ሩሲያ እና የዓለም ዋንጫ ዝግጅት

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:13 ደቂቃ
13.06.2018

እግር ኳስ አፍቃሪው ኅብረተሰብ

21ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ነገ ሩሲያ ላይ ይጀመራል። በጨዋታው ለመሳተፍ ማጣሪያዎቹን አልፈው የተዘጋጁት የ32 ሃገራት ቡድኖች በ11 የሩሲያ ከተሞች በሚገኙ 12 ስታዲየሞች 64 ግጥሚያዎችን ያካሂዳሉ። የመላው ዓለምን ቀልብ የሳበው ሩሲያ የምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ከነገ ሐሙስ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010ዓ,ም ድረስ ይካሄዳል።

ዝናብ እየወረደ ቢሆንን ፌዲኖ በተባለችው የሩሲያ መንደር የሚገኝ የእግር ኳስ ቡድን ከሌላ አካባቢ ቡድን ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ ለመመልከት ሰዎች ተሰባስበዋል። ጨዋታውን የሚመለከቱት የመንደሯ ነዋሪዎች ጃንጥላ እና በእረፍት ሰዓት ሰዎች የሚመገቡትን ዝነኛ የሩሲያ የሱፍ ቆሎ በእጃቸው ይዘዋል። ከተመልካቾች አንዳንዶቹ ጨዋታው እየተሟሟቀ ሲሄድ ለተጋጣሚዎቹ ሊያደርጉ ይገባል ያሉትን ትዕዛዝ ጮክ ብለው ያስተላልፋሉ። 

«እግር ኳስ ሕይወታችን ነው። 43 ዓመቴ ቢሆንም ቡድኑ ወጣትነት እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ምክንያቱም ይህ ቡድን ቤተሰቤ ማለት ነው፤ ጨዋታው እንዴትም ቢጠናቀቅ የሚያመጣው ነገር የለም። ስለሚያስደስተኝ አብሬያቸው እጫወታለሁ።»

ይላል የቡድኑ ካፒቴን ቭላድሚር ሙራሾቭ። ፌዲኖ መንደር የተወለደው ቭላድሚር ገና ከጉርምስና ዕድሜው ጀምሮ የመንደሩ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ነው። መንደሯ በሆኪ ስፖርት የታወቀች እና ለዚህም የሚያመች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ቢኖራትም ኗሪዎቿ ግን ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ያመዝናል። የመንደር ቡድኖቹን ጨዋታ የሚመለከቱት ሁሉ ሀገራቸው የምታስተናግደውን የዓለም ዋንጫ በማሰብ ከወዲሁ ተደስተዋል። ሩሲያ ለዘንድሮዉ የዓለም ዋንጫ የገድ ተምሳሌት ያደረገችውን «ዛቢፍካ » የተሰኘ ምስል ያለበት ቲሸርት የለበሰ አዳጊ ልጃቸውን ያስከተሉ አንዲት እናት የኅብረተሰቡን ስሜት እንዲህ ይገልጻሉ። «እንግዶችን ለመቀበል እየተጠባበቅን ነው። ሩሲያ ያለምንም ጥርጥር ልታሳይ የምትችለው ነገር አላት።»

ዛቢፍካ ማለት ትንሿ ግብ ጠባቂ እንደማለት ነው በሩሲያኛ። በሀገሪቱ የሚካሄደውን የዓለም የእግር ኳስ የዋንጫ ውድድር ማየት እንደሚመኝ የሚናገረው ልጃቸው ግን ይህ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ለአካባቢው የሚያወጣው ነገር መኖሩን ይጠራጠራል። ፌዲኖ ከሞስኮ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መንደር ናት። ለዓለም ዋንጫ ዉድድር ዋና ከተማ ሞስኮ ፀድታለች። መንገዶቿ ተጠግነዋል። ህንፃዎች፣ አጥሮች እና የባቡር ጣቢያዎች በወጉ ታድሰዋል። ባለስልጣናት እንደሚሉት በዋና ከተማ እንዲህ ያሉትን ተግባራት ለማከናወን እና ጨዋታ ከሚካሄድባቸው ከተሞች ጋር ሞስኮን ለሚያገኛኝ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት 150 ቢሊየን ሩብል ማለትም ከ2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ፈስሷል። ባጠቃላይ ለዝግጅቱም 683 ቢሊየን ሩብል ወይም ከ9 እስከ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መውጣቱን  የጨዋታው ዝግጅት ኮሚቴ አስታውቋል። ፌዲኖ መንደርም ከዓለም ዋንጫው በረከት የመሠረተ ልማቷ በተለይም ለስፖርቱ ዘርፍ ይደርሰኛል በሚል ተስፋ እየጠበቀች ነው።

Fußball WM Team Russland Training

ለዚህ ደግሞ መነሻ አላት። በአቅራቢያዋ በምትገኘው ቮስከርሲንክ ከተማ አዲስ ስታዲዮም ወይም የመለማመጃ ስፍራ እንደሚገነባ ተወርቷል። ቭላድሚር ግን ከተማዋ ያላት አሮጌ ጅምናዚየም በመሆኑ አዲስ ቢገነባላት ይመርጣል። ያም ቢሆን ከዓለም ዋንጫው የሚገኝ ትርፍ ካለ የሚታየው ከውድድሩ በኋላ እንደሚሆን ገምቷል። አሁን ግን ትኩረቱ ሁሉ በዓለም ዋንጫ ላይ ሆኗል። እሱና መሰሎቹ ትኬት ቆርጠው ስታዲየም በመግባት ጨዋታውን ለመከታተል በጣም ውድ በመሆኑ አቅማቸው አይፈቅድም።

«ይህ በእርግጥ ያናድዳል። ቢያንስ አንድ ጨዋታ እንኳ ማየት ብንችል ግሩም ነበር። ምናልባት ይህም አይቻልም ይሆናል። ሁላችንም በቲቪ እንከታተላለን። ሚስቶቻችን ከወዲሁ ተናድደዋል። ምክንያቱም አንድ ወር ሙሉ ቴሌቪዥን ስናይ መክረማችን እንደሆነ ያውቃሉ።»

የፌዲኖ ከተማን ስታዲየም የሚያስተዳድረው አካል ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎችን ኳስ አፍቃሪዎቹ እንዲመለከቱ ከልብስ መለወጫው አጠገብ ወንበሮች እና ፕሮጀክተር ከወዲሁ አስተካክሏል። እዚህ ስፍራ የሚሰበሰቡት ተመልካቾች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከመንደሯ ነዋሪዎች አንዲቱ ያውቃሉ። «በጣም ከመጮሃቸው የተነሳ ቤት ውስጥ ሆኖ እንኳ ይሰማሉ። ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ ቤት ስለምንሆን፤ ወንዶቹ ሲጮኹ እንሰማለን፤ እናም ደስ ይለናል።»

ነገ ሩሲያ እና ሳዑድ አረቢያ በሞስኮ ሉዜኒክ ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ የ2018 የዓለም ዋንጫ ይከፈታል። በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ጁላይ 15 ለዋንጫ የሚደርሱት ተጋጣሚዎች በዚሁ ስታዲየም የፍፃሜውን ግጥሚያ ያደርጋሉ።

ሸዋዬ ለገሠ / ኤሚሊ ሻርዊን

ነጋሽ መሐመድ
 

ተዛማጅ ዘገባዎች