1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክልና የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥረት

ዓርብ፣ መጋቢት 21 1999

የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል

https://p.dw.com/p/E881

የእስራኤል ፍልስጤምን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአዲስ መልክ በተንቀሳቀሰው የሰላም ጥረት ውስጥ የአውሮፓን ድጋፍ ለማሳየት የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ነገ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያመራሉ ። ሜርክል ሶስት ቀናት በሚዘልቀው የመካከለኛው ምስራቅ ቆይታቸው ዮርዳኖስ እስራኤልና ሊባኖስ እንዲሁም ፍልስጤም ራስ ገዝ ይሄዳሉ ። ነገ የሚጀመረው የሜርክል ጉብኝት ዓላማም እንደ ወቅቱ የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንትነታቸው ለአካባቢው ሰላም ሊያበረክቱ በሚችሉት አስተዋፅኦ ላይ ከአካባቢው አገራት መሪዎች ጋር መምከር ነው ።
በዚህ ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊዛ ራይስ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪሙን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥረት እንደገና በሚነቃቃበት መንገድ ላይ ከመካከለኛው ምስራቅ መሪዎች ጋር ሲመክሩ ነበር የከረሙት ። ሜርክልም እነርሱን ተከትለው ለአካባቢው ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ በሚችሉበት መንገድ ላይ ለመነጋገር ነው ወደዚያው የሚያቀኑት ። የጀርመን ባለስልጣናት እንዳሉት ሌላው የጉዞአቸው ዋነኛ ዓላማ የምዕራባውያን ድጋፍ ያለው ለዘብተኛው ፋታህና አክራሪው ሀማስ በዚህ ወር ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ከመሰረቱ ወዲህ ሰለ አካባቢው አጠቃላይ ሁኔታ በአካል ተገኝተው ግንዛቤ መውሰድ ነው ። በቆይታቸውም የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልሜርትና የፍልጤሙን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ያነጋግራሉ ። በዚሁ ወቅትም ሜርክል በአውሮፓውያን ስም ማካሻ የሌለውንና የማይለወጠውን መልዕክት ያስተላልፋሉ ። መልዕክታቸውም አዲሱ የፍልስጤም መንግስት የመካከለኛውን ምስራቅ የሰላም ሂደት በዕማኝነት የሚከታተሉት አራቱ ወገኖች ያስቀመጡዋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እስካላከበረ ድረስ ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ አብሮት አይሰራም የሚል ነው የሚሆነው ። አራቱ የሰላሙ ሂደት ዕማኞች የአውሮፓ ህብረት ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎችም አዲሱ መንግስት አመፅን እንዲያወግዝ ለእስራኤል ዕውቅና እንዲሰጥ እንዲሁም ለከዚህ ቀደሞቹ የሰላም ስምምነቶች እንዲገዛ የሚጠይቁ ናቸው ። ጀርመን በህብረቱ የፕሬዝዳንትነት መንበርዋ ወቅት ቅድሚያ ከሰጠቻቸው ጉዳዮች ውስጥ የአራትዮሹን ወገን የሰላም ጥረት እንደገና ማንቀሳቀስ ነበር ። በዚሁ መሰረትም በየካቲት ወር በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ስብሰባ ተደርጎ ነበር ። ጥቂት የሚባል ውጤት ብቻ ያስገኘው ይኽው ስብሰባ እንደገና ለመነጋገር ቃል ገብቶ ተለያይቷል ። አንዳንድ ምንጮች እንደጠቆሙት የአራትዮሹ ወገን በሚያዚያ ውስጥ ምናልባትም ግብፅ ሻርም ኤል ሼክ ሳይሰበሰብ አይቀርም ። የአራትዮሹ ወገን የሰላም ጥረት በዚህ ደረጃ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዋሽንግተን ደግሞ ስልትዋን ቀይራ እስራኤልና ፍልስጤማውያንን በተናጠል በማነጋገር አባስና ኦልሜርት በየአስራ አራት ቀኑ እንዲገናኙ አስማምታቸዋለች ። ይህን ስምምነት ጀርመን በአድናቆት ነው የተቀበለችው ። በዚሁ ሳምንት ሪያድ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ጉባኤ ያካሄዱት የአረብ ሊግ አባላት ደግሞ ከአምስት ዓመት በፊት ያቀረቡት የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ዕቅድ እንደገና እንዲንቀሳቀስ ተስማምተዋል ። ይኽው ዕቅድም የፍልስጤም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰዒድ አቡ እንደሚሉት የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ስቧል
ድምፅ..............................................................
ጀርመንም ከአረብ አገራት በኩል የቀረበው የአሁኑ የሰላም ዕቅድ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ሂደት እንዲቃና ይበልጥ የሚያነቃቃ ጥሩ አጋጣሚ ነው ባይ ናት ። ሊጉ የዛሬ አምስት ዓመት ያቀረበው ይህ ዕቅድ እስራኤል እአአ በሺህ ዘጠን መቶ ስልሳ ሰባቱ ጦርነት የያዘችውን መሬት ለቃ ከወጣች በእስራኤል ሰላም ይሰፍናል ከእስራኤል ጋርም ሰላማዊው ግንኙነቱ ይቀጥላል የሚል ነው ። በተጨማሪም የፍልስጤም መንግስት ምስረታንና የፍልስጤም ስደተኞችን መመለስም እንድትፈቅድም ይጠይቃል ። ስለ አረብ ሊጉ ጉባኤ ውጤትም ሜርክል ከዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላ ጋር አማን ውስጥ ነገ ይነጋገራሉ ። በአረብ ሊግ በኩል የቀረበውን ይህ ዕቅድ እስራኤል በአሁኑ መልኩ አልቀበለውም ነው ያለችው ። የእስራኤሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬስ በእስራኤል ራድዮ ባሰሙት ንግግር የምናቀርብላችሁን እንዳለ ተቀበሉ ማለት አይቻልም ። ልዩነቶቻችንን ማስወገድ የሚቻለው በድርድር ብቻ ነው ብለዋል ።