1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሜን አፍሪካ ላይ የሰነበተው ተቃውሞና ላምፔዱሳ

ሰኞ፣ የካቲት 7 2003

ቱኒዚውያን መሪያቸውን ካባረሩ በኋላ እስከአሁን አልተረጋጉም። ወጣቱ በጀልባ ውደ አውሮፓ ስደትን ጀመረ። ላምፔዱሳ ሰሞኑን የሰሜን አፍሪካው አብዮት መዓት ይዞባት መጥቷል።

https://p.dw.com/p/R0ms
ምስል dapd

መንፈሳዊው መጽሀፍ ኢያሪኮ በጩኸት ፈረሰች አለ። ያኔ። ጥንት! ዘንድሮ የቱኒዝና የካይሮ ቤተመንግስታት በጩኸት ፈረሱ። የቱኒዙን የሳምንት የካይሮውን የ18 ቀናት ጩኸት መንግስታቱን ለግብዓተ መሬት ዳረገው።

አትሞ

በእርግጥ የቱኒዚያው የ23 ዓመት የቤን ዓሊ ዘመን ያከተመው ብሶት በወለደው የህዝብ ጩኸት ነው። የ30 ዓመቱ የሆስኒ ሙባረክ ወንበርም የተወገደው በህዝብ ቁጣ ነው። በ18 ቀናት ቁጣ። የፈረንጆቹ 2011 አዲስ አብዮት ይዞ ብቅ ብሏል። በእስከአሁንም ሁለት የሰነበቱ መሪዎችን አሰናብቷል። በእርግጥም 2011 ፍትህ ዲሞክራሲና ነጻነት ለተራቡ ህዝቦች የምስራች ዘመን ይዞ የመጣ መስሏል። ሰላም ጤና ይስጥልን። ቱኒዚያ ተጀምሮ ግብጽ የተጋጋመው የህዝብ ቁጣ፤ ወደ አልጄሪያና የመን ተዛምቷል። ይህ ሰሜን አፍሪካን እየናጣት ያለው አብዮት መንግስታትን ማፈናቀል ብቻ ሳይሆን ስደትንም አስከትሏል። የዕለቱ ማህደረ ዜና መነሻውን የሰሞኑ የህዝብ ቁጣ መድረሻውን የቁጣው ውጤቶች ላይ በጣሙንም የኢጣሊያዋን ደሴት ላምፔዱሳን ውጥረት ውስጥ መግባቷ ላይ አተኩሮ ጥቂት ደቂቃዎችን አብሮአችሁ ይቆያል።

………………….

በዓለማችን በስልጣን ለረጅም ዓመታት የቆዩ መሪዎች 15 ነበሩ- እስከ 2010 መጨረሻ። እስከ ባለፈው ታህሳስ ወር ድረስ። ከ15ቱ 13ቱ የሚገኙት አፍሪካ ውስጥ ሲሆን ሁለቱ በእስያ የመንንና ባህሬን የሚመሩት ናቸው። ከእነዚህ ስልጣን ጠገብ ዕድሜ ካላቸው መሪዎች የሊቢያውን ሞአመር ጋዳፊን የሚስተካከል የለም። ጋዳፊ 42ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል- ቤተመንግስት ከገቡ። የኢትዮዽያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 20 ዓመታትን በማስቆጠር ከ15ቶቹ ውስጥ ገብተዋል። በእርግጥ 2011 ያቀጣጠለው የህዝብ ቁጣ በስልጣን ላይ ዓመታትን በከረሙት ላይ ያነጣጠረ መስሏል። በእስከአህንም 2ቱን አስወግዷል። የቱኒዚያው ቤን ዓሊና የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ ከተጣበቁበት፤ የሙጥኝ ብለው ከሰነበቱበት መንበራቸው ተፈናቀሉ። የሁለት መሪዎች ወግ--የቤን አሊና ሙባረክ። የሁለት ሀገራት ወግ --የቱኒዚያና ግብጽ። የሁለት ከተሞች ወግ--የቱኒዝና ካይሮ። ዓለም 2011 ከገባ ጀምሮ የነጻነትን ታላቅነት ሲመሰክር ሰነበተ። የህዝብ ቁጣ በእርግጥ ታሪክ ሰርቷል። ኢያሪኮ በጩኸት ፈረሰች። ቱኒዝናካይሮም የተጣበቃቸውን በጩኸት ተላቀቁት።

አትሞ

የቱኒዚያውና የግብጹ ህዝባዊ አመጾች ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያመሳስላቸው ይልቃል። ሁለቱም የህዝብ ብሶች የወለዳቸው ናቸው። ሁለቱም በአንድ መሪ፤ በአንድ ፓርቲ ለዓመታት መመራት ያንገሸገሻቸው ናቸው። ሁለቱም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተመሩ፤ ድንገት የህዝብ ቁጣ ፈንድቶ የተቀሰቀሱ የተቀጣጠሉ ናቸው። ወጣቶች የመሩዋቸው፤ ሴቶች አደባባይ ወጥተው የከረሙባቸው፤ ህጻናት ድምጻቸውን ያሰሙባቸው አመጾች ነበሩ። በእርግጥ ሁለቱም ውጤታማ ሆነዋል። ቱኒዚያ ላይ ሲጀመር ወደ ሌሎች ሀገራት ላሊዛመት እንደሚችል ፍንጭ ነበረው። 23 ዓመት በስልጣን የቆዩት ቤን ዓሊ እግሬ አውጪኝ ብለው ሲፈረጥጡ፤ ካይሮ ትኩሳቱ ጀመራት። ማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን በሆኑት ፌስ ቡክና ቲውተር የተጠራሩት ግብጻውያን እንደ ቱኒዚያዎቹ ይሳካላቸዋል ብሎ ያስበ፤ የገመተ ብዙም አልነበረም። ካይሮ ቱኒዝን አይደለችም፤ ሙባረክም ቤን ዓሊን አይደሉም የሚሉ ድምጾች ጎልቶው ሲወጡ፤ የካይሮው ታሂር አደባባይ ታሪክ ሊሰራበት የመጀመሪያው ቀን ላይ አረፈ። ጥር 25 2011 ዕለቱ ማክሰኞ። የቱኒዚው ጩኸት ካይሮ ላይ ተደገመ።

አትሞ

በእርግጥ የመጀመሪዎቹ ቀናት የሙባረክን ወንበር የሚነቀንቁ አይመስሉም ነበር። በካይሮ፤ በአሌክሳንድሪያ፤ በስዌዝ፤ እና በሌሎች የግብጽ ከተሞች ማክሰኞ የተጀመረው ህዝባዊ ቁጣ ከፖሊስ ጋር እያጋጨ እያላተመ ዘለቀ። ሙባረክ ከስልጣናቸው እንደማይወረዱ ግን በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገለጹ። በዘመነ ስልጣናቸው ያልነበረ የምክትል ፕሬዝዳንት መዋቅር አውጥተው የደህንነት ሃላፊያቸውን ማስቀመጣቸውን ገለጹ። የሙባረክ እርምጃ የታህሪር አደባባይን ከጩኸት የሚያስጥለው አልነበረም። አንድ ሳምንት አለፈ። ሁለተኛውም ተከተለ። ሙባረክም ከቤተመንግስት ህዝቡም ከታሂር አደባባይ ንቅንቅ አላሉም። የግብጽ ጦር ኃይል፤ ተቃውሞውን ያስተነፍሳል ተብሎ ሲጠበቅ በተቃራኒው የገለልተኝነት ሚናው ይዞ፤ ሙዚየሞችን ከመጠበቅ አንዳንዴም ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ከሙባረክ ደጋፊዎች ጥቃት ሲከላከል ታየ። በእርግጥ የግብጽ ጦር ሚና ለአፍሪካውያን መሪዎች ትምህርት የሰጠ ነው የሚል አስተያየት ከየቦታው ይሰማ ነበር። የሆኖ ሆኖ ዓለም የህዝብ ጉልበት የቱን ያህል ጠንካራ፤ አንዲም ከተነሳ የሚበግረው እንደሌለ ከመመስከር ሌላ ምንም ያለው የለም። የሁለተኛው ሳምንት መጨረሻ አርብ እንደ ብዙዎች ግምትና ተስፋ ሙባረክ የቤን ዓሊ እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል የሚል ነበር። ሰልፈኞቹም ዕለቱን ስም ሰጥተው አደባባይ ወጡ።ዴይ ኦፍ ዲፓርቸር- የስንብት ቀን- ለሙባረክ። ሆኖም ዕለቱ እነደስሙ ሙባረክ የተሰናበቱበት አልሆነም። እሳቸው ከመላው ዓለም የሚደርስባቸውን ግፊት ችላ ብለው ወንበሩን የሙጥኝ ማለት መወሰናቸውን እንጂ እንደሚሰናበቱ ፍንጭ እንኳን አልሰጡም። በመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት የ300 ሰዎች ህይወት የጠፋበት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉበት አመጽ ግን ቀጠለ።

Flash-Galerie Ägypten Anti-Mubarak Protest
ምስል AP

የዓለም ዓይንና ጆሮ ወደ ካይሮ በተለይም ታህሪር አደባባይ ላይ ካነጠጠረ ሶስተኛ ሳምንቱን ያዘ። ሙባረክ ለህዝቡ ጥሪ ጀርባቸውን እንደሰጡ ናቸው። 17ኛው ቀን ምሽት ላይ ለህዝባቸው ንግግር እንደሚያደርጉ ሲታወቅ የሰልፈኞች እምነት ዓለም በሞላ የጠበቀው የሙባረክን የስንብት ንግግር ነበር። ማምሻውን በመንግስት ቴሌቪዥን ብቅ ያሉት ሙባረክ ግን እስከመጪው መስከረም ስልጣን እንደማይለቁ፤ ዳግም ገለጹ። በታህሪር አደባባይ ቤቱን ትቶ ድንኳን ተክሎ በተቃውሞና ጩኸት የከረመው ሰልፈኛ ዳግም በቅጣ ተቀጣጠለ። እውነትም ቱኒዚያ ግብጽ አይደለችም። ሙባረክም ቤን ዓሊን አይደሉም።

…………………

18ኛው ቀን ዓርብ። የሙባክ የሀሙስ ምሽት እምቢኝ ከወንበሬ ንግግር የፈጠረው ንዴት ታህሪር አደባባይን፤ የአሌክሳድሪያንና ጎዳናዎች፤ የስዌዝን መንገዶች በጩኸት አመሰው። በእርግጥ 18ኛው ቀን የሙባረክ የስንበት ዕለት ይሆናል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ከተሾሙ ሁለት ሳምንት ያልሞላቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የ30 ዓመቱ የሙባረክ ሩጫ ማክተሙን ገለፁ።

አዲዮስ ሙባረክ። ታህሪር አደባባይ በደስታ ጩኸት ቀለጠች።

አትሞ

ሞሃመድ ሰይድ ሆስኒ ሙባረክ። በእርግጥ ስልጣኑን ሲይዙ በታሪካዊ አጋጣሚ ነበር። 30 ዓመት ከሰነበቱበት መንበራቸውም ሲፈነገሉ በታሪካዊ የህዝብ ዓመጽ ሆኖ ያለፈው ዓርብ ተመዘገበ። አሁን በዚያ የካይሮ ቤተመንግስት ሙባረክ የሉም። ለጦር ኃይላቸው ስልጣኑን አስረክበው፤ ከወንበራቸውም፤ ከካይሮም፤ ምናልባትም አሁን አሁን እንደሚጠረጠረው ከግብጽም ምድር ዱካቸው ጠፍቷል። እሳቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ የተወለዱ፤ በመሪነት እሳቸውን ብቻ በሚያውቁ ግብጻውያን ወጣቶች ጩኸት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናበቱ። ዓለም ከዳር እስከዳር አጀብ ሲል ነበር የሳምንቱ የእርፍት ቀናት ያለፉት። በዓመት 1 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ የምትሰጣት አሜሪካ 18ቱን ቀናት ስትንቆራጠጥ ከረመች። ከጂሚ ካርተር ጀምሮ እስከ ባራክ ኦባማ ድረስ ከ6 የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ጋር እየተጨባበጡ እየተቃቀፉ የሰነበቱት ሙባረክ ያለፈው ዓርብ ታሪካዊ መፈናቀል ሲገጥማቸው አሜሪካ የህዝብ ድምጽ ሁሌም አሸናፊ ይሆናል ነበር ያለችው። ፕሬዝዳንት ኦባማ፤ ታሪክን ሲስራ ቆመን ለመመስከር በቃን አሉ።

የሙባረክን ስንብት ተከትሎ እየተሰማ ያለው አስተያየት ብዙ መልክ አለው። በተለይ ስልጣኑን የተረከበው ወታደራዊው ቡድን ሁገሪቱን ወዴት አቅጣጫ ይመራት ይሆን የሚለው ያስፈራ ያጠራጥር ጀምሯል። አሜሪካ በአደራ ስልጣኑን የተረከበው ወታደራዊ ቡድን ከእስራዔል ጋር የተደረሰው ስምምነት ተጠብቆ እንዲቆይ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ ስትል የወታደራዊ ቡድን ቃል አቀባይ ስምምነቶች በሙሉ እንደተከበሩ ይቆያሉ ብሎ አሜሪካንንም እስራዔልንም የሚያረጋጋ ምላሽ ሰጥቷል።

የወታደሩ ቃል አቀባይ የግብጽ እጣ ፈንታ ያሰጋቸውና ለ18 ቀናት አደባባይ የሰነበቱት አንዳንዶች ጥያቄያቸን በሙሉ እስኪመለስ ወደቤት አንገባም ቢሉም በወታደሮች በግድ እንዲነሱ ተደርገዋል። ወታደራዊው ቡድን በእርግጥ ህዝቡ የሚፈልገው መሆኑ እንደማይቀር፤ ስልጣን ወደ ሲቪሉ አስተዳደር እንደሚሸጋገር ለማሳመን በመጣር ላይ ይገኛል።

አሁን ሁኔታዎች እያሉ ያሉ ቢመስሉም ሰሜን አፍሪካን የናጣት የህዝብ አመጽ ያስከለውና ለውና በቀጣይም ሊያስከትል የሚችለው ፈተና ማነጋገሩ አልቀረም። በእርግጥ ቱኒዚውያንም ሆኑ ግብጻውያን ፈላጭ ቆራጮቹን መሪዎቻቸውን ተገላግለዋቸዋል። የጭቆናውን ቀንበር አራግፈዋል። ሆኖም መጪው ጊዜ ያሰቡትን የፈለጉትን፤ የሞቱለትንና የደሙለትን ሊያስገኝላቸው ስለመቻሉ እርግጠኛ አይደለም። የግብጽ ጦር ቃል አቀባይ ግን ተስፋ አላቸው። ሁሉም ነገር እየተሻሻለ ይሄዳል ይላሉ።

ሰሜን አፍሪካ የፈነዳው ህዝባዊ አመፅ ቱኒዚያንና ግብጽን ለለውጥ አብቅቶ የሚቆም አልሆነም። ተረኛው ላይ በተራ ተጀምሯል። አዚያው ሰሜን አፍሪካ አልጄሪያ የቱኒዙና የካይሮው ማዕበል ይንጣት ጀምሯል። የመንም ተራው ደርሷት እየታመሰች ናት። አልጀርስ ላይ ባለፈው ዓርብ የጀመረው ተቃውሞ ተጋግሎ ፓሊስና ህዝቡ ተጋጭቷል። አልጀርስ እንደ

የዓለም ሰሞንኛ አጀንዳ ሆኖ የከረመው የህዝብ ዓመጽ የጀመረባት ቱኒዚያ ከቤን ዓሊ በኃላ መረጋጋት የሰማይ ያህል እንደራቃት አለች። ከመቼው በላይ ወጣቱ ቱኒዚያዊ እየተሰደደ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ቀናት የኢጣሊያዋ አነስተኛ የደሴት መንደር ላምፔዱሳ በቱኒዚያውያን ወጣቶች ተጨናንቃ ሰንብታለች። መዳረሻቸውን ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት አድርገው የወጡት እነዚህ ቱኒዚያውያን በገፍ ሆነው በጀልባ ወደ ላምፔዱሳ መጉረፍ ጀምረዋል። በ27 ጀልባዎች የተሳፈሩ 2600 ስደተኞች ያለፈው ቅዳሜ ምሽት ላምፔዱሳ ደርሰዋል። የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢጣሊያ ተወካይ ሲሞና ሞሲያሬሊ ናቸው።

ድምጽ

በእርግጥ የሰሜን አፍሪካው አብዮት ውጤቱ ለአውሮፓ ሀገራትም ሁነኛ ፈተና ይዞባቸው መጥቷል። በህገ ወጥ ስደተኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ እየተነጋገረ ያለው የአውሮፓ ህብረት የሰሞኑ የስደት ጎርፍ እንዳያጥለቀልቀው በጽኑ ሰግቷል። የኢጣሊያው የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሮቤርቶ ማሮኒ ገና የሚመጡ ስደተኞች ከቱኒዚያ የባህር ጠረፍ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ድምጽ

የኢጣሊያው የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ያቀረቡት የመፍትሄ ሀሳብ በእርግጥ ቱኒዚያን አስቆጥቷል። እዚያው ቱኒዚያ የባህር ጠረፍ ላይ ጣቢያ ተክለን ሰራዊት አቁመን ስደቱን እንግታው የሚለው የሚኒስትሩ ሃሳብ በቱኒዚያ ዘንድ የተወሰደው በሌላ ትጉም ነው። እናም የሚንትሩን ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች ቱኒዚያ። በእስከአሁን አራት ቱኒዚያውያንን ውሃ በልቶአቸዋል። ብዙዎች የት እንደገቡ አልታወቀም። የላፔዱሳ ፖሊስ አዛዥ የስደቱን ጉዙ እጅግ አደገኛ ይሉታል።

ድምጽ

በእርግጥ ኢጣሊያ እነዚህ ቱኒዚያውያን የኢኮኖሚ እንጂ የፖለቲካ ስደተኞች አይደሉም ብላ በተለያዩ አከባቢዎች ልታሰፍራቸው አቅዳለች። ይሁንና ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ የአውሮፓ ህብረት እንዲያግዛት ጠይቃለች። ህብረቱ ሌሎች ስደተኞችን መቀበል ይቅርና ቀድመው የገቡትን ፍቃድ ያልተሰጣቸውን ወደ ሊቢያ ለመመለስ እያሰበ ባለበት በዚህን ወቅት የቱኒዚያውያኑ ስደት ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። አሁን የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ካትሪን አሽተን ቱኒዚያ ይገኛሉ። ዋንኛው ትኩረታቸውም ይኸው የስደተኞቹ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

……………..

ቱኒዚያ ጀመረ ግብጽ ተከተለ። በሁለቱም የተሳካ የህዝብ ዓመጽ ተካሄደ። ተረኞቹ ሀገራት ትኩሳቱ ጀምሮአቸዋል። ህዝብ ዘንድሮ በእርግጥ በጨቋኝ መሪዎች ላይ ተነስቷል። መሳይ መኮንን ነበርኩ…ጤና ይስጥልኝ