1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩስያና መፃኢው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

ረቡዕ፣ የካቲት 21 2004

ሩስያ ውስጥ የፊታችን እሁድ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በምርጫው በተወዳዳሪነት የሚቀርቡት ዕጩዎች ስም ከአምስት ሣምንታት በፊት ቢታወቅም፡ አንዱም ባለፉት አራት ዓመታት በጠቅላይ ሚንስትርነት ላገለገሉትና አሁን የተባበረች ሩስያ ፓርቲ ወክለው ለሚወዳደሩት ቭላዲሚር ፑቲን ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ታዛቢዎች አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/14C6E
ምስል picture-alliance/dpa

ይሁንና፡ ዬጎር ቪኖግራዶቭ እንደዘገበው፡ በወቅቱ ብዙዎች የሚያነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚንስትር ፑቲን ያሻንፋሉ የሚለው ሳይሆን ይህንኑ ከወዲሁ የተረጋገጠውን ድላቸውን በመቃወም አደባባይ የሚወጡት ሩስያውያን ቁጥር ስንት ይሆናል የሚለው ነው። አርያም ተክሌ
ከፑቲን ጎን በተወዳዳሪነት ከቀረቡት መካከል ብዙዎቹ ካሁን በፊትም ከፍተኛውን የሀገሪቱን ሥልጣን ለመያዝ የሞከሩና ፓርቲዎቻቸው ከብዙ ዓመታት ወዲህ በሩስያ ምክር ቤት የተወከሉ የቀድሞ ፖለቲከኞች ናቸው። የቀኝ አክራሪው ሊበራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ቭላዲሚር ሽሪኖቭስኪ፡ እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ ከመንግሥቱ ፓርቲ ጋ ቅርበት እንደነበረው የሚነገርለት የፍትሓዊት ሩስያ ፓርቲ ተወካይ ሴርጌይ ሚሮኖቭ፡ የኮሚንስቱ ፓርቲ መሪ ጌናዲ ሱጋኖቭ ይገኙባቸዋል። ለፑቲን ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የነበሩት ተሀድሶ ለውጥ አራማጁ ፓርቲ መሥራች ግሬጎሪ ያቭሊንስኪ በቂ የደጋፊዎች ድምፅ አላሰባሰቡም በሚል አስመራጩ ኮሚሽን ዕጩነታቸውን ሰርዞዋል። ይህንን የኮሚሽኑን ውሳኔ ብዙ ሩስያውያን ታዛቢዎች ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳለው ይገምታሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት ነጻ ተወዳዳሪ እንደሆኑ የሚናገሩት ቢልየኔሩ ባለተቋም ሚኻየል ፕሮኾሮቭ ብቻ ናቸው። እኒሁ ነፃ ተወዳዳሪነታቸውን የሩስያ መንግሥት የተጠራጠረባቸው ፕሮኾሮቭ በምርጫው የመካከለኛውን መደብ፡ የያቭሊንስኪ ደጋፊዎችንም ድምፅ ጭምር ለማግኘት እየሞከሩ ነው።
ሌቫንዳ ሴንተር የተባለ ድርጅት ከጥቂት ሣምንታት በፊት ያወጣው የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ውጤት እንዳሳየው፡ ፑቲን በምርጫው ሀምሳ ሰባት ከመቶ የመራጩን ድምፅ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሩስያን እንደሚያሳድጉና ወደመጪው ዘመንም እንደሚያራምዱ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ባሰሙት የመጨረሻ ንግግራቸው ያስታወቁት ፑቲን እንደሚያሸንፉ ለደጋፊዎቻቸው ገልጸዋል።
« የራሳችን ፍላጎትና ጥቅም ስላለን ማንም ከውጭ መጥቶ የሱን ፍላጎት እንዲጭንብን ዕድል አንሰጥ። ድል አድራጊ ሕዝብ ነን። ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ የመጣ በደማችን ውስጥ ያለ ባህርያችን ነው። እና አሁንም እናሸንፋለን። እናሸንፋለን? አዎ። ማንም ወደ ውጭ መመልከት የለበትም፤ እናት ሀገሩንም መክዳት የለበትም። እና ደግሜ ልጠይቃችሁ። ሩስያን እንወዳለን? አዎ። »
ይሁን እንጂ፡ ፑቲን በምርጫው ዘመቻ ወቅት ከተፎካካሪዎቻቸው ጋ ፊት ለፊት ተገናኝተው ክርክር በማካሄድ ፈንታ ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን በጋዜጦችና በአምደ መረብ ማውጣቱን ነው የመረጡት። »
ፑቲንን ሊያሰጋ የሚችለው ትልቁ ተቃውሞ ብዙም ዕእእእድል እንደሌላቸው ከተነገረላቸው ተፎካካሪዎቻቸው ሳይሆን በአንጻራቸው አደባባይ ከሚወጣው ሕዝብ ነው። ፑቲን ምንም እንኳን ከአራት ዓመታት በፊት ሀገሪቱን ለሁለት የሥልጣን ዘመን በፕሬዚደንትነት ቢመሩም አሁን እንደገና በተወዳዳሪነት መቅረባቸው የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ባይጥስም ተቃዋሚዎቻቸው የፑቲን አመራር እንዲያበቃ እየጠየቀ መሆኑን ነው አንዱ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ያሰሙ አንድ ሩስያዊ የገለጹት።
« ሕገ መንግሥቱ ፈቀደ አልፈቀደም አይደለም ጥያቄው። ፑቲን ሥልጣኑን እንደተቆጣጠሩት ነው የሚሰማን። ልክ እንደ ጋዳፊ ሥልጣንን የሙጥኝ ብለው መያዝ ይፈልጋሉ። እርግጥ፡ መሪዎቻችን የሚወስዱት ርምጃ ያስፈራናል። ግን፡ ሕዝቡ ሁኔታው እንዲህ ሊቀጥል እንደማይችል ተረድቶታል። »
ያቭሊንስኪ ከምርጫው በመወገዳቸው ጠቅላይ ሚንስትር ፑቲን በመጀመሪያው ዙር እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። ይሁንና፡ ሁለተኛ ዙር ላይ ከተደረሰ ግን የፑቲን ተፎካካሪ የኮሚንስቱ ፓርቲ መሪ ሱጋኖቭ እንደሚሆኑ ብዙዎች ይገምታሉ።

Demonstration Faire Wahlen Russland
ምስል Vladimir Izotov/DW
Russland Wahlen Präsidentschaftkandidat Michail Prochorow
ምስል picture-alliance/Ria Novosti

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ