1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰብዓዊ ሁኔታ በደቡብ ሱዳን

ማክሰኞ፣ የካቲት 27 2010

በእርስ በርስ ጦርነት ከ5 ዓመት በላይ የደቀቀችው ደቡብ ሱዳን አሁን የምትገኝበት አሳሳቢ መሆኑን የእርዳታ ድርጅቶች ያመለክታሉ። በተለያዩ ነፍጥ አንጋቢዎች ሰላሙ የደፈረሰው ዜጋ ገሚሱ ለሞት፤ የተረፈዉም ለስደት እና ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጧል። ፖለቲከኞቿ ዛሬም ለሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት ሊፈጥር የሚችል ሰላም ለማስፈን የተዘጋጁ አይመስሉም።

https://p.dw.com/p/2tnQo
Südsudan UN denken über Verstärkung von Unmiss nach
ምስል Reuters/A. Ohanesian

የፀጥታ ሁኔታዉ አሁንም አስተማማኝ አይመስልም

 ፒቦር ዉስጥ የበዓል ድባብ ሰፍኗል። በስተ ምሥራቅ ሱዳን ከቦር ከተማ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ለበዓሉ ሥርዓት ሲባል ዳግም ተከፍቷል። የፒቦር ነዋሪዎች ከዉጭ ዓለም ጋር የሚገናኙበት ብቸኛው መስመር ይኸው ነው። ለወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ጥቃት ምክንያት እንዲሁም በዝናብ ወቅት መንገዱ ስለሚሰምጥ መስመሩ ተቋርጦ ነበር። የከተማዋ ነዋሪዎች ራሳቸውን በዚህ ረገድ እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ብዙም አያዉቁም። አንጀሊና ክሌመንት የአካባቢዉ ነዋሪ ናቸዉ፤

«መንገዱ በሚዘጋበት ጊዜ የምግብ ሸቀጥ የሚያቀርብልን አናገኝም፤ በዚህ ምክንያት ድንገር የማሽላ ዋጋ ሁለት እጅ እጥፍ፤ እንዲሁም የምግብ ዘይትም በ20 እጅ እጥፍ ጨመረ። መንገዱ ከተከፈተ ጀምሮ እንደ ዕድል ሆኖ ዋጋዉ መልሶ ቀንሷል።»

በሱዳን የተመድ ተልዕኮ በ22 ቀናት ዉስጥ 200 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል እንዲጠገን አድርጓል። አሁን ወደፒቦር የእርዳታ አቅርቦት ዳግም መድረስ ችሏል። በአካባቢዉ የሚኖሩ ሴቶችም ወደሃኪም ለመሄድ፤ ልጆችም ወደ ትምህርት ቤት ዳግም መጓጓዝ ጀምረዋል። የተስፋ ብልጭታ።

«ግድያን እንቃወማለን» ይላል በአካባቢዉ አስተዳደር ዉስጥ የሚገኘው ዳዊት ያዉ ያዉ። «የኑሮ ሁኔታችንን ማሻሻል እንፈልጋለን፤ የሚጠጣ ዉኃ የለንም፤ ትምህርት ቤትም የለንም፤ በዚም ምክንያት ወጣቶች በአካባቢዉ እንዲሁ ሥራ ፈትተው ይዉላሉ።»

Flüchtlingslager Tomping in Juba Südsudan
ምስል DW/Scholz/Kriesch

ምንም እንኳን ከገና በዓል አንስቶ በተዋጊ ኃይሎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም የሚፀና አይነት አይደለም። መንግሥት እና አማፅያን መደራደራቸዉን ቀጥለዋል። ሆኖም ግን ይህንን ደም አፋሳሽ ቀውስ ለማስቆም መፈለጋቸዉ ወይም እንደዚያ የማሰባቸዉ ነገር እርግጠኛ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም። የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ጀምሮ ተጨማሪ ታጣቂ ኃይሎች አብዛኞቹም የየራሳቸዉ ግብ ያላቸው እንዲሁ ተራ ወንጀለኛ ቡድኖች እየተፈጠሩ ነው። እስካሁን 10 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል፤ አራት ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ተሰደዋል። 7,5 ሚሊየን የሚሆኑ ደቡብ ሱዳናዉያን ሕይወታቸውን ለማሰንበት የሚረዳ አስቸኳይ ርዳታ ይፈልጋሉ። በተለይም ደግሞ ልጆች ክፉኛ ለችግር መጋለጣቸዉን የተመ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሲኤፍ ሥራ አስኪያጅ ሄንሪታ ፎሬ ይናገራሉ።

«ለልጆች እጅግ አስከፊ ሁኔታ ነው፤ ምክንያቱም በጥቃቱ የእኔ የሚሏቸዉን ያጣሉ፤ ወይም ደግሞ ከቤተሰቦቻቸዉ በዚሁ ምክንያት ይለያያሉ። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ በሀገሪቱ ሳር እና የዉኃ ላይ ተክሎችን እየተመገቡ ብቻቸዉን ይዞራሉ፤ ዓለም ደግሞ ይህን ችላ ማለት አይችልም።»

Südsudan UN denken über Verstärkung von Unmiss nach
ምስል picture alliance/AP Photo/J. Patinkin

በድርድሩ ሂደትም ዉጊያዉ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ነዉ። ሆኖም ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበረው የሰዎች ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ብሎ ሙሉ በሙሉ ለመናገር በጣም ገና ነው። እንዲያም ሆኖ ሊሻሻል የሚችልባቸው ዕድሎች መኖራቸው ይታያል። ለዚህም ነው አሁን ርዳታ ሲመጣ የታየው።

«ግጭቱ ዛሬ የሚያከትም እንኳን ቢሆን ልጆች አሁንም አስቸኳይ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል።» ይላሉ በሱዳን የዩኒሴፍ ተጠሪ ማሂምቦ ንዶይ። ሆኖም ግን ድርጅታቸው ለዚሁ ሥራ 183 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገዋል። እስካሁን ያገኘው ግን አንድ ሦስተኛዉን ብቻ ነው። ገንዘቡ የባከነው ትዉልድ ሁሉ ዳግም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንዲችል የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የምግብ ርዳታ ለማቅረብም እጅግ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም በመጪዉ የድርቅ ወቅት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚጎዱት ሕጻናት ቁጥር ዳግም ይጨምራል። 

ሸዋዬ ለገሠ/ ዩርገን ስትራይክ

ኂሩት መለሰ