1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜይ ፈተና

ዓርብ፣ ሰኔ 9 2009

ተችዎች እንደሚሉት ሜይ ምርጫው አስቀድሞ እንዲጠራ ያደረጉት በተቀናቃኛቸው በሌበር ፓርቲ ውስጥ ግጭት በተፈጠረበት እና የሌበር ፓርቲ መሪ ጀርሚ ኮርቢን በህዝብ አሰተያየት መመዘኛ ድጋፋቸው አንሷል በተባለበት አጋጣሚ በሚካሄድ ምርጫ ያለ አንዳች ችግር ለተጨማሪ 5 ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ለማረጋገጥ ነበር። ይህ ግን አልሰመረም።

https://p.dw.com/p/2ecfK
London May nach Parlamentswahl
ምስል Getty Images/AFP/O. Andersen

ሜይ የገጠማቸው ፈተና

ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት የምትጀምረው ድርድር ሲቃረብ የተካሄደው የብሪታንያ ምርጫ ውጤት አስደምሞ ከርሟል። ወቅቱን ያልጠበቀው ምርጫ ውጤት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የቴሬሳ ሜይን ምኞት አላሳካም።  ልዩ ልዩ ጫናዎችንም አስከትሎባቸዋል። 
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተካሄደው የብሪታንያ ምርጫ የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ እና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን ያሸማቀቀ፣ አብላጫ ድምጽ ያሳጣ እና የሰሜን አየርላንድ ፓርቲ ድጋፍ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደረገ ነበር። በምርጫው የፈለጉትን ውጤት ማግኘት ያልቻሉት ሜይ ከሰሜን አየርላንዱ ዴምክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ DUP ጋር ተጣምረው አዲስ መንግሥት ለመመስረት እየተነጋገሩ ነው። ሜይ ባለፈው ሚያዚያ  ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ እንዲጠራ ያደረጉት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት የምትወጣበትን የብሪክዚትንድርድር ፣ በተጠናከረ አቅም ለማካሄድ በሚል ነበር።  
«በአውሮጳ ለብሪታንያ የሚጠቅም የተሻለ ስምምነት ላይ መድረስ የሚችል፣ህዝብ እምነት የሚጥልበት ጠንካራ እና የተረጋጋ አመራር የማግኘት ጉዳይ ነው፤ ለብሪክዚት ፍላጎቱ ያለው እና ወሳኝ የሆነውን እቅድ የሚያቀርብ።»
ሜይ ከስምንት ሳምንት በፊት ይህን ባሉበት ወቅት በምርጫው ፓርቲያቸው በርካታ መቀመጫዎችን ያገኛል፤ተቀናቃኙ የሌበር ፓርቲ ደግሞ ተንኮታኩቶ ይወድቃል የሚል ነበር ትንበያው ። ይሁን እና ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነው የሆነው። ሜይ የተሻለ አቅም ያስገኝልኛል ባሉት በዚህ ምርጫ ፓርቲያቸው ቀድሞ ከነበረው መቀመጫ 12 ቱን አጥቷል። ከ650ው የብሪታንያ ምክር ቤት መቀመጫ ፓርቲያቸው ያሸነፈው 318 ቱን ነው። ውጤቱ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ቢበልጥም ፓርቲያቸውን ብቻውን መንግሥት መመሥረት አላስቻለውም። በብሪታንያ የምርጫ ህግ አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት 326 መቀመጫዎችን ማግኘት አለበት። ይንኮታኮታል የተባለው ሌበር 30 ተጨማሪ መቀመጫዎችን በማሸነፍ በምክር ቤቱ የመቀመጫዎቹን ቁጥር ወደ 262 አሳድጓል። ብሔረተኛው የስኮትላንድ ፓርቲ መቀመጫዎች ደግሞ ወደ 35 ዝቅ ብለዋል። በአሁኑ ምርጫ ፓርቲው 21 መቀመጫዎችን አጥቷል።  ፍጹም ካልተጠበቀው ከዚህ ምርጫ ውጤት በኋላ ሜይ የፈለጉትን ባያገኙም ሊገጥሟቸው የሚችሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያሳወቁት። እንደ ብሪታንያ ልምድ ከንግሥት ኤልሳቤጥ፣ መንግሥት የመመሥረት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ባሰሙት ንግግር ወቅቱን ላልጠበቀው ምርጫ ሰበብ ባደረጉት በብሬክዚት ድርድር መንግሥታቸው የህዝቡን ፍላጎት እንደሚያሟላ ቃል ገብተዋል።
«ይህ መንግሥት በ10 ቀናት ውስጥ በሚጀመረው በወሳኝ የብሬክዚት ንግግር ውስጥ ሀገሪቱን ይመራል። ብሪታንያን ከአውሮፓ ህብረት በማስወጣት የብሪታንያ ህዝብ ፍላጎት ያሟላል።»
ተችዎች እንደሚሉት ሜይ ምርጫው አስቀድሞ እንዲጠራ ያደረጉት በተቀናቃኛቸው በሌበር ፓርቲ ውስጥ ግጭት በተፈጠረበት እና የሌበር ፓርቲ መሪ ጀርሚ ኮርቢን በህዝብ አሰተያየት መመዘኛ  ድጋፋቸው አንሷል በተባለበት አጋጣሚ በሚካሄድ ምርጫ ያለ አንዳች ችግር ለተጨማሪ 5 ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ለማረጋገጥ ነበር። ይሁን እና በዚህ ምርጫ «የሜይ ዓላማ» የተባለው አልሰመረም። ይልቁንም ድጋፍ የላቸውም የተባሉት የሌበሩ መሪ የተሻለ እና ያልተጠበቀ ውጤት በማስመዝገብ ባለድል ሆነዋል። በብሪታንያው የበርሚንግሀም ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ማቲው ኮል ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ኮርቢንን ከዚህ ቀደም ያጣጥሉ የነበሩት የፓርቲያቸው አባላት ሳይቀሩ አሁን የቀደሞ ይሰነዝሩባቸው የነበረውን ነቀፌታ ስህተት ነበር እያሉ ነው።
« ኮርቢን በምርጫው ውጤት ተሸንፈዋል። በብዙ መንገድ ሲታይ ግን አሸናፊው እሳቸው ናቸው። በፓርቲያቸው ውስጥ የሚቃወሟቸውን ተጠያቂ ማድረግ አቁመዋል። አጥብቀው ይተቿቸው ለነበሩ ጄስ ፊሊፕስ ወይም ጃክ ድሮሚን ለመሳሰሉ የፓርቲያቸው አባላት አሁን የሌበር መልዕክት እየሰራ ነው። አንዳንዶቹ ኮርቢን እጅግ በጣም ጥሩ ዘመቻ እንዳካሄዱ እነርሱ ግን በተሳሳተ መንገድ ይረዷቸው እንደነበር በግልጽ እየተናገሩ ነው ።»
ኮርቢን ከሜይ በተለየ ከሁሉ አስቀድሞ ህዝብን አሰልችቷል ያሉትን ቁጠባ ለማስቀረት ነበር ቃል የገቡት። ከዚህ ሌላ ለሁሉም በዩኒቨርስቲዎች ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ ለማድረግ የህጻናት የጤና እንክብካቤም ያለ ከክፍያ ነጻ እንዲሆን ለጤና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እንዲደረግ ቃል ገብተዋል። እነዚህ እና ሌሎችም ቃል የገቡባቸው ጉዳዮች ብዙ መራጮች ማግኘት እንዳስቻሏቸው ይታመናል።በአንጻሩ የሜይ መርህ ለአዛውንቶች እንክብካቤ ከሚወጣው ገንዘብ ቤተሰቦች አብዛኛውን እንዲሸፍኑ እንዲሁም መንግሥት ከሚሰጣቸው ድጎማዎች የተወሰኑት እንዲቆሙ የሚጠይቅ መሆኑ በርካታ ድምጾችን ለማጣታቸው ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል። «ለጥቂቶች ሳይሆን ለብዙዎች» የሚል የምርጫ ዘመቻ መርህ የነበራቸው ጀርሚ ኮርቢን በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሁለት የሽብር ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ መዘው ያወጡት የሜይ የቀደመ ውሳኔ በውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረም ይገመታል። ሜይ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ባገለገሉበት በ6 ዓመታት የፖሊሶች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ኮርቢ በዘመቻው ወቅት ካነሱ በኋላ ትኩረቱ ወደ ሀገሪቱ የፀጥታ ጉዳዮች እንዲሆን አድርጎት ነበር። ኮርቢ ከምርጫው በኋላ ደግሞ ሜይ ከሥልጣን መልቀቅ አለባቸው ብለዋል 
«ጠቅላይ ሚኒስትሯ ምርጫ የጠሩት ሥልጣን ፈልገው ነበር። ያገኙት ግን የወግ አጥባቂዎችን መቀመጫዎች ማጣት፣ ድምጾችን ማጣት ድጋፍ እና የመታመኛ ድምጽ ማጣት ነው። ይህ በርግጥ እኔ እንዳሰብኩት ከሥልጣን ለመውረድ በቂ ነው።»
ሜይ ከሥልጣን እንዲለቁ የጠየቁት ተቀናቃናቸው ኮርቢ ብቻ አይደሉም። ከፓርቲያቸው አባላትም አንዳንዶቹ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል። አና ሶብሪ የቀድሞ ሚኒስትር እና ብሪታንያ በአውሮጳ ህብረት አባልነት እንድትቆይ ዘመቻ ያካሄዱ የነበሩ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኛ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የህዝቡን ስሜት አያዳምጡም ከሰዎች ጋር አይቀራረቡም የሚሏቸው ሜይ መነሳት አለባቸው።
«ለረዥም ጊዜ እንዴት ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አይታየኝም። ያሳዝናል ግን መነሳት ያለባቸው ይመስለኛል። ሆኖም መረጋጋት ያስፈልገናል። ይበልጥ ግልጽ መሆን አለባቸው፣ህዝቡን ማዳመጥ አለባቸው። በምክር ቤት ውስጥ በአግባቡ ሊወክሉን ይገባል። እነዚህን ካደረጉ ሥልጣን የሚለቁበትን መንገድ ያመቻቻሉ። ከዚያ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖረናል።»
ከውጤቱ በኋላ ዶቼቬለ አስተያያየታቸውን የጠየቃቸው ድምጽ የሰጡ ዜጎች ሜይ አብላጫ ድምፅ ባለማግኘታቸው በእጅጉ አዝነዋል። ከመካከላቸው እኚህ ድምፅ ሰጭ ከምንም በላይ ለምርጫው የጠፋው ገንዘብ እና ጊዜ ይቆጫቸዋል።
«ለሌላ ውጤታማ ነገር ሊውል የሚችል ብዙ የቀረጥ ከፋይ ገንዘብ እና አስተዳዳራዊ ጥረት እንዲሁም የሁለት ወራት ጊዜ አባክነናል። በዚህ ጊዜ ለቴሬሳ ሜይ ምኞት ሳይሆን ለብሬክዚት ማቀድ እንችል ነበር። ከቀናት በኋላ የብሬክዚት ድርድር ይጀመራል። አሁን የኛ አቋም በጣም ተዳክሟል። ሜይ በሀገሪቱ ላይ ይህን አድርገዋል። እጣ ፈንታችንን ለአጠራጣሪ ሁኔታ ዳርገውታል ።»
ለእኚህ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ሜይ መቅደም የነበረበትን ባለማስቀደማቸው ስህተት ሰርተዋል።
«በርግጥ ይህ ምስቅልቅል ያለ ነገር ነው። አዝናለሁ፤ ሜይ ብሪክዚትን በይፋ ማንቀሳቀስ ከመጀመራቸው በፊት ነበር ይህን ምርጫ ማካሄድ የነበረባቸው።»
ለእኚህ ብሪታንያዊ ውጤቱ አሳፋሪ ነው ።
«ወሳኝ የሆነው ብሬክዚት እየተቃረበ በመጣበት ወቅት እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን አሳፋሪ ነው።»
የፖለቲካ ተንታኞችም ሜይ በስልጣን የመቆየት እድላቸው የተመናመነ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ፕሮፌሰር ጌርሀርድ ዳነማን በበርሊኑ የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የብሪታንያ የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ማዕከል ሃላፊ ናቸው በርሳቸው አስተያየት ሜይ ከአሁን በኋላ በሥልጣን ላይ መቆየቱ አጅግ አዳጋች ይሆንባቸዋል። ዳነማን እንደሚሉት ያም ተባለ ይህ ሜይ ከሥልጣን መውረዳቸው አይቀርም። 
«ይህ የማይቀር ነው። ቴሬሳ ሜይ ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለመቀጠል በጣም በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆንባቸው። 
ምንም እንኳን ሜይ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከየአቅጣጫው ግፊት ቢደረግባቸውም ሥልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ አይመስሉም። ትናናት በብሪታንያ ፓርላማ ለተወከሉ የፓርቲያቸው አባላት ባሰሙት ንግግር 
«እዚህ ችግር ውስጥ የከተትኳችሁ እኔ ነኝ ከችግሩ የማወጣችሁም እኔው ነኝ ሲሉ» ቃል ገብተውላቸዋል ። ጥያቄው የድርድር አቅማቸው ተዳክሟል የተባለው ሜይ የወደፊቱን ሃላፊነት  እንዴት ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ነው።

Infografik Wahlergebnis Unterhauswahl UK Großbritannien AMH
Arlene Foster, Parteichefin der nordirischen DUP und Theresa May
ምስል picture-alliance/empics/C. McQuillan
Großbritannien Wahlen 2017 – Jeremy Corbyn
ምስል picture alliance/PA Wire/D. Lipinski

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ