1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰኔ 30 ሀገር አቀፍ የንባብ ቀን

ሐሙስ፣ ሐምሌ 2 2007

ሰኔ 30 ሀገር አቀፍ የንባብ ቀን በሚል የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ስላዘጋጀዉ የመጽሐፍ ትርኢትና ሽያጭ በተመለከተ መምህር ደረጀ ገብሪ የሰጡንን አስተያየት ነበር ያደመጣችሁት። በትርኢቱ የታሪክና ተረት ነገራ መረሐ-ግብር የልምድ ልዉዉጥ ሂሳዊ ዉይይቶች የመጽሐፍ ስጦታዎችና ሌሎች በርካታ ዝግጅቶች ተዘጋጅተዉ እንደነበር ተመልክቶአል።

https://p.dw.com/p/1FvYw
Buchmesse in Addis Abeba Lesetag
ምስል Ethiopian Writers Association

[No title]


የዓመቱ የትምህርት ጊዜ ሲጠናቀቅ በተለምዶ ሰኔ ሰላሳ ከማንበብና ከመጻፍ መለያያ ጊዜ አድርጎ የመዉሰድ ልምድ በማስወገድ እንደዉም ሰኔ 30 ንባብ የሚጀመርበት ቤተሰብ እህት ወንድ ጓደኛ ሰፊዉን ክረምት ወራት መጽሐፍን የማንበብ ልምድን የሚያጎለብትበት የልምድ የመለዋወጫ ጊዜ እንዲሆን የተጀመረ ዝግጅት ነዉ ያሉን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በአማርኛ ቋንቋና በሥነ-ጽሑፍ ትምህርት መምህር ደረጀ ገብሬ፤
«ትርኢቱን ያዘጋጀዉ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ነዉ ማኅበሩ ሰኔ ሰላሳ በኢትዮጵያ የንባብ ቀን ተብሎ እንዲከበር አስቦ የተንቀሳቀሰ ነዉ ከአምና ጀምሮ። ይህ ዝግጅት ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ነዉ። የንባብ ባህልን ለማዳበር ልምድን ለመቀያየር ፤ ወጣቱም ትምህርት ቤት ተዘግቶ ሰፈር ዉስጥ መዋልን ስለሚጀምር አንባቢ እንዲሁኑ ጊዜያቸዉን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ከመጥፎ ነገር እንዲቆጠቡ ከመጽሐፍት ጋር ለማስተዋወቅ የተደረገ ዝግጅት ነዉ።
የኢትዮጵያ የደረሳንያን ማኅበር ከቀደመዉ ጊዜ በፊት ጀምሮ በሃገሪቱ ላሉ ስነ-ጽሑፎች እና የትምህርት ስርዓርአት መጠንከር ቀዳሚ ድርሻን ሲያበረክት የቆየ ተቋም ነዉ፤ አሁንም የንባብ ባህል እንዲሆን ጥረት በማድረግ ላይ ነዉ ሲሉ የገለፁት የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ይታገሱ ጌትነት፤
« የኢትዮጵያ የደረሳንያን ማኅበር ከቀደመዉ ዘመን አንስቶ በአባላቶቹ አማክኝነት የትምህርት ስርዓቱ ላይና በሀገሪቱ የእዉቀት ስርዓቶች ላይ በርካታ አስተዋጽዖን ሲያደርግ የቆየ ተቋም ነዉ። ከዝቂት ዓመታት ወዲህ ግን በጣም የተዳከመ የንባብ ባህል በሀገሪቱ ዉስጥ እየተንሰራፋ የመጣበት ሁኔታ ይታይ ነበር፤ እነዚህን ነገሮች ማስተካከል የሚቻልበት ማኅበረሰቡ በእዉቀት የሚጎለብትበት አንድ ንቅናቄ ያስፈልጋል በሚል እምነት በመያዝ፤ ይሄንንም ከጊዜ አንጻር በአብዛኛዉ አንባቢን የሚገኝበት ጊዜ ቢመረጥና በሀገራችን የንባብ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ማድረግ ቢቻል ሰዎችን ወደንባብ መሳብ ይቻላል፤ የተዳከመዉንም የንባብ ባህል በማዳበር በሃገሪቱ ዉስጥ ያለዉን የእዉቀት መስፋፋት ሂደት ማጠናከር ይቻላል በሚል እምነት ነዉ ማኅበሩ ይህን ዝግጅት ያቀደዉ።»
የደራስያን ማኅበር የንባብ ባህል ንቅናቄ በሚል መርሁ ሥር « ልጆን ከመችሐፍ ጋር ሲያወዳጁ ነገዉን አብጁ» «ንባብ ለብቁ ተወዳዳሪነት የመፍትሔ ቁልፍ ነዉ» « ንባብ አስተማማኝ ድህነትን መመከቻ ጋሻ ነዉ» « ብልህ ከመጽሐፍ ይማራል ፤ ሰነፍ በነፍሱ ይከስራል» የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብቶአል። ዝግጅቱ ይላሉ አቶ ይታገሱ ጌትነት በመቀጠል፤
«ዝግጅቱ ለአምስት ቀናት ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 30 ድረስ የተካሄደዉ መጽሐፍትን አደባባይ ላይ ለማኅበረሰቡ በማቅረብ የመጽሐፍ ትርኢትን በማሳየት ተከናዉኖአል። ይህ ግን በዚህ የሚቆም አይሆንም፤ በየክልሉ በሚገኙ የማኅበሩ ቅርንጫፎች በመቀሌ በባህርዳር ፤ በጎንደር በደሴና በሰመራና በሐረር ያሉ ቅርንቻፎች አሉ፤ ይህን ፕሮግራም ወደራሳቸዉ ወስደዉ የሚያከናዉኑት ነዉ የሚሆነዉ።»
እንዲህ አይነቱ የመጽሐፍ ትርኢት በሃገራችን የመጀመርያዉ አይደለም ያሉት መምህር ደረጀ ገብሪ በበኩላቸዉ፣
« እንዲህ አይነቱ የመጽሐፍ ትርኢት ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለአስረኛ ጊዜ አካሂደናል፤የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስቴርና የወመዘክር ቤተ-መጽሐፍት በመተባበር ለአንድ ሳምንት አካሂደዋል፤ ከሐምሌ 23 እስከ 26 እንዲሁ በእግዚቢሽን ማዕከል የመጽሐፍ ትርኢት ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የመጽሐፍት ትርኢት ማካሄድ ራሱ ባህል እየሆነ መጥቶአል።
“ሰኔ 30 የንባብ ቀን” በሚል መርህ የማህበሩ ቅርንጫፎች በሚገኙባቸው ሐረር፣ ጎንደር፣ ሰመራ፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር እና ሌሎች ከተሞች ውስጥ ከንባብ ጋር የተያያዙ የውይይትና የስነ-ጽሑፍ መድረኮች እንደተዘጋጁም ተገልጧል፡፡ ፕሮግራሙ ህጻናትንም አልዘነጋም፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰዉ ያደርጋልና፤
«ማንበብ ሙሉ ሰዉ ያደርጋል የሚል ነዉ በሀገሪቱ ያለዉ መፈክር። በመጽሐፍ ዙርያ የሚሰሩ በሪድዮም የሚናገሩ በቴሌቭዝንም የሚያቀርቡ በመጽሐፍት ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ሰዎች እንደ ዋና መፈክር አድርገዉ የያዙት ማንበብ ሙሉ ሰዉ ያደርጋል ነዉ።»

በአዲስ አበባ ዘመናዊ ትምህርት ጀመረ በሚባልበት ቦታ ይህ የመጽሐፍ አዉደ ርዕይ መካሄዱን የገለጹት የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ይታገሱ ጌትነት፤
« ትርኢቱ የተደረገዉ የዘመናዊ ትምህርት መጀመርያ ቦታ ነዉ በሚባለዉ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በሚገኘዉ ቦታ ላይ ነዉ፤1900 ወይም 1907 ዓ,ም አካባቢ ላይ ይመስለኛል ። ይህ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘዉ ቦታ ላይ በርካታ ሰዉ ይንቀሳቀሳል ከላይ የስድስት ኪሎ ከታች በኩል የአራት ኪሎ ዩንቨርስቲ አለ። በንባብ ንቅናቄዉ ላይ በተለያዩ እድሜ እና እዉቀት ደረጃ ላይ የሚገኙ አካላት ተገኝተዉ በቦታዉ ላይ የንባብ ሰዓት ተካሂድዋል።»
በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ አንባቢ እንደመጨመሩ በመጠን አሳታሚዉም ሆነ ደራሲዉ ጥቂት እንዳልሆነ ይነገራል። ግን ቋንቋዉ ጥራቱን ምን ያህል የጠበቀነዉ ፤ ከዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ምን አይነት አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይሆን የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ይታገሱ ጌትነት፤
« በመሰረቱ እንዲህ አይነቱ የስነጽሑፍ መጓደል ክስተቶች በየትናዉም ዘመን ላይ ሊያጋጥም ይችላል። በነባሩም በአሁኑም። ይህ ከዘመኑ የአኗኗር እድገት ሁኔታ ነዉ የሚፈታዉ። ለምሳሌ የእዉቀትና የቋንቋዎች መደበላለቅ ዘመን በሆነበት ጊዜ ላይ ዲቃላ የሆኑ ቃላቶች መምጣታቸዉ የማይታበል ሃቅ ነዉ። ይህ በቋንቋ ዉስጥ ተፈጥሮዋዊ ነዉ። ያም ቢሆን ግን የሥነ-ጽሑፍን ከፍታን ሊያሳይ የሚችለዉ መደበኛዉን የቋንቋ ቅርስ ተከትሎ እያንዳንዱ ሥነ-ጽሑፍ ዉስጥ በተገቢዉ ሁኔታ መገለፁ ና መቀመጡ አንዱ መለክያ ሆኖ ይቀመጣል።»
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋና በሥነ-ጽሑፍ ትምህርት መምህር ደረጀ ገብሬ በበኩላቸዉ ፤ መጽሐፍ መታተሙ በጀመርያ የሚደገፍ ነዉ፤ ጥራት በሂደት የሚገኝ ነዉ
« መጽሐፍ መዉጣቱ በራሱ ጥሩ ነዉ ጥራት በሂደት ነዉ የሚመጣዉ በየሞያ ። ጥሩ ጥሩ መጽሐፍት አሉ፤ ተልካሻ አይነቶችም አሉ። በኔ አስተያየት መታተማቸዉን በማንኛዉም አቅጣጫ እደግፋለሁ። ነገርግን ህትመት ጥራት የፊደሎች ግድፈት፤ አጣጥሞና ቋንቋቸዉን አስተካክሎ ማቅረብ ያስፈልጋል። በተጻፉበት አይነት መስክ ማለቴ ነዉ። ግን ይህንን ሳያሟሉ የሚታተሙም አሉ። ሁሉም መጽሐፍ የተባለዉን ጥራት ጠብቀዉ አናገኛቸዉም ። በጥያም መጠን እጅግ ጥሩ መጽሐፍ ጥራቱን የጠበቀ ለአንባቢ ይቀርባል።
በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል የማንበብ ባህልን ለማስፍት በተለያዩ ጉዜያት የተለያዩ ዝግጅቶችን አካሂዶአል። የማዕከሉ የቤተ-መጽሐፍትና የኢንፎርሜሽ ክፍል ሃላፊ አቶ ዮናስ ታረቀኝ እንደገለፁት የማንበብ ባህልን ለማጎበት በተለይ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር ይሰራሉ
«እስካሁን እጅግ ትልቁ የምንለዉ የዛሬ ሰባት አመት አዲስ አበባ ታንብብ ብለን የጀመርነዉ የመጽሐፍ ንባብ ክፍለጊዜ ነዉ ይህ ዝግጅት ላይፕሲሽ ከሚገኘዉ ዓለማቀፍ የመጽሐፍ አዉድ በመነሳት የጀመርነዉ ነዉ። ከዝያም በቀጠሉት ዓመታት ዝግጅቱን በማስፋት ኢትዮጵያ ታንብብ ብለን ዝግጅቱን ቀጠልን። በዚህ ዝግጅት ላይ ታዋቂ ጽሐፍቶችና የስነጽሑፍ ባለሞያዎች በየትምህርት ቤቱ በመሄድ የንባብ ፕሮግራም ለተማሪዎች ያዘጋጃሉ። ለተማሪዎች ስለንባብ አስፈላጊነት ስለንባብ ጥቅም እንሰብካለን እናስተምራለን።
የመጀመርያዉን የጎዳና ላይ የመጽሐፍ አዉደ ርዕይ በጀርመን የባህል ማዕከል ጎተ ኢንስቲቲዉት እንደተደረገ የሚገልፁት አቶ ዮናስ ታረቀኝ በሐምሌ ወር ሌላ ትልቅ የንባብና የመፅሐፍ አዉደ ርዕይ ዝግጅት እንዳላቸዉ ገልፀዋል።
ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Buchmesse in Addis Abeba Lesetag
ምስል Ethiopian Writers Association
Buchmesse in Addis Abeba Lesetag
ምስል Ethiopian Writers Association
Buchmesse in Addis Abeba Lesetag
ምስል Ethiopian Writers Association