1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰዓሊዉና ቡሩሹ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 23 2012

«ችግራችን ስራዎቻችንን የምናሳይበት ጋለሪ የለንም ፤ ይህ ችግራችን ሲጓተት የመጣ ነዉ። ሙዚቃም ጥበብ ነዉ። ትያትርም ጥበብ ነዉ። ፊልም ጥበብ ነዉ። ስዕልም እንደሌላዉ ሁሉ ጥበብ ነዉ። መንግሥት ይህን ችግራችንን አይቶ፤ የስዕል ማሳያ ቦታ ቢያቆምልን ስንል እንጠይቃለን። »

https://p.dw.com/p/3TUTX
Äthiopien Botschaftstour für junge Künstler
ምስል Privat

መንግሥት እንደ ፊልምና ትያቴር ቤት ሁሉ የስዕል ጋለሪ ይከፈትልን

«በኢዮቤልዩ ቤተ-መንግስት፤ ማለትም በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ መኖርያ ቤት እንዲህ አይነት የስዕል አዉደ ርዕይ ሲካሄድ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። ይህ ደግሞ መንግሥትና እታች ያለዉ ሕዝብ አብሮ የመሆን የቤተሰባዊ ስሜትን መፍጠር ነዉ። በእለቱ የሆነዉ ያንን ቤት ማለት ቤተ-መንግሥቱን ከርቁ የምንመለከተዉ ሰዎች አሁን ግን ቤታችን እንደሆነ አይነት ስሜት እንዲሰጠን ያደረገ ትዕይንት ነበር ። ፕሬዚዳንቷም ልክ እንደ ቤተሰብ አስጎብኝ እየተዘዋወሩ ጓዳ ጎድጓዳዉን  እንዲህ ነዉ እንዲህ ነዉ እያሉ ፤ ያለዉን ሁሉ በግልጽ አስረድተዋል። »

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

ሰዓሊ ስዩም አያሌዉ ይባላል። ሰሞኑን የኢዮቤልዩ አልያም ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትን ከጥበብ ስራዎቻቸዉ ጋር ከጎበኙ የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ ነዉ። በርከት ያሉ ሰዓሊያን የሥነ-ጥበብ ስራቸዉን ይዘዉ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ኤንባሲዎች የአንድ ቀን ዓዉደ ርዕይ ማዘጋጀት ከጀመሩ ሰባት ዓመት ሆንዋቸዋል። በዘንድሮ ዓመት ዝግጅታቸዉ ግን ከተለያዩ ኤንባሲዎች በተጨማሪ በኢዮቤልዩ ቤተ- መንግሥትም  የሥነ-ጥበብ ስራዎቻቸዉን ይዘዉ ተገኝተዉ ለክብር ት ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘዉዴ አሳይተዋል።  በክብርት ፕሬዚዳንትዋ መኖርያ ቤትም ሻይ ቡና ብለዋል።  በተለያዩ ኤንባሲዎች የሥነ-ጥበብ ስራን ማሳየት ከጀመረ ሰባት ዓመት የሆነዉ እና የዚህ ኃሳብ አምጭ ከሆኑት ሰዓልያን መካከል ሰዓሊ ሰይፉ አበበ ይገኝበታል።                                                                                                                                                                                                                         «እኛ በየዓመቱ  ስዕልን ይዘን በመጓዝ የምናዘጋጀዉ ዓዉደ ርዕይ አለ። ሰዎችን በአዉቶቡስ ይዘን ፤ የተለያዩ የስዕል ባለሞያዎችንና ስራዎቻቸዉን ሰብስበን፤ እናሳያለን። እንዲህ እያደረግን በአዲስ አበባ በሚገኙ በተለያዩ ኤምባሲዎች ዝግጅት ማድረግ ከጀመርን ሰባት ዓመት ሞልቶናል። ለምሳሌ በዚህ ዓመት በቤልጄምኤምባሲ፤ ፈረንሳይና ጀርመን ኤንባሲ እንድናዘጋጅ  ፈቃደኛ ነበሩ፤ ስራዎቻችንንም  አሳይተናል። ባለፈዉ ዓመት ደግሞ ፈረንሳይና ቤልጄም ኤምባሲ ፈቃደኛ ነበሩ። ከዛም በፊት ፖላንድ ኤምባሲ እንዲሁ ፈቃደኛ ነበር። በአሁኑ ዓመት ምንድን ነዉ ለየት የሚያደርገዉ ኤንባሲዎቹ ጋር የስዕል ስራዎቻችንን ለማሳየት ዝግጅት ላይ እያለን፤ ቤተ-መንግሥትም እንዲፈቀድልን ጠየቅን፤ ተፈቀደልንም። በዚህ ዝግጅት ላይ በተለይ ወጣት ሰዓልያንን ለማሳተፍ እና ድጋፍ ለመስጠት ፤ እንዲነቃቁ ለማድረግ ከነስዕሎቻቸዉ ቤተ-መንግሥት ስዕሎቻቸዉን ለእይታ እንዲያቀርቡ  አደረግን።  በቂ እዉቀት እና ልምድ ያላቸዉ ሰዓልያን ደግሞ በተለያዩ ኤንባሲዎች ስራቸዉን እይዲያሳዩ አደረግን። ቤተ-መንግሥቱ ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ምንም አይነት የሥነ-ጥበብ ዝግጅት አልተደረገበትም። እና ይህን በመፍቀዳቸዉ እጅግ ደስተኞች ነን። በቤተ-መንግሥቱ ዉስጥ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከሚኖሩበት ቤት ጀርባ የጃፓን ጋርደን የሚባል ቦታ ይገኛል። በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ጃፓኖች በጃፓን ባህላዊ መንገድ ሰርተዉ ለጃንሆይ ያበረከቱት መናፈሻ ነዉ። ወንዝ አለዉ የጃፓን ባህላዊ ቤቶችም ይገናሉ ። በጃፓን ባህላዊ መንገድ የተሰራ በጣም የሚያምር ቦታ ነዉ።  የተለያዩ አትክልቶች ሁሉ ያለበት ጋርድን ነዉ። የኛም ዓዉደ ርዕይ ማለት ስዕሎቻችንን ያሳየንበት ቦታ እዚሁ የጃፓን ጋርድን በተባለዉ በፕሬዚደንትዋ መኖርያ ቤት አጠገብ ባለዉ ጋርድን ዉስጥ ነዉ።  ስድስት አዉቶቡስ ማለትም ወደ ሦስት መቶ የሚሆን ሰዉ ነበር በዚሁ የስዕል ትርኢት ላይ የተገኘዉ። የተለያዩ አምባሳደሮች የስዕል አፍቃሪዎች፤ የዉጭ ሃገር ዜጎች ሁሉ ነበሩ። በቤተ-መንግሥቱ ስድስት ወጣት የስዕል ባለሞያዎች ናቸዉ ስዕሎቻቸዉን ያቀረቡት።»    

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

ሰዓሊ ስዩም አያሌዉ ሰዓሊዎችን እና ስራዎቻቸዉን ይዘን በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ኤምባሲዎች እንዲሁም በኢዩ ቤልዩ ቤተ- መንግሥት ስራዎቻችንን በማቅረባችን በተለይ ደግሞ ወጣት ሰዓልያን ለዚህ ተሞክሮ መብቃታቸዉ በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃትን የሚሰጥ በአይነቱ ለመጀመርያ ጊዜ የሆነ ሲል ገልፆታል።

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

«ይህ የስዕል ዓዉደ በአይነቱ የተለየ ነዉ። በርግጥ ለሰባተኛ ዓመት፤ ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደ ቢሆንም ዘንድሮ ለየት የሚያደርገዉ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ይኸዉ ዓዉደ ርዕይ በመካሄዱ ነዉ። በፕሬዚዳንትዋ መኖርያ ቤት ቅጽር ጊቢ ዉስጥ ወጣት ሰዓልያን ስዕሎቻቸዉን ለእይታ በማቅረባቸዉ ለወደፊቱ ከፍተኛ ተስፋ እና ብሩህ የሆነ የወደፊት ስሜት እንዲኖራቸዉ ያደረገ ትልቅ ዝግጅት ነበር። »

በተለያዩ ኤምባሲዎችም ሄዳችሁ ነበር እንዴት ነበር የተቀበሏችሁ?

« አሁን በሃገራችን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ የአርት ማለት የስዕሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ትንሽ ቀዝቀዝ ብሎአል። እንደሚታወቀዉ የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ ሲደክም የስዕል ማለት የአርቱም እንቅስቃሴ ይደክማል። ከዚህ አንፃር ሃገር ዉስጥ ያሉ ዲፕሎማቲኮች እና የሃገር ዉስጥ ባለሃብቶችም ወደዚህ የሥነ-ጥበብ ትዕይንት ማምጣት መቻል ከባድ ነዉ ። ይህን ላደረጉት ያለምንም ክፍያ ምንም አይነት ትርፍ ከኛ ሳይፈልጉ ፤ ይሄንን ስራ እያንቀሳቀሱ የሚገኙት የካክተስ ኮሚኒኬሽን ሰራተኞች፤ በተለይ ደግሞ ዋና ማኔጀሩ ያሲር ባግሬሽ ትልቅ ምስጋና ሊሰጠዉ ይገባል። ኤምባሲዎችን አሳምኖ ሰዓሊዎችን አሰባስቦ ፤ ጥርት ብሎ፤ ጥሩ ሆኖ እንዲካሄድ በማድረግ ያሲር ባግሬሽ የተወጣዉ ሚና ከፍተኛ ነዉ። በቤልጂየም ኤንባሲ በጣም ጥሩ በሆነ ጋርድን ዉስጥ ስዕሎቻችን ካሳየን በኋላ የሄድነዉ ወደ ጀርመን ኤምባሲ ነዉ። ኤምባሲዉ በሩን ክፍት አድርጎ ሰዓሊዎቹ ስዕሎቻቸዉን በፈለጉት መንገድ አስቀምጠዉ ለተጋባዥ እንግዶች አሳይተዋል። በዓዉደርዕዩ የስዕል አፍቃሪዎችና ሰዓሊዉ በነፃነት የተገናኙበት ቦታ ነበር። በኤንባሲዉ ሰዓሊያኑ ስዕሎቻቸዉን ያቀረቡበት ዝግጅት በጣም ግሩም ነበር።  ከዝያ ወደ ፈረንሳይ ኤንባሲ ነዉ የሄድነዉ። ኤምባሲዉ ጊቢዉ እጅግ የሚያምር ነዉ አትክልቱ አበባዉ፤ እና እዛ መሃል ስዕሎቹ ተቀምጠዉ በጣም ግሩም የሆነ እይታን ነበር የፈጠረዉ። ነጮቹ ተመልካቾችም ስዕሎቹን በሚፈልጉት ዋጋ ገዝተዉ ተደስተዉ ነበር፤ አዉደ ርዕዩን  የተመለከቱት። ያገኘናቸዉ ዲፕሎማቶች ሁሉ አድራሻችንን ጠይቀዉ ስቱድዮአችን እንደሚመጡ ቃል ገብተዉልናል። በመጨረሻ ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ በመኖርያ ቤታቸዉ በኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት የመጨረሻ የማሳረግያ ግብዣ ተደርጎ ነበር። የአርት «የስዕል» ማኅበረሰብ ሙዚቀኞች የዲፕሎማቲክ ቤተሰቦች ፤ ባለኃብቶች፤ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ሁሉ እዚህ ቤተ- መንግሥት ሲገኑ ትልቅ መደነቅ ነዉ።  በቤተ -መንግሥቱ የነበረዉ ሕዝብ በሙሉ ትልቅ አድናቆትን ፈጥሮለት ነበር። በጣም ደስታ የፈጠረ ጊዜ ነበር ። ምነዉ ባላለቀ ሁሉ አሰኝቶናል። »

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe
Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

ሥነ ጥበብ፤ ሙዚቃ ፤ሥነ ጽሑፍ ፤ግጥም ትያትርና፤ ፊልም ኅብረተሰቡ አዕምሮዉን የሚያጎለብትበት ፤ ግንዛቤዉን የሚያሰፋበት በመሆኑ በዘርፉ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል የመንግስትም ድጋፍ ያሻናል ያለዉ ሰዓሊ ሰይፉ አበበ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የነበረዉን ቆይታ እንዲ ይተነትናል።   

«ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት እንደደረስን ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘዉዴ አልነበሩም። እኛ ተጠናቀን ከገባን በኋላ ፍተሻዉ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ነበር ወደኛ ወደ እንግዶቻቸዉ የመጡት። በቤተ-መንግሥት ስዕሎቻቸዉን ያቀረቡት ሰዓሊዎች ስድስት ነበሩ። ስዕሉን ያቀረብንበት ቦታዉ በጣም ያምራል። የጃፓን ጋርድን ይባላል። ሲጀመር ቤተ-መንግሥት ያለዉን የጃፓን ጋርደንን አናዉቀዉም ነበር። እዚሁ ጋርድን ጋር ሕይወት ያላቸዉ አንበሶች አሉ። በጣም ብዙ ዛፎች አሉ። የድሮ ቦታ ነዉ። ስንመኘዉ የነበረዉን ቦታን  ነዉ የጎበኘነዉ። ዓዉደርዕዩን ያሳዩት ስድስቱ ሰዓሊዎች በቦታዉ በጣም ተደንቀዉ ነበር። ፕሬዚዳንትዋ ከመጡ እና እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉን በኋላ የቀረበዉን ስዕል ጊዜ ሰጥተዉ እየተዘዋወሩ ተመልክተዋል። እኛም ሥነ-ጥበብ፤  ቤተ-መንግሥት በመግባቱ ምስጋና አቅርበናል። ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ወደፊት በርካታ ኢትዮጵያዉያን ሰዓልያንን ከነስራዎቻቸዉ  ቤተ-መንግሥት እንደምናይ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል። በቤተ- መንግሥት የቀረቡት ስራዎች ወደ ስድሳ ይሆናሉ። ስዕሉን ካዩ በኋላ የሻይ ቡና እንዲሁም የፎቶ መነሳት ፕሮግራምም ነበር።       

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታን ተከትሎ በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ የነበረዉ እንቅስቃሴ ደከም ያለ ቢመስልም ማኅበረሰቡ ስለ ሥነ-ጥበብ ያለዉ ግንዛቤ ተለዉጦአል ። ወጣት ሰዓሊያንም ወደ ሥነ-ጥበቡ ዓለም በመምጣታቸዉ በሃገራችን ሥነ-ጥበብ አብቦአል፤ ፍሬያማ የሚሆንበት ጊዜም ሩቅ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፤ ያለዉ ሰዓሊ ስዩም አያሌዉ በበኩሉ፤  አሁንም የሥነ-ጥበብ ሰዎች ስራዎቻቸዉን የሚያሳዩበት ቦታ የላቸዉም እንደ ሙዚቃ እንደ ትያትር ቤት ሁሉ ሥነ- ጥበብም ማኅበረሰቡ ስዕልን የሚጎበኝበት የግንዛቤ እዉቀቱን የሚያሰፋበት ቤት ጋለሪ መንግሥት ሊቆምለት ይገባል ሲል ተናግሮአል። 

«የኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ዘርፍ አብቦአል ማለት ይቻላል፤ በቅርቡ ደግሞ ፌሪዉን እናያለን የሚል ተስፋ አለኝ። ያለብን ችግር ሰዓሊዉ ስራዎቹን የሚያሳይበት ጋለሪ የለዉም ይህ ችግራችን ሲጓተት የመጣ ነዉ። የስዕል ጋለሪ በአገራችን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ነዉ የሚሰራዉ በመንግስት ደረጃ የለንም። ሙዚቃም ጥበብ ነዉ። ትያትርም ጥበብ ነዉ። ፊልም ጥበብ ነዉ። ስዕልም እንደሌላዉ ሁሉ ጥበብ ነዉ። ትያትር ሙዚቃ ቤትን ብንመለከት በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ብሔራዊ ትያትር ፤ ሃገር ፍቅርን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን መጥቀስ እንችላለን ። ለስዕል ግን ቦታ የለንም።   መንግሥት ይህን ችግራችንን አይቶ ፤ የሕዝብ ጋለሪ የመንግሥት የስዕል ማሳያ ቦታ ቢያቆምልን  ስንል እንጠይቃለን። መንግሥት ይህን ቦታ ቢያቆም ሰዓሊዉ ስዕሉን በማሳየት የሃገር ዉስጥም ሆነ የዉጭ ተመልካቾችን መሳብ ይቻላል።»  

Künstler Tour   Deutschland Äthiopien Belgien Frankreich Botschaft
ምስል DW/S. Abebe

«ገጣሚዉ እንዳለዉ ከሰአሊው ስዕል የሚታየው ቀለም ፤ ውስብስብ አይደለም ዝብርቅርቅ አይደለም ፤ኑሮ ነው ሂወት ነው የኔና ያንተ ዓለም።» ስዕል የትምህርት የታሪክ የእድገት መሰረት ነዉ እና ሰዓልያኑ ስራዎቻችንን ለእይታ የሚያቀርቡበት ቦታ ወይም እንነሱ እንደሚሉት ጋለሪ እንዲከፈትላቸዉ የሚመለከተዉን ክፍል በመጠየቅ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ