1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሡዳን፤ሠላምና ጦርነት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2004

ሱዳን ነዳጅ ዘይት ወደ ዉጪ መላክ ከጀመረችበት ከሁለት ሺሕ ጀምሮ የድሕነትን ማቅ ካናቷ፥ ወደ ደረቷ ዝቅ ማድረግ ችላ ነበር።ሐብቷ, ጠላቷ ለመሆን ግን ብዙ አልቆየም።ሁለት የመከፈሏ ጉዞ ይጣደፍ፥ የዳርፉር ጦርነት፥ የቤጃ ጦርነት፥ይጋጋም ገባ

https://p.dw.com/p/14joM
A SPLA soldier walks in a market destroyed in an air strike by the Sudanese air force in Rubkona near Bentiu April 23, 2012. Sudanese warplanes carried out air strikes on South Sudan on Monday, killing three people near the southern oil town of Bentiu, residents and military officials said, three days after South Sudan pulled out of a disputed oil field. REUTERS/Goran Tomasevic (SOUTH SUDAN - Tags: CIVIL UNREST POLITICS TPX IMAGES OF THE DAY)
ምስል Reuters

ሱዳንን እሁለት የገመሰዉ ስምምነት ባይቀብር ሞቷል።የደቡብ ሱዳኖችን የነፃነት ፌስታ ባይጠፋ ተጨናጉሏል።ሱዳኖች ስምምነት ፌስታዉን ያጠፋዉን ጦርነት እንዲያቆም ዓለም መምከር፣ ማስጠነቀቁን አላባራም።ኢትዮጵያ ለሽምግልና መጠየቋ ከአዲስ አበባ በተሰማ በማግስቱ ግን ዩጋንዳ ለጁባዎች ወግና ካርቱሞችን ለመዉጋት መዛቷ ከካምፓላ ተዘገበ።አርብ።ዩጋንዳ በአፍሪቃ ሕብረት ስም ሞቃዲሾ፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥም አብዬ ላይ ሠራዊት አስፍረዋል። የሱዳኖች ጦርነት መነሻ፥ የሠላም ዉላቸዉ ማጣቃሻ የዓለም ሚና የሱዳን ጎረቤቶች አቋም መድረሻችን ነዉ። ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
               
«ዋና ፀሐፊዉም ደዉለዉልኝ ነበር» አሉ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር፣ ያዘመቱት ጦር ሒጂሊጅን በተቆጣጠረ ባረተኛዉ ቀን ለታተመዉ ሱዳን ትሪቡን ለተሰኘዉ ጋዜጣ።የተባበሩት መግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙንን ማለታቸዉ ነበር።«ሒጂሊጅን ለቃችሁ ዉጡ አሉኝ።»ቀጣዩ አረፍተ ነገር በርግጥ አጭር ነበር ግን አጓጊ።ቀጠሉ ፕሬዝዳንቱ፣ «በርስዎ ዕዝ ሥር ሥላይደለሁ እኔን ለማዘዝ አይጨነቁ አልኳቸዉ።» እያሉ።

ከደፈጣ ዉጊያ ወደ አዲስ ሐገር መሪነት የተለወጡት የደቡብ ሱዳን  ነፃ  አዉጪ ጦር ወይም ንቅናቄ መሪዎች እንደ መንግሥት ሐገር ለመምራት፥ የፖለቲካ ዲፕሎማሲዉን ዉጥንቅጥ በቅጡ ለመረዳት በርግጥ በቂ ጊዜ አላገኙም።በዓለም አቀፉ የሥልት ጥናት ተቋም ኢትዮጵያዊዉ የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ብሩክ መስፍን እንደሚሉት ደግሞ ጁባዎች ካዲስነታቸዉም፥ ከካርቱሞች ሌላም-ሌላ ዉስጣዊ የሚባል ችግር አለባቸዉ።
              

የሰሜን ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አል-በሽር ከፍተኛ አማካሪያቸዉን ሙስጠፋ ዑመር ኢስማኢልን ወደ አዲስ አበባ የላኩት፥ከጦርነቱ መሠረታዊ ምክንያት ጋር የሳልቫ ኪር መግለጫ  በሚያነጋግርበት ወቅት ነበር።

የልዩ አማካሪ የሙስጠፋ ዑመር ኢስማኤል ተልዕኮ ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር ጦራቸዉን ከሒጂሊጅ ያስወጡ ዘንድ የአፍሪቃ ሕብረትና ኢትዮጵያ እንዲያግባቧቸዉ ሽምግልና ብጤ ለመጠየቅ ነበር።የአል-በሽር መንግሥት ምናልባት ከሳልቫ ኪር መንግሥትም የበለጠ ዉስጣዊ በሚባል ችግር የተወጠረ ነዉ።የዳርፉር ጦርነት፥ የሰሜን ኮርዶፋን ጦርነት፥ የሕዝቡ ቅሬታ፥ የተቃዋሚዎች ጥያቄ እና ሌላም።እንደገና አቶ ብሩክ።
          

ያም ሆኖ አል-በሽር ልዩ መልዕክተኛቸዉን ወደ አዲስ አበባ መላካቸዉ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ልምዳቸዉ ከሳልቫ ኪር የተሻለ መሻሉን ጠቋሚ መስሎ ነበር።አል-በሽር ልዩ መልዕክተኛቸዉን ወደ አዲስ አበባ ከሸኙ በሕዋላ ግን መከላከያ ሚንስራቸዉ አብድልረሒም ሙሐመድ ሙስጠፋ ያስረቀቁትን የዉጊያ ዕቅድ ነበር ያፀደቁት።

መከላከያ ሚንስትሩ ሒጂሊጅ አካባቢ የሠፈረዉን ጦር አዛዦች ሰብስበዉ የዉጊያ ንድፉን ሲያስረዱ ደግሞ አል-በሽር የፓርቲያቸዉን ወጣት አባላት ካርቱም ዉስጥ ሰብስበዉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብን ሳል ቫኪር ከሚመሩት ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ ወይም ጦር አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት እንደሚፋለሙ ይዝቱ ገቡ።
                 
«ዛሬ አባት ሐገራችንን እና የደቡብ ሕዝባችንን ከሕዝባዊዉ ንቅናቄ ነፃ እናወጣለን።ሐላፊነት አለብን።ሐላፊነቱ ደግሞ የሥነ-መርሕ ሐላፊነት ነዉ።ለደቡብ ሱዳን ሕዝባችን የምናስተላልፈዉ መልዕክት ንቅናቄዉ ሥልጣን እንዲይዝ በመፈቀዳችን የፈፀምነዉን ስሕተት እናስተካክለን የሚል ነዉ።»

ሰላምና ጦርነት።ሱዳን።ጥንት እንዲያነበረች።ድሮም።የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ጦር ወይም ንቅናቄ መሪ ዶክተር ኮሎኔል ጆንጋራንድ የዛሬ ስድስት አመት እንደ መሠከረቱ ያቺ ሰፊ፥ ጥንታዊት አፍሪቃዊት ሐገር ከጦርነት የተለየ ታሪክ የላትም።
                 
«ሐገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዉጪ ሐይላት ተወራ ለባሪያ ፍንገላና ለመሰል የበዝበዛ ንግዶች ከተጋለጠችበት ከ1821 ጀምሮ በጦርነት እንደ ተመሰቃቀለች ነዉ።ከ1955ቱ የነፃነት ዋዜማ ጀምሮ ደግሞ ከርስ በርስ ጦርነት አልተላቀቀችም።»

ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት አል-በሽር ወደ አዲስ አባባ-የላኳቸዉን የሰላም መልዕክተኛቸዉን ተልዕኮ ዉጤት ሲያዳምጡ ሒጅሊጅ ያዘመቱት ጦር በተነደፈለት ዕቅድ መሠረት የደቡብ ጠላቱን ካየር-ከምድ ይወቅጠዉ ገባ።ዘንድሮም-ጦርነት።

ጦሯቸዉን በሰላም ከሒጂሊጅ እንዲያስወጡ የፓን ጊ ሙንን አስተያየት፣ የአፍሪቃ ሕብረትን ማስጠንቀቂያ ፣የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ምክር፣ የአዉሮጳ ሕብረትን ጥቆማ «አታዙኝም» እያሉ ያጣጠሉት ሳል ቫኪር ለሰሜኖቹ ዱላ ደም ሕይወት ገብረዉ ሒጅሊጅን በማረኩ በአስረኛዉ ቀን ለጠላቶቻቸዉ አስረከቡ።አርብ።ጥር 9 2005  ከናይሮቢዉ ትልቅ አዳራሽ የታደሙት የአፍሪቃ ታላላቅ መሪዎች በሙሉ፣ ከተቀረዉ ዓለም ምርጥ ዲፕሎማቶች አብዛኞቹ ከአስራ አራት አመት በፊት ሞቃዲሾና ሐርጌሳ፣ አዲስ አበባና አስመራ ላይ የሆነና የተባለዉን ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።

ሶማሊያን የልቂት-ፍጅት የጥፋት-ዉድመት ጉዞን ከቅርብም ከሩቅም አይተዉታል።የአዲስ አበባ እና አስመራ ላይ ሁለት መንግሥት ሲቆም የተገባዉ ቃል፣ተስፋ በሰባተኛ አመቱ በደም ጎርፍ መታጠቡን ልቅም አርገዉ ያዉቁታል።አንዳዶቹማ የተፈፀመዉ አድራጊ፣ ይደረጋል ተብሎ የነበረዉ ቃል-ተስፋ ሰጪዎች፥ ገሚሶቹ የአድራጊ-ተናጋሪዎቹ ደጋፊ፣ ጥቂቶቹ አስደራጊ፣አናጋሪዎችም ነበሩ-ናቸዉም።

የዚያን ቀን እዚያ ትልቅ አዳራሽ ሥለ ሱዳን የተፈረመና የተነገረዉ አጓጉል እንዳይባርቅ ከሶማሊያ፣ ከኢትዮ ኤርትራ ዉድቀት-ጥፋት የቀረበ አስተምሕሮት በርግጥ ሊኖር አይችልም ነበር። ፈራራሚ፥ አፈራራሚ፥ ታዛቢዎችም ካለፈዉ የመማርን ብልሐት ጥንቃቄን ከመምከር-መናገር ይልቅ ዉል-ቃሉ የትልቂቱ አፍሪቃዊት ሐገርን የዘመነ-ዘመናት የግጭት ጦርነት መንስኤን ነቅሎ ይጥላል-አሉ።ወይም አስባሉ።
               
«እንኳን ደስ አላችሁ።ደስታም በናንተ ላይ ይሁን።ንቅናቄያችሁ SPLM/ SPLA እና የብሔራዊ ምክር ቤት መንግሥት አጠቃላይ የሰላም ሥምምነት አቅርበዉላችኋል።ዛሬ የፈረምነዉና ሁላችሁም ያያችሁትን ፍትሐዊና የተከበረ ሠላም-አቅርበዉላችኋል።በዚሕ የሠላም ስምምነት መሠረት በአፍሪቃ ረጅሙን ጦርነት አቆምን።-ከነሐሴ 1955ጀምሮ ሰላሳ-ዘጠኝ ዓመታት ያስቆጠሩትን ሁለት ጦርነቶች። በዚሕ የሠላም ስምምነት መሠረት ከእንግዲሕ በየዋሕ ሕፃናትና ሴቶች ላይ ከሰማይ የሚወርድ ቦምብ የለም።»

ዶክተር ኮሎኔል ጆን ጋራንግ።እሳቸዉ ዛሬ በርግጥ የሉም።ጥይት ቦምቡ ግን ደቡብም-ሰሜንም፥ ምዕራብም ሱዳን ከሰማይም-ከምድርም ይዘንባል።የዋሕ ሕፃናት፥ሴቶች፥ አዛዉንቶችም ይሞታሉ፥ ይቆስላሉ፥ ይሰደዳሉም።ዳርፉር፥ ኮርዶፋን፥ ደቡብ ሱዳን በቀጠለዉ ዉጊያ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች መተዋል፥ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል ወይም ተሰደዋል።ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአንዲት አካካቢ ሒጂሊጅ በሁለቱ መንግሥታት ጦር መካከል በተደረገዉ ጦርነት ብቻ ከአምስት መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።

               
«ይሕ የሰላም ስምምነት ሱዳንን ለዘላለም ይቀይራታል።ሱዳን ከእንግዲሕ እንደከዚሕ ቀደሙ አትሆንም፥ መሆን አትችልምም።»

የጋራንግን ንግግር አል-በሽር በሌላ አባባል ደግመዉታል።ከኬንያ እስከ ሩዋንዳ፥ ከኢትዮጵያ እስከ ግብፅ፥ ከኤርትራ እስከ ዩጋንዳ፥ በዚያ አዳራሽ የተሰበሰቡ መሪዎችና ተወካዮች አድንቀዉታል።የዋሽግተን፥ የለንደን፥ መንግሥታት፥ የኒዮርክ-ብራስልስ ዲፕሎማቶች ደግፈዉታል።እና ሱዳን በርግጥ ተለዉጣለች።ሁለት ሆናለች።

የሶማሌ ፖለቲከኞች ሞቃዲሾና ሐርጌሳ ላይ፥ የኢትዮ-ኤርትራ ፖለቲከኞች አዲስ አበባና አስመራ ላይ ሁለት መንግሥት ማቆማቸዉ ለየሕዝባቸዉ ሰላም እንዳልተከረ ሁሉ አንድነቱም ሁለትነቱም፥ የሰላም ድርድር ዉሉም በጦርነት የኖረችዉን ሱዳንን ከጦርነት አለማላቀቁ ነዉ ቁጭቱ።አቶ ብሩክ እንደሚሉት ሱዳን እሁለት ከተከፈለችም በሕዋላ፥ ሱዳኖች የሰላም-ስምምነቱን እያፈረሱ፥ ድርድራቸዉን እያቋረጡ የመዋጋት-መጋጨታቸዉ ሰበብ ብዙ ነዉ።ዋናዉ ግን -ሐብት።
             
የሁለት ሺሕ አምስቱ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ችግር የሚባሉ ጉዳዮችን መነካካቱ አልቀረም። እንደየትኛዉም ስምምነት ሁሉ የተነካካቱን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት እቅም እንደሌለዉ ግን ያኔም-ይታወቅ ነበር።ከሁሉም በላይ ሱዳንን ለሰላሳ ዘጠኝ አመታት ያነደደዉ ጦርነት ከሱዳኖች እኩል በሐያሉ ዓለም የጥቅም ግጭት፥ በአካባቢዉ ሐገራት ተቋራኒ ፍላጎት የሚዘወር መሆኑን ፈራሚ አፈራራሚዎች አላጡትም።


ጦርነቱን ለማስቆም የተደረገዉም ስምምነት ገቢራዊ ሊሆን የሚችለዉ በጦርነቱ ዘዋሪዎች ሙሉ ፍቃድና ፍላጎት መሆኑ ግልፅ ነበር።የስምምነቱ ልክ፥ የገቢራዊነቱ መሠረት እየታወቀ ያኔ-እንደ ሙሉ በኩልሔ መታየቱ፥ ተስማሚ-አስማማዎች ሕዝብን ማስደነስ ማስቦረቃቸዉ ነዉ-ጉዱ። ከሱዳን-ጎረቤቶች ስሕተት ያለመማርቸዉ ጥፋት።
                  

ሁለቱ መንግሥት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ወይም ወደ ያቋረጡትን ድርድር እንዲቀጥሉ ከየአቅጣጫዉ የሚደረግላቸዉ ጥሪ-ምክር እንደቀጠለ ነዉ።የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች ግን አሁንም ለዉጊያ እየዛቱ ነዉ።ከዋሽንግተን-እስከ ኬንያ፥ ከኒዮርክ እስከ አዲስ አበባ፥ከካይሮ እስከ ብራስልስ፥ ያሉ መንግሥታትና ማሕበራት ሱዳኖች ለሰላም እንዲገዙ ሲጠይቁ ዩጋንዳ ግን የጁባ መሪዎችን ዛቻ ፉከራ ታዳምቅ ይዛለች።

የፕሬዝዳት ሙሳ ቬኒ መንግሥት ከከሱዳን እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፥ ከሩዋንዳ እስከ ሶማሊያ በነበረና ባለዉ የርስ በርስ ጦርነት እጁን እንደ ዶለ ነዉ።የሐገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አሮንዳ ንያካሪማ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ሁለቱ ሱዳኖች ሲዋጉ ዩጋንዳ ከደቡብ ጎረቤቷ ጎን ተሰልፋ ሰሜንን ትወጋለች እንጂ ዝም ብላ አትቀመጥም።

የዩጋንዳ ዛቻ በርግጥ «የምን ገላጋይ---» ከማሰኘት አላለፈም።ግን የሱዳኑ ጦርነት ትናንትም ሆነ ዛሬ የሱዳኖች ብቻ እንዳልሆነ ጥሩ ማረጋገጪያ ነዉ።የዩጋንዳዉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በሰሜን ሱዳን ላይ ጦርነት እንደሚያዉጁ ያስታወቁት ኢትዮጵያ ሱዳኖችን እንድታግባባ ሰሜን ሱዳን መጠየቋ በተነገረ ማግስት ነዉ።የኢትዮጵያ መልስ፥ እና አቋም እስካሁን በግልፅ አልተነገረም።

አቶ ብሩክ እንደሚሉት ግን ጦርነቱ ከቀጠለ የሚጎዱት ሱዳኖች ብቻ አይደሉም።የአካባቢዉ ሐገራት  በጣሙን ኢትዮጵያ ጭምር እንጂ።በዚሕም ምክንያት ኢትዮጵያ ሁለቱን ሱዳኖች ለመሸምገል ብትጥር ተገቢ  ነዉ።ይጠበቅባታልም።
             
ግን እንዴት? የዩናይትድ ስቴትሱ የነዳጅ ኩባንያ ቼቭሮን በ1981 የመጀመሪያዉ የሱዳን ነዳጅ ዘይት ናሙና ሲያመርት ከጥጥ፥ ሒና ምርት በስተቀር ድሕነት የሚያናጥርባት ሐገር የብልፅግና እድገቷ በር ተከፈተ አሰኝቶ ነበር።በርግጥም ሱዳን ነዳጅ ዘይት ወደ ዉጪ መላክ ከጀመረችበት ከሁለት ሺሕ ጀምሮ የድሕነትን ማቅ ካናቷ፥ ወደ ደረቷ ዝቅ ማድረግ ችላ ነበር።ሐብቷ, ጠላቷ ለመሆን ግን ብዙ አልቆየም።ሁለት የመከፈሏ ጉዞ ይጣደፍ፥ የዳርፉር ጦርነት፥ የቤጃ ጦርነት፥ይጋጋም ገባ።ነጋሽ መሀመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

epa03088900 A handoud picture released by the United Nations Missions in South Sudan (UNMSS), shows President of South Sudan Salva Kiir speaking during a press conference in Juba, South Sudan, 02 February 2012. Kiir said South Sudan is rejecting African Union (AU) high implementation Panel proposal. 'the proposal would bind us to dependency on Sudan's infrastructure' he added. EPA/ISAAC BILLY/HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++
ኪርምስል picture-alliance/dpa
Sudanese President Omar Hassan al-Bashir waves to supporters after receiving victory greetings at the Defence Ministry, in Khartoum April 20, 2012. South Sudan said on Friday it would withdraw its troops from the disputed Heglig oil region more than a week after seizing it from Sudan, pulling the countries back from the brink of a full-blown war. Sudan quickly declared victory, saying its armed forces had "liberated" the area by force as thousands of people poured onto the streets of Khartoum cheering, dancing, honking car horns and waving flags. REUTERS/ Mohamed Nureldin Abdallah (SUDAN - Tags: MILITARY CONFLICT POLITICS) Generalleutnant Umar Hasan Ahmad al-Baschir (arabisch ‏عمر حسن أحمد البشير‎, DMG ʿUmar Ḥasan Aḥmad al-Bašīr; * 1. Januar 1944 in Hosh Bannaga bei Schandi, Sudan) ist der Staatspräsident des Sudan, der 1989 nach einem unblutigen Militärputsch an die Macht kam und das Land nach einer islamisch-fundamentalistischen Haltung regiert. Seit 1993 ist al-Baschir Staatspräsident.
አል-በሽርምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ