1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዋንዳ እና የጎሣ ጭፍጨፋ ተመልካች ባህላዊ ፍርድ ቤቶች

ሰኞ፣ ጥር 9 1997

በርዋንዳ ከተሞችና መንደሮች - የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች፡ ሐቁ ያድናል የሚል ጽሑፍ የሚነበብቸው ትልልቅ ሰሌዳዎች ይነበባሉ። በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተራ ሌቦችና ጋጠወጦችን ክስ ይከታተሉ የነበሩት የሀገር ሽማግሌዎች የሚያካሂዱዋቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አሁን በ 1994 ዓም የተፈፀመውን አሰቃቂውን የጎሣ ጭፍጨፋ ወንጀል በመመልከት ላይ ይገኛሉ። ከሁለት ዓመት የዝግጅት ጊዜ በኋላ ባለፈው ዓርብ ስምንት ሺህ የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን እንደገና ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/E0kX

በርዋንዳ የሩሀንጌሪ ክፍለ ሀገር በሚገኘው በሚኖርበት የካናያምፔሪሪ መንደር አንድ መቶ ሀምሳ ሰዎች በተሰበሰቡበት በአንድ የድንች ተክል ቦታ አንድ የመንደሩ አዛውንት በዚያ በተከፈተው ባህላዊው የጋቻቻ ፍርድ ቤትን በዳኝነት በመምራት የክስ ሰነዶችን እየተመለከተ ብይን ይሰጣል። ገበሬዎች፡ የቤት እመቤቶች፡ አናጢዎች እና የመደብር አሻሻጮች ናቸው በመላ ርዋንዳ በተቋቋሙት የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች በነፍሰ ገዳዮችና ላይ ብይን የሚሰጡት።

የጋቻቻ ፍርድ ቤት በሦስት ለችሎት ባልቀረቡ፡ ግን በዝርፊያና በነፍስ ግድያ ወንጀል አምነው የተቀበሉ ግለሰቦችን ጉዳይ እንደሚመለከቱ ዳኛው ቢያስታውቁምና ምሥክሮችና ተመልካቾች በክሱ ሰነድ ላይ የሚጨምሩት ሀሳብ መኖሩን ቢጠይቁም፡ ጥቂቶችብቻ ናቸው አስተያየታቸውን የሰጡት።
የጋቻቻ የፍትሕ አውታር ዓላማ ዕርቀ ሰላም ለማውረድና የርዋንዳ ኅብረተ ሰብን መልሶ ለመገንባት መሆኑን በሩሄንጌሪ ክፍለ ሀገር ችሎቶችን የሚያስተባብሩት የቀድሞው መምህር ዦን ማሪ ራባሜንየ አስታውቀዋልላባሜንየ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመላ ርዋንዳ እየተዘዋወሩ በርካታ ችሎቶችን በመጎብኘት ተሞክሮ ሰብስበዋል። ልክ እንደ ራባሜንየ በርካታ ችሎቶችን የተመለከቱት አንዲት የመንደሩ ባልቴት የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች የተሳካ ውጤት ማስገኘታቸውን እንደሚጠራጠሩ ሲገልፁ እንዲህ ነበር ያሉት። « በችሎቶቹ ወቅት ሁሌ አዲስ ወቀሳ ይቀርባል። ተከሳሾችን ከእሥር ቤት በመፍታት ፈንታ እዚያው እንዲቆዩ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል። እስካሁን ድረስ አንድም ብይን አልተሰጠም፤ በዳኞች ላይም የማስፈራራት ርምጃ ይወሰዳል፤ ምሥክሮችን ባልታወቀ ሁኔታ ሞተው ይገኛሉ። አለመተማመንና ፍርሀት ተስፋፍቶዋል።» ይህ ችግር መኖሩን ራባምየ ባይክዱም ፍርድ ቤቶቹ የኣካ ውጤት ማስገኘታቸው እንደማይቀር በርግጠኝነት ይናገራሉ። የመጀመሪያው ብይን በሚሰጥበትም ጊዜ መተማመኑ ተመልሶ ይመጣል ብለዋል። የስድሳ ሺህ ተከሳሾች ጉዳይን የሚመለከቱት ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጉት የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሥራቸውን እንደሚያጠናቅቁ ራባሜንየ ተስፋቸውን ከመግለፃቸውም ሌላ፡ አሰቃቂ ወንጀል መፈፀማቸውን አምነው የሚቀበሉና ከቀንደኞቹ የጎሣ ጭፍጨፋ ጠንሳሾች ያልሆኑት ተከሳሾች ከእሥር ቤት እየተለቀቁ ወንጀሉን ወደፈፀሙባቸውና ሰለባዎቻቸው ወደሚኖሩባቸው መንደሮቻቸው እንደሚመለሱም አስረድተዋል። ይህ ግን ለሀገሪቱ ትልቅ ሸክም ቢሆንም ሌላ አማራጭ እንደሌለ የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ አስታውቀዋል።