1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራባውያን ናቫልኒ እንዲፈታ ጥሪ አቀረቡ

ሰኞ፣ ጥር 10 2013

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተቺ አልክሲ ናቫልኒ ከታሰረ በኋላ ምዕራባውያን ብርቱ ትችት መሰንዘር ጀመሩ። ናቫልኒ ለአምስት ወራት ገደማ በጀርመን ያደረገውን ሕክምና አጠናቆ ትናንት ወደ ሩሲያ ሲመለስ በሞስኮ ሼሬሜቲቫ አውሮፕላን ማረፊያ የፓስፖርት መቆጣጠሪያ እንደደረሰ በጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውሏል።

https://p.dw.com/p/3o5zN
Russland Moskau | Flughafen Scheremetjewo | Alexej Nawalny
ምስል Polina Ivanova/REUTERS

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተቺ አልክሲ ናቫልኒ ከታሰረ በኋላ ምዕራባውያን ብርቱ ትችት መሰንዘር ጀመሩ። ናቫልኒ ለአምስት ወራት ገደማ በጀርመን ያደረገውን ሕክምና አጠናቆ ትናንት ወደ ሩሲያ ሲመለስ በሞስኮ ሼሬሜቲቫ አውሮፕላን ማረፊያ የፓስፖርት መቆጣጠሪያ እንደደረሰ በጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውሏል። የሩሲያ መንግሥት ብርቱ ተቺ እየተባለ የሚጠራው ናቫልኒ ከሞስኮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኝ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በዚያው በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተሰየመ ችሎት ዛሬ ሰኞ ጉዳዩ የታየው ናቫልኒ ሒደቱን «በፍትህ መሳለቅ» ሲል ተችቷል። የናቫልኒ ረዳቶች እንደተናገሩት ከጠበቆቹ እንዳይገናኝ የተከለከለ ሲሆን ከችሎት እንደሚቀርብ እንኳ የተነገረው ባለቀ ሰዓት ነው። 
ረዳቶቹ በለቀቁት እና የችሎቱን ሒደት በሚያሳይ ቪዲዮ አሌክሲ ናቫልኒ «በፍትሕ ሒደቱ ላይ በርካታ ስላቅ ተመልክቻለሁ። ፍትሐዊ ሒደቱን ቀደው ጥለውታል» የሚል ነቀፌታ አሰምቷል። የሩሲያ የእስር ቤት አስተዳደር ናቫልኒ ከዚህ ቀደም በማጭበርበር ክስ የተጣለበትን እና በይርጋ የታገደ ቅጣት በመተላለፉ እንዳሰረው አስታውቋል። የሩሲያው ፍርድ ቤት የ44 አመቱ ናቫልኒ ለ30 ቀናት እንዲታሰር ውሳኔ ማስተላለፉን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ ናቫልኒ ከዚህ ቀደም በቀረበበት ክስ ለባለሥልጣናቱ ሪፖርት እንዲያደርግ የተላለፈበትን ውሳኔ ወደ ጀርመን በመጓዝ በመጣሱ ጥፋተኛ ሆኖ እንዳገኘው የዜና ወኪሉ ጨምሮ ዘግቧል። ናቫልኒ ግን ከሰባት አመታት በፊት የቀረበበትን እና ለትናንትናው እስር አብቅቶታል የተባለውን ክስ ፖለቲካዊ ሲል ያጣጥላል። 
ናቫልኒ ትናንት ወደ ሞስኮ ሲያመራ ሊታሰር እንደሚችል ቢያውቀውም ለምዕራባውያን ግን ተቀባይነት አላገኘም። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሐይኮ ማስ የሩሲያን እርምጃ «ለመረዳት የሚቸግር» ብለውታል። «ሩሲያ በራሷ ሕገ-መንግሥት እና በተስማማችባቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረት የሕግ የበላይነትን እና የሲቪል መብቶችን የማክበር ግዴታ አለባት» ያሉት ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ «ይኸ መርኅ ለአሌክሲ ናቫልኒም ሊተገበር ይገባል» ብለዋል። 
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ደር ላየን፣ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ዶሚኒክ ራብ እና የሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሩሲያ ናቫልኒን እንድትፈታ ጥሪ አቅርበዋል። ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሱሊቫን «ናቫልኒ በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል። በሕይወቱ ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸሙ ተጠያቂ መሆን አለባቸው» ብለዋል።

Russia Moskau Alexej Navalny Oppositionskritiker
ምስል Kira_Yarmysh/AP/picture alliance

 

እሸቴ በቀለ 

አዜብ ታደሰ