1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሜን ጎንደር ዞን በሦስት ዞኖች ተከፈለ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2009

ሰሜን ጎንደር ዞን በ3 ዞኖች መከፈሉ ተገለጠ። ይህ የተደረገው አካባቢው እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ለአስተዳደር አመቺ ባለመሆኑ ነው ሲል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል። በአካባቢው የተቃውሞ ንቅናቄዎችን እንደሚያስተባብሩ የገለጡት አቶ ቴዎድሮስ ከበደ በበኩላቸው «ዞኑ የተከፋፈለው የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን ነው» ይላሉ።

https://p.dw.com/p/2j5dC
Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

Northern Gonder Zone divided in two three - MP3-Stereo

ከከፍተኛው የራስ ዳሸን ተራራ አንስቶ እስከ ዝቅተኛው የመተማ ቆላማ አካባቢዎችን ያካትታል ሰሜን ጎንደር ዞን። የክልሉ አስተዳደር፦ ዞኑ ሰፊ የቆዳ ስፋትን የሚያካትት በመሆኑ «ለአስተዳደር አመቺ አይደለም» ይላል። ሰሜን ጎንደር ዞን በመንግሥት ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎችንም አስተናግዷል። ከተጎራባች ትግራይ ክልል ጋርም የድንበር እና የማንነት ጥያቄ በተደጋጋሚ ይስተጋባበታል። ይኽ ዞን አሁን በሦስት ዞኖች መከፈሉ ተገልጧል። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ በቀለ ዞኑን በሦስት መክፈል ያስፈለገበት ምክንያት የሚከተለው ነው ይላሉ።

«በሦስት ዞን የተደራጀበት ምክንያት፤ ዞኑ ከሌሎች ዞኖች አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ከ46 ሺህ ስኲዌር ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት አለው። የሕዝብ ቁጥሩም ከ 3.8 ሚሊዮን በላይ ነው። ከዚያ ባሻገርም ዞኑ የመሠረተ-ልማት ተደራሽነት፣ የመልካም አስተዳደር  አገልግሎት ተደራሽነት፤ በአጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴውን ከሌሎች ዞኖች እኩል ለመምራት ፈታኝ ኹኔታዎች አሉበት። የመልክአ-ምድሩም አቀማመጥ በጣም አስቸጋሪ ወጣ ገባ  እና ዳገት፣ ቁልቁለት ያለበት ነው። በዚህ የተነሳ ኅብረተሰቡም  ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት ወደ አንድ የዞን ማእከል ማሰባሰቡ በጣም አስቸጋሪ ነበረ።»
በተናጠልም በተደራጀ መልኩም ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ ሰፊ ጥናት በማድረግ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ዞኑን በሦስት የማካለል ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ አቶ ጸጋዬ ተናግረዋል። በዚህም «ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቷል» ብለዋል።   በአካባቢው ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ከሚያስተባብሩ አካላት አንዱ መሆናቸውን የገለጡት የአምሃራ ራስን እና ወገን አድን አርበኝነታዊ ተጋድሎ ንቅናቄ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ቴዎድሮስ ከበደ ግን ውሳኔው የተላለፈው «የሕዝቡን ጥያቄ ለማፈን ነው» ይላሉ።

«ሰሜን ጎንደር ውስጥ ያሉ ለም መሬቶችንና ሕዝቡን ባላቸው የመንግሥት ሥልጣን፣ ጉልበት ተጠቅመው የአማራን ህዝብ ማዳከም እና  መጨቆን የእነሱ ተንበርካኪ፣ የእነሱ ተገዥ ኹኖ እንዲኖር ስለሚፈልጉ በእነሱና በተላላኪያቸው ብአዴን ባለሥልጣኖቻቸው ሕዝብን ለማንበርከክና የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን ስለሆነ በእኛ በኩል የህዝብ ጥያቄ አልተመለሰም መመለስም የሚችል አቅምም ፍላጎትም የላቸውም ስለዚህ የህዝቡ ጥያቄ በእዚህ መልኩ ሊመለስ አይችልም።»

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

የሰሜን ጎንደር መተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ አድማጫችን በበኩላቸው ሰሜን ጎንደር ዞንን ለሦስት ከመከፋፈል በፊት ሌሎች ሊሠራባቸው የሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ ይላሉ። 

«ከምንም በላይ ጎንደርን ጎንደር የሚያስብለው ማንነቱ፤ ድንበሩ ነው መጠበቅ ያለበት። ከዚያ በኋላ ሌላው ነገር ጊዜው የሚያመጣው ነው ይደርሳል። የክልሉ ድንበር ነው በቃ መጠበቅ ያለበት። ያ ሳይጠበቅ ይኼ በሦስት ከፈልነው አራት ከፈልነው [ምንም ነገር የለውም።]»

ሰሜን ጎንደር ዞር እና አካባቢው ተደጋጋሚ ግጭቶች እና የመንግሥት ተቃውሞዎች የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ናቸው። የተለያዩ ጥያቄዎችም ይደመጡበታል። አቶ ቴዎድሮስ ከበደ።
«የዞኑ በሦስት መከፈል እንግዲህ እነሱ አቅደውታል። አሁን ደግሞ ሌላ ነገር እያሰሙን ነው። ከፊል መተማን እና ታች በረሃማውን ቆላ የቋራን አካባቢ ወደ ክልል ስድስት ለመስደድ አሁን ካድሬዎቻቸው እየተንቀሳቀሱ ነው። ሌላው ሁለቱ ዞኖች ደግሞ  ያው በቅማንት ስም ከፊል መተማ እና ታች አርማጭሆን ወደ ወልቃይት ኹመራ አካባቢ አጠቃለው የቅማንት ዞን ከተሰኘ በኋላ ቅማንቶችን ከክልል ትግራይ ጋር አዋስነው የእነሱን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያደርጉት እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይደለም።  ሕዝቡም እኛም በደንብ አድርገን ዕናውቃለን። ይኼ ነገር እንዳይሆን ደግሞ ከፍተኛ ትግል እየተደረገ ነው። እኛም ዘመቻ ካሣ ብለን ተጋድሎዎችን እያደረግን ነው።»

«ግጭቶች መነሻቸው የሕዝብ የእርካታ ችግር ነው» ያሉት አቶ ጸጋዬ በቀለ ደግሞ «የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ ችግሮችም እንደሚፈቱ ተናግረዋል። «እነዚህ ሲመለሱ የግጭት ችግሮችም እግረመንገዳቸው እየተፈቱ ይሄዳሉ። አስተዳደሩም ሁሉንም አይነት አገልግሎት በቅርብ ርቀት ያገኛል።  እነዚህ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ተመለሱ ማለት ደግሞ ግጭቶችም መልስ እያገኙ ይሄዳሉ ማለት ነው። ከዚህ ውጪ ያሉ ጥያቄዎች ካሉ ደግሞ አሁንም ቢሆን ኅብረተሰቡ ነጻ ሆኖ ጥያቄዎችን ማንሳት ይችላል። እና የተለየ ትርጉም ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም በእኛ እይታ።»

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዲስ ባወጣው አደረጃጀት፦ ሰሜን ጎንደር ዞን ማእከሉን ደባርቅ ከተማ ላይ አድርጎ በስምንት ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ተደራጅቷል። ምዕራብ ጎንደር በበኩሉ ገንዳ ውሃ ከተማ ላይ ሦስት የከተማ አስተዳደሮች እና አራት የወረዳ አስተዳደር ተደርጎለታል።  ማዕከላዊ ጎንደር ደግሞ ጎንደር ከተማ አስተዳደርን ይዞ በዙሪያው ዐሥራ ሁለት ወረዳዎችን ማካተቱ ተገልጧል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ