1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞርጋን ሻንጋራይ ሲታወሱ

ቅዳሜ፣ የካቲት 10 2010

የዚምባብዌዉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ሞርጋን ሻንጋራይ በዚምባባዌ ፖለቲካ ጉልህ አስዋጽኦ ያላቸዉ ሰዉ ነበሩ። ሻንጋራይ በጎርጎሮሳዉያኑ 1999  የዲሞክራሲ ለዉጥ ንቅናቄ ፓርቲ በምህጻሩ DMC ን በመመስረት በሀገሪቱ ፖለቲካ የሮበርት ሙጋቤን  ዛኑፒኢፍ ፓርቲ በብርቱ መፎካከርም የቻሉ ጠንካራ ሰዉ ተደርገዉም በብዙዎች ዘንድ ይወሰዳሉ።

https://p.dw.com/p/2spLY
Simbabwe Zitattafel Morgan Tsvangirai

Amh.Fokus Afrika17/2/2018 The Death of Morgan Tsvangarai - MP3-Stereo


 እኝህ ሰዉ ያለፈዉ ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010 ዜና እረፍታቸዉ ተሰምቷል።  ለዚምባቡዌ ለውጥ ለረዥም ጊዜ በመታገል ስለሚታወሱት ሻንግራይ ታሪክ የዛሬዉ የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት ቅኝት ያደርጋል።
 

ዚምባብዌን ለጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚንስትርነት ያገለገሉት ሞርጋን ሻንጋራይ ሀገሪቱ ዉስጥ ለሁለት አስርት ዓመታት ባሳረፉት የዲሞክራሲ አሻራ ብዙዎች ያስታዉሷቸዋል።
የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለለዉጥ ፓርቲ መስራች የሆኑት ሻንጋራይ ለ37 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይተዉ ያለፈዉ ጥቅምት ከስልጣን የወረዱትን  ሮበርት ሙጋቤንና  መንግሥታቸዉን  በብርቱ የተገዳደሩ እና የሚተቹ ነበሩ። በሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓትም ከሙጋቤ ፓርቲ ማለትም የዚምባቡዌ ብሔራዊ የአፍሪቃ አንድነት የአርበኞች ግንባር በምህፃሩ ዛኑፒኤፍ ዉጭ ሌላ አማራጭ እንዳለ ለዚምባቢዌ ህዝብ ያሳዩ ናቸዉ ይሏቸዋል። የዚምባብዌ ብሄራዊ የተማሪዎች ሕብረት መሪ ኦስታሎስ ጊፍት ሲሚባ ያለሻንጋራይ ስለ ዲሞክራሲ ማሰብ አይቻልም ነበር ይላል።

«ሞርጋን ሻንጋራይ ባይኖር ኖሮ ስለ ዲሞክራሲ ማዉራት ባልተቻለ ነበር ።ይህንን እንድናገር ያደረገኝ የእርሱ ቁርጠኝነት ነዉ። እርሱ ሮበረት ሙጋቤ ባደራጀዉ ያረጀ እና ጨካኝ የአምባገነናዊ የፖለቲካ አስተዳደር እስከ 1990 ድረስ አብሮ ሲታገል ቆይቷል።»

Zimbabwe Oppositionsführer Morgan Tsvangirai
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

የፓርቲያቸዉ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ኤልያስ ሙድዙሪ የዚህን የፓለቲካ ጀግና ዜና እረፍት ይፋ ማድረግ አሳዛኝ ነዉ ሲሉ በቲዉተር ገፃቸዉ አስፍረዋል ።
በሙጋቤ መንግሥት እስር እንግልትና ወከባ እንደደረሰባቸዉ የሚነገርላቸዉ ሻንጋራይ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በካንሰር በሽታ መያዛቸዉን ይፋ ያደረጉት፤ይህንን በማድረጋቸዉም በዚምባብዌ የተቃዉሞ ፓለቲካ እንደ ጀግና እንዲታዩ አድርጓቸዋል። የብሪታንያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በቲዉተር ገፃቸዉ እንዳሰፈሩት «ሻንጋራይ በጨቋኞች ፊት በድፍረትና በቆራጥነት መቆም የቻሉ የዚህ ዘመን ጀግና የፖለቲካ መሪ ነበሩ» ብለዋቸዋል። ነገር ግን ይህንን ጀግና በሚያሳዝን ሁኔታ አጣነዉ ሲሉ አክለዋል።
የዲሞክራሲ ንቅንቄ ለለዉጥ ፓርቲ አባል ዴቪድ ኮልታሮት በበኩላቸዉ ሻንጋራይ እንደ አንድ የዚምባብዌ ታላቅ አርበኛ ሲታወሱ ይኖራሉ ነው ያሉት። ሻንጋራይ እንደማንኛችንም ስህተት ሊሰራ ይችላል ነገር ግን ዚምባብዌን ዲሞክራሲያዊ ፣ ዘመናዊና መቻቻል የሰፈነባት ሀገር ለማድረግ በርትቶ መስራቱን ግን ማንም አይጠራጠርም ብለዋል።
በጎርጎሮሳዊዉ 1952 ከገበሬና የማዕድን አዉጪ ሰራተኛ ቤተሰብ የተወለዱት ሻንጋራይ በ1980 ዓ/ም ነበር የአዲሲቷን ነፃ ሀገር ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍን የተቀላቀሉት ይሁን እንጅ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ፓርቲዉን በይፋ መተቸት ጀመሩ። እናም በዚሁ ዓመት የተደረጉ በርካታ የተቃዉሞ ሰልፎችንና የሠራተኛ የሥራ ማቆም አድማዎችን መምራትና ማደራጀት ቀጠሉ። በዚህም ለዉጥ አምጥተዉ እንደነበር ሞርጋን ኮሚቺ ይገልጻሉ።

Morgan Tsvangirai
ምስል picture-alliance/Photoshot

«ሻንጋራይ ታላላቅ የህዝብ የተቃዉሞ ሰልፎችንና የሠራተኛ የሥራ ማቆም አድማዎችን መርቷል። የሠራተኞች መብት በዚምባብዌ እንዲከበር ተደራድሯል። ለዉጥም አምጥቷል።»
 በ1999 ዓ/ም ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለለዉጥ በምህፃሩ /DMC / የተሰኘ ፓርቲያቸውን መሰረቱ። በ2002 ዓ/ም በሀገሪቱ በተካሄደ ብሄራዊ ምርጫም ለመጀመሪያ ጊዜ የሙጋቤ በመፎካከር ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነዉ ቀረቡ። ከዚህ ምርጫ በኋላ ግን ሻንጋራይ በመንግሥት ጥርስ ዉስጥ በመግባታቸዉ የተነሳ ተደጋጋሚ እስርና ስቅይት ተፈጸመባቸዉ። ይሁን እንጅ ትግላቸዉን በመቀጠል በሀገሪቱ በ2008 በተካሄደ ምርጫም ተወዳዳሪ ሆነዉ ቀረቡ። በዚህ ምርጫ ምንም እንኳ አሸንፈዉ መንግሥት ባይመሰርቱም ከሙጋቤ መንግሥት ጋር ጥምር መንግሥት መስርተዉ ጠቅላይ ሚንስትር  ለመሆን በቅተዋል። ያም ሆኖ ግን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለረዥም ጊዜ በቆየባት ዚምባብዌ  የሻንጋራይ መንገድ ቀላል አልነበረም ሲል የሀገሪቱ የተማሪዎች ህብረት መሪ ይናገራል።
  «ቀላል አይደለም ።ሮበርት ሙጋቤ በዚህ ሀገር አንድ የፓርቲ ስርዓት መገንባት ነዉ የፈለገዉ። ይህ ሀሳብ ነዉ በዚምባቤያዉያን የተወሰደዉ። አዲስ የማህበራዊ ዲሞክራሲ መዝሙርን ማስተዋወቅ ለሻንጋራይ ቀላል አልነበረም።»
የ DMC ፓርቲ አባል ፋራሪ ጌዊንሁሬ በበኩላቸዉ መንግሥት ማለት ዛኑ ፔኢፍ ብቻ ነዉ ብለዉ ለሚያስቡ የሀገሬዉ ሰዎች ሻንጋራይ የተለዬ መንገድ ያሳዩ ሰዉ ናቸዉ ይሏቸዋል።
«በዚምባብዌ ፖለቲካ በብዙ ሰዎች ዘንድ መንግሥት ማለት ዛኑ ፒኤፍ ብቻ  ነዉ የሚል አስተሳሰብ ነበረ። በሻንጋራይ መሪነት የስልጣን መጋራት ስምምነት ሲፈጸም ግን፤ ሀገሪቱን ወደፊት እንድትራመድና ኢኮኖሚዋም የተረጋጋ እንዲሆን ሊያደርጉ የሚችሉና በተለዬ መንገድ የሚሰሩ ዝምባቤያዉን እንዳሉ ነዉ ሁሉም  ያስተዋለዉ።»
ሻንጋራይ ከሙጋቤ መንግስት ጋር በወቅቱ ጥምር መንግስት መመስረታቸዉ በሀገሪቱ መቻቻል የሰፈነበት ፖለቲካ ለማራመድ የሚጥሩ ሰዉ መሆናቸዉን ያሳዩና የሀገሪቱ ዜጎችም በመጠኑም ቢሆን የለዉጥ ስሜት እንዲሰማቸው ያደረገ ነበር። ይህ ተግባራቸዉ ግን በተቃዋሚ ኃይሎች ዘንድ እምብዛም የተወደደ እንዳልነበረ ሞርጋን ሻንጋራይ ለዶቼ ቬለ ገልጸዉ ነበር።
«የዲሞክራሲ ንቅናቂ ለለዉጥ ከዛኑ ፒኤፍ ጋር ጥምረት ዉስጥ ሲገባ ሀገርን ለማዳን ነበር ።ስምምነቱ እርግጥ ነዉ ፍጹም አልነበረም ነገር ግን  ሀገሪቱን ከዉድቀት ለማዳን ይቻል ይሆናል ብዬ አስቤ ነዉ።በተቃዋሚ ሀይሎች ዉስጥ በተካሄደዉ የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ምክንያት አንዳንድ ጉዳት ሊኖር ይችላል።» 
ለዚህም ይመስላል አሌክሳንደር ራሶር የተባሉ የዚምባብዌ የፖለቲካ ተንታኝ ሻንጋራይ ከግል ህይወታቸዉ ይልቅ በዚምባብዌ የተቃዉሞ ፖለቲካ ዋና ገፀ-ባህሪ ሆነዉ ያለፉ ሰዉ ናቸዉ በማለት ለአጃንስ ፍራን ፕሬስ የተናገሩት።
የሞርጋን የሻንጋራይ ሞት ለአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስልጣናቸዉን ያደላድላል የሚሉ ቢኖሩም ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ለለዉጥ ፓርቲ ግን የመከፋፈል አደጋ ተደቅኖበታል ነዉ የተባለዉ። ራሳቸዉ በሚመሩት ፓርቲም ይሁን በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ እንደ ምሰሶና ተምሳሌት የሚቆጠሩትን ሻንጋራይን ማጣት በተቃዉሞ ጎራ ላሉ የዚምባቡዌ ፓለቲከኞች ቀላል እንዳልሆነ ከወዲሁ እየተነገረ ነዉ።
ፓርቲያቸዉን ለመምራት የሚተካ ሰዉ ማግኜት ላይ ከወዲሁ መከፋፈል እንዳለም እየተነገረ ነዉ። እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር ሻንጋራይ ይፈቱበት የነበረዉ መንገድ በብዙዎች ዘንድ ከበሬታ እንዲያተርፉ ካደረጋቸዉ ምክንያት አንዱ ነበር ይላሉ የፓርቲዉ አባል ፤ሞርጋን ኮሚቺ።
«የዲሞክራሲዊ ንቅናቄ ለለዉጥ /DMC/ ን ለማዋሃድ ብዙ ጊዜ ሰርቷል። በፓርቲዉ ዉስጥ ችግሮች ሲከሰቱ መፍትሄ በመፈለግ ፓርቲዉን አሁን ድረስ አቆይቶታል። እናም በፓርቲዉ ደጋፊዎች ከፍተኛ  አክብሮት ነበረዉ። በፓርቲዉ ዉስጥ መከፋፈል ሲፈጠር ምንም ይሁን ምን በእርሱ ላይ አመኔታ አላቸዉ። እናም ንቅናቄዉ ቀጥሏል። እርሱ ፋና ወጊና ባለ ራዕይ ነዉ።»
በጎርጎርጎሮሳዊዉ 2008 ዓ/ም ባለቤታቸዉን በመኪና አደጋ ያጡት ሞርጋን ሻንጋራይ ላለፉት ሁለት ዓመታት በካንሰር ህመም ሲሰቃዩ ቆይተዉ ለህክምና በሄዱበት ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ነበር ያለፈዉ ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010ዓ,ም በተወለዱ በ 65 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

Simbabwe Präsident Emmerson Mnangagwa besucht kranken Oppositionsführer Morgan Tsvangirai
ምስል DW/P. Msvanhiri
Simbabwe Opposition Nelson Chamisa
ምስል picture-alliance/AP/T. Mukwazhi

ፀሓይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ