1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜቄዶንያ፤ ወደ ሰሜን አዉሮጳ የስደተኞች መንገድ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 14 2007

ከሶርያ ከአፍጋኒስታን እንዲሁም ከፓኪስታን የፈለሱ በርካታ ስደተኞች የባልካን ሃገራትን አቋርጠዉ ወደ ሰሜናዊ አዉሮጳ ሀገራት ለመግባት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የርስ በርስ ጦርነትና የሰብዓዊ ቀዉስ ካስከተለዉ ድህነት ለማምለጥ በመሰደድ ላይ ያሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመከላከል ሃንጋሪ ድንበርዋን በአጥር ለመከለል አቅዳለች ።

https://p.dw.com/p/1GJ4p
Mazedonien Flüchtlingsansturm in Gevgelija
ምስል DW/N. Rujevic

[No title]

ይህ ከተሰማ በኋላ አጥሩ ከመገንባቱ በፊት ስደተኞች ወደ ሰሜናዊ አዉሮጳ ለመግባት እድላቸዉን በመሞከር ላይ ይገኛሉ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሜቄዶንያ ጂቬጂሊያ ከተማ የሚገኘዉ የባቡር ጣብያ በማጨናነቅ ላይ ይገኛሉ። በከተማዋ የሚገኙት ባለሥልጣናት በበኩላቸዉ ሥደተኞቹን በዝምታና በፍጥነት ወደ ሰርብያ ማሻገሩን ተያይዘዉታል።
አንድ የሜቂዶንያ ፖሊስ በባቡር ፉርጎኖች ስርቻ የተደበቀ ሰዉ እንዳለ በስድብ«እነዚህ አሸባሪዎች ሁሉ » እያለ የእጅ ባትሪዉን ብልጭ ድርግም እያደረገ ጎንበስ ቀና እያለ ስደተኞች መኖር አለመኖራቸዉን ይፈልጋል። በሜቄዶንያ ጂቬጂሊያ ከተማ የሚገኙት ስደተኞች የየቀን ትግል የሚጀምረዉ ከግሪክዋ ተሰሎንቄ ከተማ ወደ ቤልግሬድ የሚጓዘዉ ባቡር የግሪክና የሜቄዶንያን ድንበር አልፎ ጄቪጂሊያ ከተማ ባቡር ጣብያ ሲደርስ ነዉ።

Mazedonien Gevgelija Bahnhof Flüchtlinge
ምስል Reuters/S. Nenov


በዚች ትንሽ በሆነችዋ የባቡር ጣብያ የጉዞ ትኬት የገዙ 2000 ስደተኞች ባቡር ለመሳፈር ይጠብቃሉ። ነገር ግን በፉርጎዉ መሳፈር የሚችለዉ ቢበዛ 200 መንገደኛ ብቻ ነዉ። ፖሊሱ በንዴት አሁንም እነዚህ ሁሉ ታድያ ምንድ ናቸዉ? አሸባሪዎች ናቸዉ!» ። ሲል ራሱ ይጠይቃል ። አብሮት ያለዉ ሌላኛዉ ፖሊስ ግን ነገሩን እምብዛም ከቁብ የቆጠረዉ አይመስልም። ባለፈዉ ሳምንት አርብ እዚህ ባቡር ጣብያ ላይ የታየዉ ነገር ግን ከምን ግዜዉም ለየት ያለ ነበር። ዉጥረትና የርስ በርስ ጦርነት ካለባቸዉ የተለያዩ የዓለም ሀገራት የፈለሱና እዚህ ቦታ የተሰባሰቡ ስደተኞች በባቡር ዉስጥ ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ታይተዋል። ሕጻናት በባቡሩ መስኮት ወደ ውስጥ ይወረወራሉ ፤ በርግጥ ቤተሰቦቻቸዉ ይሳፈሩ አይሳፈሩ የሚታወቀ ነገር የለም። ባቡር ቦታ አግኝቶ ለመሳፈር የነበረዉን ትግል መግለፅ እጅግ ያዳግታል። አንዳንዶች በጃቸዉ ጩቤ ይዘዉ ሌላዉን በማስፈራራት ለመግባት ሲሞክሩም ታይተዋል፤ በዚሁ ትግል በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በቅርብ ቀናት የሜቄዶንያ የባቡር ጣብያ ባለሥልጣን መሥርያ ቤት ስደተኞች በሀገሪቱ ዉስጥ ባለዉ ትራንስፖርት ያለምንም ችግር መጠቀም እንዲያስችላቸዉ የሚፈቅድ መታወቅያ ሰጥቶአል። ይህ መታወቅያ ግን የሚያገለግለዉ ለ 72 ሰዓታት ብቻ ነዉ። ከ 72 ሰዓታት በኋላ ስደተኛዉ ሀገሪቱን ለቆ መዉጣት አልያም የተገን ጥያቄን ማቅረብ ይኖርበታል።

እዉነታዉ ግን አንድም ስደተኛ በሜቄዶንያ ተገን የመጠየቅ ፍላጎት የለዉም። በዚህም ስደተኛዉ በሶስት ቀናት ዉስጥ ጂቬጂሊያ ከተማ ከሚገኘዉ የባቡር ጣብያ 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ ሰሜናዊ ሰርብያ መድረስ ይኖርበታል።

Mazedonien Flüchtlingsansturm in Gevgelija
ምስል DW/N. Rujevic


በኢራን፤ ቱርክን አቆራርጦ ብዙ ችግር አይቶ በሜቄዶንያ ጂቬጂሊያ ባቡር ጣብያ የደረሰዉ የ 25 ዓመቱ ፓኪስታናዊ ሞሃመድ በሜቂዶንያ እጅ ለመስጠት አልያም ሀገሪቱን ለቆ ለመዉጣት የቀረዉ አንድ ቀን ብቻ ነዉ። ብዙ የተንገላታው ሞሃመድ በጂቬጂሊያ ከተማ ያለምንም መፀዳጃና መተኛ ሁለት ቀን ማሳለፉን እንደችግር አላየዉም፤


« በፓኪስታን ምን እየሆነ እንደሆነ የፖኪስታንን ቴሌቭዥን አልተከታተላችሁም? ከሁለት ወራት በፊት የታሊባን ቡድን አንድ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት አድርሶ በርካታ ሕጻናትን ገድሎአል። ምንም አይነት ሐጥያት በደል ያልፈፀሙ የስምንት እና የስድስት ዓመት ልጆች ነበሩ»


እንደ ሞሃመድ አይነቱ ስደተኛ ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ የጂቬጂሊያ ከተማ ከንቲባ ኢቫን ፍራንጎቭ አንድ ነገር ለማድረግ ሃሳብ አቅርበዋል። ከሃንጋሪ ልምድ በመቅሰም በሜቂዶንያ እና በግሪክ ድንበር ላይ አጥር እንዲቆም ነዉ ሲሉ ሃሳብ ያቀረቡት። ከንቲባ ኢቫን በሰርብያ የዜና አገልግሎት «ታንዩግ » ላይ ቀርበዉ እንደተናገሩት ወደ ሃገሪቱ የገቡት እንዚህ ስደተኞች ከተማዋን ያቆሽሻሉ፤ የአዉሮጳዉ ሕብረትና ፤ የሕብረቱ የስደተኞች ጉዳይ መሥርያ ቤት ደግሞ ስለጉዳዩ የሆነ መፍትሄ ማድረግን ረስቶአል። ይህን አይነቱን አነጋገር ግን የመቂዶንያዋ የጂቬጂሊያ ከተማ ነዋሪ በሙሉ በአዎንታ አይቀበለዉም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሸልባ የነበረችዉ ከተማ በስደተኞቹ የሥራ ዉጋጋንን በማየትዋ ነዉ።

Mazedonien Flüchtlingsansturm in Gevgelija
ምስል DW/N. Rujevic

ነዋሪዎችዋ ለስደተኞቹ ሁለት ሙዝ በአንድ ይሮ፤ አንድ አነስ ያለ ከረጢት ፍንዳድሻ በቆሉ እና አንድ ላስቲክ የጠርሙስ ዉኃ በአንድ ይሮ፤ በመሸጥ ሥራን በማግኘታቸዉ ነዉ። ነዋሪዉ ለስደተኞቹ የተንቀሳቃሽ ስልክ የኤሌትሪክ ኃይል በመሙላትም ገንዘብን ያገኛል። ለአካባቢዉ ፖሊስ በዚህ ጥቅም የሚያገኙት ሁለቱም ወገን ተጠቃሚዎች ምንም አይነት ችግርን አያስከትሉም፤ ለመከልከልም አልተነሳም። ከፓኪስታን የመጣዉ ስደተኛ ሞሃመድ ግን ይህ ሁሉ ነገር አያሳስበዉም።
መሃመድ ብዙዎች ወደ አዉሮጳ ስለሚፈልሱ፤ እሱም እነሱን እንደሚከተል ይናገራል። እንደ መሃመድ፤ ተገን የሚጠይቀዉ ተስፋ የሚያገኝው ትክክለኛዉ አዉሮጳ ሲደርስ ነዉ። መሃመድ እድል ከቀናኝ ይላል፤ « እድል ቀንቶኝ ጀርመን ከገባሁ፤ አንድ ጥሩ ስራ ይዤ የወደፊት ህይወቴን እገነባለሁ» መሃመድ « ከቀናኝ!» የሚለውን አባባሉን እንደገና ደግሞታል ።


አዜብ ታደሰ / ሩጄቪክ ኔሚኒያ


ኂሩት መለሰ