1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰመጉ በቤንሻንጉልና አጎራባች አካባቢዎች 74 ሰዎች ተገድለዋል አለ

ቅዳሜ፣ መስከረም 26 2011

በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ሰሞኑን በተፈጸመ ጥቃት 74 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ዛሬ አስታወቀ። ከሟቾቹ ውስጥ አስራ ዘጠኙ ፖሊሶች ናቸው ብሏል። 

https://p.dw.com/p/365jL
Äthiopien - Human Rights Council (HRCO)
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

ሰመጉ በቤንሻንጉልና አጎራባች አካባቢዎች 74 ሰዎች ተገድለዋል አለ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ይህን የገለጸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በአጎራባች አካባቢዎች እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ባሳሰበበት መግለጫው ነው።

በአካባቢው ከዚህ ቀደምም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር ያስታወሰው ሰመጉ የሰሞኑ ጥቃት የተቀሰቀሰው አራት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ወረዳ አመራሮች ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ገልጿል። ከአካባቢው የሰበሰበውን መረጃ የጠቀሰው የሰመጉ መግለጫ በካማሺ እና አካባቢው 31 ሰዎች ሲገደሉ፤ በሶጌ፣ በሎ እና አካባቢው ደግሞ 30 ሰዎች በጥቃቱ ህይወታቸውን አጥተዋል። በቤንሻንጉል ክልል አንገር ሜጢ ከተማ ውስጥ 13 ሰዎች መገደላቸውን መግለጫው አክሏል። 

በሰሞኑ ጥቃት የቆሰሉ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን የገለጸው ሰመጉ ተጎጂዎቹ በነቀምቴ እና በወለጋ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታሎች እንደዚሁም በተለያዩ የግል የህክምና ተቋማት እየታከሙ እንዳሉ ጠቁሟል። ከ200 በላይ ቤቶች በተቃጠሉበት በሰሞኑ ጥቃት ወደ 90 ሺህ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው በአጎራባች አካባቢዎች ለመጠለል መገደዳቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ብሔርን መነሻ ባደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች ምክንያት ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከሁለት ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሰመጉ በማስታወስ “ዜጎች በገዛ ሀገራቸው በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትናቸው ጥያቄ ውስጥ ወድቋል” ብሏል። የኢትዮጵያ መንግስት “የዜጎችን በህይወት የመኖር፣ በሀገሪቱ በፈለጉበት አካባቢ ተንቀሳቅሶ ኑሮን የመመስረት እና ንብረት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብቶችን እንዲያስጠብቅ እና እንዲያስከብር” ሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል። 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ