1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰንዓ፤ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት አሊ አብደላ ሳልህ መገደላቸዉ

ሰኞ፣ ኅዳር 25 2010

በየመን የሚንቀሳቀሰዉ የሁቲ አማፅያን ቡድን የቀድሞዉ የየመን ፕሬዝደንት አሊ አብደላ ሳልህ መገደላቸዉን አስታዉቋል። መረጃዉን ይፋ ያደረገዉ ለሁቲ ቅርበት ያለዉ የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር ሲሆን ከሳልህ በተጨማሪ በርካታ ደጋፊዎቻቸዉም መገደላቸዉን ገልጿል። የሁቲ ሚሊሻዎች የሳልህ መኖሪያ ቤት ላይም ጥቃት ማድረሳቸዉንም ዘገባዉ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/2okgv
Jemens ehemaliger Präsident Ali Abdullah Saleh
ምስል picture-alliance/dpa/epa/Str

 የሳልህ ነዉ የተባለ ፎቶ እና ቪዲዮም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተሰራጭቷል። ዘግየት ብሎም የሳልህ ፓርቲ አጠቃላይ የሕዝቦች ምክር ቤት ዜናዉን ማረጋገጡን አል አረቢያ ዘግቧል። ሮይተርስ ፓርቲዉን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ሳልህ ከሰንዓ ዉጭ በሁቲዎች በተሰነዘረባቸዉ ጥቃት ነዉ የተገደሉት።

Jemens ehemaliger Präsident Ali Abdullah Saleh
ምስል picture-alliance/dpa/epa/Str

በዋና ከተማዋ ሰንዓ በኢራን እንደሚደገፉ በሚነገርላቸዉ የየመን ሁቲ ሚሊሺያዎች እና በቀድሞዉ የየመን ፕሬዝደንት አሊ አብደላ ሳላህ ደጋፊዎች መካከል የሚካሄደዉ ዉጊያ መጠናከሩም ተገልጿል። በዉጊያዉ እስካሁን ቢያንስ 125 መገደላቸዉን ፤ 238 ደግሞ መጎዳታቸዉን ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።  የሳላህ ደጋፊዎች ከሁቲዎች ጋር ስድስት ቀናት ባስቆጠረዉ የከተማ ዉጊያ ሚዛናቸዉን እያጡ እንደሆነ ተገልጿል። ሳዑድ አረቢያ መራሹ ኃይል በበኩሉ የሁቲዎችን ይዞታ ለሁለተኛ ቀን ከአየር መደብደቡንም ሮይተርስ ጠቅሷል። ቀደም ሲል ሳላህ ከሁቲዎች ጋር በማበር ሳዉዲን ይቃወሙ እንደነበር አይዘነጋም። ከሁቲዎች ጋር ቅራኔ ዉስጥ ከገቡ በኋላ ን ሳዑዲ ድጋፏን እየሰጠቻቸዉ እንደሆነ ነዉ የተገለጸዉ። በዋና ከተማዋ የሚካሄደዉ ዉጊያ እና የአዉሮፕላን ድብደባ የሰንዓ ነዋሪዎችን ጭንቅ ዉስጥ እንደከተተ ያመለከቱት በየመን የተመ የልማት እና የሰብዓዊ ርዳታዎች አስተባባሪ ጃሚ ማክጎልድሪክ በዚህ ምክንያት ሲቩሉን ኅብረተሰብ ለመርዳት አዳጋች እንደሆነባቸዉ ገልጸዋል።

Jemen Sanaa Kämpfe
ምስል Reuters/M. al-Sayaghi

«ከባድ መሣሪያ ሲጠቀሙ እና ስታኮሱ እንዲሁም ከአየር ድብደባዉ ማምለጥ የሚያስችል ቦታ ለማግኘት በጣም አዳጋች ነዉ። ስለዚህ ሰዎች የሚችሉትን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ መልዕክቶችን እንልካለን። ሆኖም ግን ከእነሱም ሆነ ከእኛ ቁጥጥር ዉጭ የሚሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ዉጊያዉ የሚካሄድበት አቅራቢያ በመሆናችን ምክንያት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ አባላት ምድር ቤት ዉስጥ ነዉ የምንገኘዉ። በዚህም ምክንያት በቀላሉ ወደዉጭች ወጥተን የእኛን ርዳታ የሚፈልጉትን የተጎዱትን ወይም የታመሙትን መርዳት አንችልም።»

ይህ በእንዲህ እንዳለም ትናንት ከሰዓት በኋላ የኢራን ኤምባሲ በሮኬት መመታቱ እና በዚህ ሰበብም በእሳት መጋየቱ ተዘግቧል። ሮኬቱ ከማን እንደተተኮሰ ግን እስካሁን ግልፅ የወጣ ነገር የለም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ