞ ስሜታቸዉን በመቆጣጠር ችሎታቸዉን ማሳየታቸዉን ነዉ ይላሉ።
በትግልና ከትግል በኋላም የቆሙለትን ዓላማ የግል ስሜታቸዉ ሳያሸንፈዉ 87ዓመታትን በክብር ተጉዘዉ በእርጅና ዘዉድ ሽበታቸዉ ያጌጡበት ማንዴላን ለማስደሰት ከህዝባቸዉ የቀረበላቸዉ የአዉደ ርዕይ ስጦታ ነዉ።
በስፍራዉም የኔልሰን ማንዴላን የህይወት ጉዞ ከሚተርከዉ ስብስብ በተጨማሪ ከዳሊ ላማ ወርቃማ ሃዉልት፤ በቅርብ በሞት የተለዩትን የፍልስጤም የትግል ዓርማ ያሲር ዓራፋትን የልጅነት ታሪክ፤ የታዋቂዉ የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ አባት የስዕል ዉጤቶች ይገኙበታል።
የማንዴላ ፋዉንዴሽን ይህን የልደት ስጦታ አዉደ ርዕይ የከፈተዉ ባለፈዉ ሐሙስ ሲሆን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኔልሰን ማንዴላን የእስር ቤት ህይወት ከሚተርከዉና በአስቂኝ መልክ ከተዘጋጀዉ መፅሃፍ ጋር አዟዙሮ የማሳየት ዕቅድ ይዟል።
ማንዴላም በተለያዩ ጊዜያት ያገኟቸዉ ሽልማቶች የተካተቱበትን ይህን አዉደ ርዕይ ከጎበኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር እነዚህ ሽልማቶች ስለእኔ ማንነት የሚተርኩ አይደሉም ይልቁንም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስጦታዉን ስለሰጡኝ ሰዎች ስሜትና አስተሳሰብ የሚተርኩ ናቸዉ ነዉ ያሉት።
ከስጦታዎቻቸዉ መካከልም በቤተልሄም ከተወለዱት አራፋት የተሰጣቸዉ በዲ ኔሮ አባት የተሳለዉ ስዕል ይገኝበታል።
ማንዴላም የሮበርት ዲ ኒሮ አድናቂና ፊልሙንም በድብቅ የሚያዩ መሆናቸዉን ቱጃሩ የንግድ ሰዉና የእሳቸዉ የቅርብ ጓደኛ ሲሪየል ራማፎሳ የአዛዉንቱን ጓደኛቸዉን ክንድ ደግፈዉ እያዟዟሩ ሲያስጎበኟቸዉ እንደቀልድ ገልፀዉታል።
ከ25ዓመታት ግዞት በኋላ ከ1986 እስከ 1991ዓ.ም. ድረስ በፕሬዝደንትነት ያገለገሉት ማንዴላ የ87ኛ ዓመት የልደት በዓላቸዉን የሚያከብሩት ከአሁኗ ባለቤታቸዉ ግራሳ ማሼል፤ ከሶስት ልጆቻቸዉ፤ ከልጅ ልጆቻቸዉና ከልጅ ልጅ ልጆቻቸዉ ጋር በመሆን በምስራቃዊ ኬፕታዉን ኩኑ መንደር በሚገኘዉ ቤታቸዉ ይሆናል።
ማንዴላ በአሁኑ ጊዜ ህዝብ ፊት ሲቀርቡ የሰዉ ክንድ ለድጋፍ እየያዙ ሲነዉ። አብዛኛዉን ጊዜም በቤታቸዉ ከቤተሰቦቻቸዉና ለእሳቸዉ ሶስተኛቸዉ ከሆኑት የቀድሞዉ የሞዛምቢክ ፕሬዝደንት ሳሞራ ማሼል ባለቤት ከግራሳ ማሼል ጋር በመሆን ያሳልፋሉ።
የማንዴላ ፋዉንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ጆን ሳሙኤል እንደሚሉት አሁን ማንዴላ ራሳቸዉን በማያስጨንቅና ዘና ባለ የህይወት መስመር ዉስጥ ገብተዋል።
አብዛኛዉን ጊዜም ከወይዘሮ ማሴል ጋር ከማሳለፍ በላይ ነገሮችን ቀለል አድርገዉ መመልከት ጀምረዋል።
ያም ሆኖ ግን ደቡብ አፍሪካን ከነጮች የበላይነት አላቀዉ የጋራ መንግስት ለመስረት ያበቁት የትግል ሰዉ አሁንም በሁሉም ዘንድ የጀግንነት ክብራቸዉ እንደተጠበቀ በመሆኑ የኤችአይቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማነቃነቅ የሚችል አቅም አላቸዉ ተብሎ ይታመናል።
የማንዴላ 87ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር በዚህ ብቻ አያበቃም የኬንያዋ ኖብል ተሸላሚ ዋንጋሪ ማታይ በነገዉ ዕለት የተፈጥሮ ጥበቃን አስመልክተዉ የሚያደርጉት ንግግርም የዚሁ አካል ነዉ።