1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 11 2001

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ በዚህ ሣምንትም አስደናቂ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ቀስ በቀስ እያገገመ ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ሊይዝ በቅቷል።

https://p.dw.com/p/GbUS
የዓለም የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና 2009 መለያ አርማ
የዓለም የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና 2009 መለያ አርማምስል picture-alliance/ dpa

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ወሣኝ ግጥሚያዎች ዘግይተው በገቡ ጎሎች መወሰናቸው መለያው የሆነበት ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ ቦልተን ወንደረርስን በዘጠናኛዋ ደቂቃ ላይ በቡልጋሪያው ኮከብ በዲሚታር ቤርባቶቭ አማካይነት ባስቆጠራት ብችኛ ጎል 1-0 በመርታት ነው በውድድሩ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀደምቱን ቦታ ሊይዝ የቻለው። ማንቼስተር ዩናይትድ በወቅቱ በ 21 ግጥሚያዎች 47 ነጥቦችን በማሰባሰብ በአንዲት ነጥብ ልዩነት የሚመራ ሲሆን ሊቨርፑል ነገ ኤቨርተንን ካሸነፈ ግን ለጊዜውም ቢሆን ወደ ሁለተኛው ቦታ መመለሱ የማይቀር ነው። ቢሆንም አንድ ጨዋታ ስለሚጎለው እንደገና ቁንጮ የመሆን ዕድል አለው።

ሌላው ቀደምት ክለብ ኤፍ.ሢ.ቸልሢይ ስቶክ-ሢቲይን ትግል በተመላው ግጥሚያ ዘግይቶ በ 88ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ወሣኝ ግብ 2-1 በማሸነፍ በ 45 ነጥቦች በሶሥተኝነቱ ቦታ ተቆናጧል። ለቼልሢይ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ጁሊያኖ ቤሌቲና የቡድኑ መንኮራኩር ፍራንክ ላምፓርድ ነበሩ። ኤስተን ቪላና አርሰናል ለንደን ደግሞ የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች በማሸነፍ አራተኛና አምሥተኛ ሆነው ይከተላሉ። ሊጋውን በጎል አግቢነት ቀደምት ሆኖ የሚመራው 14 ያስቆጠረው የቸልሢው ኒኮላስ አኔልካ ነው። በተረፈ ባለፈው ረቡዕ የእንግሊዝ እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫ ግጥሚያ ቆስሎ የነበረው የቸልሢው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ጆው ኮል የተሳሣ የቀዶ ጥገና ሕክምና ቢደረግለትም በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለመሳተፍ እንደማይችል ክለቡ ገልጿል። ለቸልሢይ ቀዳዳውን መሽፈኑ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በዚህ ሰንበትም ኤፍ.ሢ.ባርሤሎናን ከግስጋሤው ለማቆም የቻለ አልተገኘም። ባርሣ በዓለምአቀፍ ከዋክብቱ አማካይነት ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛን 5-0 ቀጥቶ ሲሽኝ የሊጋ አመራሩን ወደ 12 ነጥቦች ከፍ ለማድረግ ችሏል። የባርሤሎና ድል ዋስትና የሆኑት በተለይ ክለቡ ከውጭ የገዛቸው ተጫዋቾቹ ነበሩ። ፈረንሣዊው ቲየር ሄንሪና የካሜሩኑ ሣሙዔል ኤቶ እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥሩ አንዷን ግብ አስደናቂ በሆነ አጨዋወት እንደተለመደው ለብቻው አልፎ ያገባው ደግሞ አርጄንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነው። ሬያል ማድሪድ ኦሣሱናን 3-1 በማሸነፍ በአራተኛ ተከታታይ ድሉ በሁለተኝነቱ ሲቆናጠጥ ሶሥተኛው ሤቪያ ነው። በተቀረ ቢልባኦ-ቫሌንሢያን 3-2፤ ማላጋ-ኤስፓኞልን 4-0፤ እንዲሁም ቪላርሬያል-ማዮርካን 2-0 ሲያሸንፉ፤ አልሜይራና-አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ አቻ-ለአቻ፤ 1-1 ተለያይተዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ.አ. ሻምፒዮኑ ኢንተር ሚላን በአታላንታ በመሽነፉ ቀደም ሲል የነበረ አመራሩ ወደ ሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሏል። ጁቬንቱስ ከላሢዮ እኩል-ለእኩል በሆነ ውጤት ባይወሰን ኖሮ አመራሩ እንዲያውም ወደ አንዲት ነጥብ ባቆለቆለ ነበር። ፊዮሬንቲናን 1-0 የረታው ኤ.ሢ.ሚላን በአንጻሩ የሣምንቱ ተጠቃሚ ነበር። ከሰንበቱ አጠቃላይ ውጤት በኋላ ኢንተር፣ ጁቬንቱስና ኤ.ሢ.ሚላን በስሥት ነጥቦች ክልል ውስጥ የሊጋው ቀደምቶች ናቸው። በተረፈ ጌኖዋ-ሌቼ 2-0፤ ቬሮና-ናፖሊ 2-1፤ ፓሌርሞ-ሣምፕዶሪያ 2-0፤ ቦሎኛና-ካታኛ ደግሞ 2-1 ተለያይተዋል። ጌኖዋ በአራተኛው ቦታ ሲቆናጠጥ፤ አምሥተኛ ናፖሊ፤ እንዲሁም ፊዮሬንቲና ስድሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት የቦሎኛው ማርኮ-ዲ-ቫኢዮ 14 አስቆጥሮ ይመራል።

የኢጣሊያን እግር ኳስ ተመልካቾች፤ በተለይም የኤ.ሢ.ሚላንን ደጋፊዎች ሣምንቱን ወጥሮ የያዘው እርግጥ የሰንበቱ ውድድር ብቻ አልነበረም። የብራዚሉ ኮከብ ካካ ምናልባትም ከመቶ ሚሊዮን ኤውሮ በሚበልጥ ገንዘብ ለእንግሊዙ ክለብ ለማንቼስተር ሢቲይ ሊሸጥ መቻሉ ብዙዎችን አልተዋጠላቸውም። ክለቡ በዚህ ግዙፍ ገንዘብ መማረኩ ባይቀርም የሚላን ደጋፊዎች ግን ሰንበቱን “ካካን አትሽጡ”፤ ካካ በገንዘብ የሚለካ አይደለም”፤ ካካን ለቀቅ አድርጉ” የሚሉ መፈክሮችን በማንሣት ድንቁ ብራዚላዊ ኮከብ በኢጣሊያ እንዲቆይ ሲጮሁ ነው ሰንበቱን ያሳለፉት። ፍላጎታቸው መሣካቱ ግን በወቅቱ በጣሙን የሚያጠራጥር ነው። በነገራችን ላይ ክለቡ ካካን በጊዜው የገዛው በስምንት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሣምንቱ ቢቀር በአመራሩ ላይ ለውጥ አላስከተለም። ኦላምፒክ ሊዮን-ግሬኖብልን 2-0፤ ዢሮንዲንስ ቦርዶም-ናንትን 2-1 በማሽነፍ በአንዲት ነጥብ ልዩነት ተከታትለው መምራታቸውን ቀጥለዋል። ከሊዮን አራት ነጥቦች ወረድ በማለት ሶሥተኛው ሌ-ሃብርን 2-0 የረታው ኦላምፒክ ማርሤይ ነው። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ደግሞ አልክማር ተከታታይ ሰባተኛ ድሉን በማረጋገጥ በ 44 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል። አያክስ አምስተርዳም-ኒሜገንን 4-2 ሲረታ ሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ትዌንቴ ኤንሼዴ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል፤ አይንድሆፈን ከሮዳ ኬርክራደ እኩል-ለእኩል በመለያየቱ ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ለማለት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች ሻምፒዮና ሂደት ከሞላ ጎደል ይህን የመሰለ ነው።

አትሌቲክስ!

ለኢትዮጵያውያን የሣምንቱ ታላቅ የአትሌቲክስ ዜና በዱባይ ማራቶን የተገኘው ድርብ ድል ነበር። በወንዶች ማራቶን ሃይሌ ገ/ሥላሤ አዲስ ክብረ-ወሰን ባያስመዘግብም ግሩም በሆነ 2 ሰዓት፤ ከ 5 ደቂቃ ከ 29 ሤኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። ሃይሌ የራሱን የዓለም ክብረ-ወሰን በማሻሻል አንድ ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የነበረው ዕድል ቢያመልጠውም 250 ሺህ ዶላር ተሽልሟል። በሴቶችም ብዙነሽ በቀለ አሸናፊ ሆናለች።

ትናንት ሕንድ-ሙምባይ ላይ ተካሂዶ በነበረ የማራቶን ሩጫ ደግሞ የኬንያው ተወላጅ ኬኔት ሙጋራ አሸናፊ ሆኗል። ኬኔት ሩጫውን ከሁለት ሰዓት፤ 11 ደቂቃ በላይ በሆነ ጊዜ ሲፈጽም ይህ እርግጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚደነቅ ውጤት አልነበረም። ሁለተኛ ዴቪድ ቱሩስ፤ ሶሥተኛ ጆን ኬላይ ሁሉም ከኬንያ! በሙምባይ ማራቶን እንደ ዱባይ ሁሉ የሴቶች ድል የኢትዮጵያ ነበር። ከበቡሽ ሃይሌ አሸንፋለች። ማርታ ማርቆስ ሁለተኛ ስትወጣ ሶሥተኛ የሆነችው ኬንያዊቱ ኢሬነ ሞጋካ ናት።

ሂዩስተን-ቴክሣስ ውስጥ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ የኤርትራው ተወላጅ አሜሪካዊ መብራቱ ክፍለዝጊ በአንድ ሰዓት፤ ከአንድ ደቂቃ፤ ከ 25 ሤኮንድ አሸናፊ ሆኗል። ክፍለዝጊ ባለፈው የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ማጣሪያውን ማለፍ አቅቶት ሳይወዳደር መቅረቱ ይታወቃል።

የዕጅ ኳስ!

ክሮኤሺያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የዓለም የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና የእግር ኳስን ያህል አይሁን እንጂ በተለይ በዚህ በአውሮፓ ሰፊ የቴሌቪዥን ተመልካቾችን ስቦ እንደቀጠለ ነው። በአራት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ማጣሪያ ትናንት ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል።
ስሎቫኪያ-አውስትራሊያ 47-12
ፈረንሣይ-አርጄንቲና 33-26
ስፓኝ-ኩባ 45-20
አስተናጋጇ ክሮኤሺያ-ኩዌይት 40-21
ፖላንድ-ሩሢያ 24-22
ጀርመን-ቱኒዚያ 26-24 እንዲሁም
ኖርዌይ-ብራዚል 39-21
ዴንማርክ-ሰርቢያ 37-36 ተለያይተዋል።
ውድድሩ ዛሬ ማምሻውን በሶሥተኛ የምድብ ግጥሚያዎች የሚቀጥል ሲሆን ጀርመን ከአልጄሪያ የምታደርገው ጨዋታ አንዱ ነው።

ከዚሁ ሌላ ሜልበርን ላይ በተከፈተው የአውስትራሊያን-ኦፕን የቴኒስ ውድድር በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ የሆነችው ሰርቢያዊት የለና ያንኮቪች የአውስትሪያ ተጋጣሚዋን ኢቮን ሞይስቡርገርን በለየለት ጥንካሬ 6-1, 6-3 በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር እንደተጠበቀው አልፋለች። በወንዶችም ያለፈው ዓመት ሻምፒዮንና ሌላው የባልካን ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች የኢጣሊያ ተጋጣሚውን አንድሬያ ስቶፒኒን በሶሥት ምድብ ጨዋታ አሸንፏል። የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን በስኬት በመወጣት ወደ ተከታዩ ዙር ካለፉት መካከል አሜሪካዊው ኤንዲይ ሮዲክ፤ የስፓኙ ዴቪድ ፌሬርና የአርጄንቲናው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮም ይገኙበታል።