1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳይንስና ኅብረተሰብ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 2005

እዚህ ቦን በሚገኘው የቦን ራይን ዚግ ዩኒቨርስቲ > ለተሰኘው ሽልማት በየዓመቱ የመወዳደርያ ሐሳብ በማቅረብ በተለያዩ የዩኒቨርስቲው የትምህርት ክፍሎች የሚገኙ ተወዳዳሪዎችን ያሳትፋል። አሸናፊዎች 5000 ዩሮ ያገኛሉ። የዘንድሮውን ሽልማት የኤሌክትሪካልና ሜካኒካል እንጂኔሪንግ የትምህርት ክፍል መምህራን የሆኑት

https://p.dw.com/p/16Vu1
ቦን ራይን ዚግ ዩኒቨርሲቲ
ቦን ራይን ዚግ ዩኒቨርሲቲምስል Fachhochschule Bonn-Rhein-Sieg
ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት ራይን ወንዝ
ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት ራይን ወንዝምስል DW/@jgayarre

ፕሮፌሰር ኤልቪራ ጃንኾቪስኪ እና ማንፍሬድ ብሬትዝ ወስደዋል። የመወዳደሪያ መሪ ሐሳቡ «በአለም አቀፍ ትብብር ድንበር የለሽ የትምህርት ስልጥናና የእውቀት ልውውጥ ፕሮጀክት» የሚለውን ሲሆን፤ ሁለቱ መምህራን ሽልማቱን ያሸነፉት ከሌሎች ሶስት የዩኒቨርስቲው የትምህርት ክፍሎች ጋር በመወዳደር ነው። ፕሮፌሰር ጃንኮቪክስና እና ፕሮፌሰር ብሬቲዝ ሐረር ከሚገኘው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የእርሻ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ጋር በትብብር ይሰራሉ።

ከሁለት ዓመታት በፊት ፕሮፌሰር ጃንኮቪክስ ምስራቅ ኢትዮጵያ ወደምትገኘው ወደ ሐረር ከተማ ተጉዘው ነበር። እዚያም በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት የተቋቋመውን ኮሌጅ ለመጎብኘት እድል አግኝተዋል፣

«ኢዚያ ሐረር ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ኮሌጅ እንዳለና የመጀመሪያ ድግሪ እንደሚሰጥ እንዲሁም ከሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ሶስቱ የእንጂነሪንግ ዘርፍ ትምህርቶች መሆናቸውን ተረዳን። እኛም ብንሆን የምናስተምረው እንጂነሮችን ነው፣ የኤሌክትሮኒክ እንጂነሮች፣ ሜካኒካል ኢንጂነሮችና የሚዲያ ቴክኒሺያኖችን እናስተምራለን። ከዚያም ፣ አንዳንድ ነገሮችን በዚህ ደረጃና በዩኒቨርስቲያችን <ትምህርት ለልማት> በተባለው መርሃ ግብር ስር እንዴት በትብብር መስራት እንችላለን የሚለውን አሰብንበት።»


ፕሮፌሰር ጃንኮቪክስ ከሰዎች ለሰዎች ድርጅት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ እሳቸው የሚያስተምሩበት የቦን ራይን ዚግ ዩኒቨርስቲ ከበጎ አድራጊው ድርጅት ጋር ለሁለት ዓመት የሚቆይ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በምስራቁ ሐረርጌ ዞን በሚያደርገው እንቅስቃሴ በ1992 ዓ,ም ያቋቋመው የእርሻ ቴክኒክ ስልጠና ማዕከል፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ሀገር-አቀፍ እውቅና አግኝቶ ነው ወደ ኮሌጅነት ያደገው።


ፕሮፌሰር ጃንኮቪክስ በሰዎች ለሰዎች የሚመራው የእርሻ ቴክንክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ እና በቦን ራይን ሲግ ዩኚቨርስቲ መካከል በሚካሄደው የትብብር ፕሮጀክት ያገኙት ሽልማት፣ በጀርመንና በኢትዮጵያ የሚገኙ እንዱስትሮዎችን ለማገናኘትና እውቀትን ለመለዋወጥ ይረዳል ይላሉ፣

«እዚህ ያሉ የጀርመን ተማሪዎች ታዳጊ ሀገራት ውስጥ የሥራ ልምድ ለመቀሰምና በትብብር ሥራ ማዕቀፍ ስር እዚያ ኢትዮጵያ ካሉ ተማሪዎችና መምህራን ጋር ለመስራትና፣ በተመሳሳይ ጊዜ አንዳችን ከሌላው ለመማማር ነው። ያም ማለት የጀርመን ተማሪዎች ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው፣ ኢትዮጵያውያንም ከጀርመን አቻዎቻቸው ይማማራሉ።»
«ሌላው መልካም ጉዳይ፣ እዚህ ያሉ እንዱስትሪዎች ተማሪዎችን ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከኢትዮጵያ ተማሪዎችና መምህራን በጋራ እንዲሰሩ እያስተባበርን ነው። እዚህ ያሉ እንዱስትሪዎች እዚያ ካሉ ጋር ትስስር ፈጥረው እንዲሰሩ እያደረግን ነው።»


እነኚ በጀርመን የሚገኙ እንዱስትሪዎች ከዚህ ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ። ለምሳሌ GKL የተባለ የእርሻ ምርቶችን የሚያመርት ድርጅት አንዱ ነው። በኢንዱስትሮዎቹ የተከናወኑ የምርምር ውጤቶችን ተማሪዎቹ በተግባር እንዲያዩት ይበረታታሉ ይላሉ የፕሮፈሰር ጃንኮቪስኪ የምርምር ጓድ ማንፍሬድ ብሬትዝ፣

«እዚህ እኛ አከባቢ ያሉ እንዱስትሪዎች ያደረጉትን አዳዲስ ምርምሮች ተማሪዎቻችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው በመሄድ እዚያ ካሉ መምህራንና ተማሪዎች ጋር ይዋያዩበታል።»

ፕሮፈሰር ጃንኮዊስኪ ከሳምንታት በፊት ዲዳክቲክስ የሚባል የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን በሐረሩ የእርሻ ቴክንክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የሚያስተምሩ መምህራንን ለማስተማር ተጉዘው ነበር፣

«የመምህራኖቹ ታታሪነትና የመማር አቅም በጣም ደስ አሰኝቶኛል። የነገርኳቸውን በደንብ ይዘውታል። እነሱም በጣም ደስ ብሏቸዋል። ከኔ የሰሙትን፣ ተማሪዎቻቸውን ሲያስተምሩ እንደሚጠቀሙበትም ነግረውኛል።»


በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የተቋቋመና ከነ ፕሮፈሰር ጃንኮቪስኪ ጋር በትብብር የሚሰራው የሐረር የእርሻ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ አራት ዋና የትምህርት ክፍሎች አሉት። ከአራቱ ውስጥ አንዱ የማኑፋክቸሪንግ የትምህርት ክፍል ሲሆን ተስፋለም ማርቆስ የዚህ ትምህርት ክፍል ተማሪ ነው። ተስፋለም በኮሌጁ የሚሰጡ በተግባር የታገዘና ትምህርትና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች መኖር እንዳስደሰተው ይናገራል።

«ደስ የሚል ነገር ነው ያላቸው። በተለይ ማኑፋክቸሪንግ ዲፓርትመንት ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ዩኒቨርስቲ የማናገኛቸውን ማሺነሪዎች፣ አንዳንድ ተማሪዎች በ{ወረቀት} የሚያውቁትን ማሺን እኛ ደግሞ {የበለጠ በተግባር እየተማርንበት} ነው የምንወጣው። እና በጣም ደስ ብሎኛል።»

ተስፋለም ወደ ፊት ትምህርቱን ሲጨርስ ትልቅ ተስፋ እንደሚሰማው ይናገራል፣
«ወደ ሥራ ዓለም ስገባ፣ ከ{ውድድር} አንጻር፣ ከሁለት ዓመት በፊት {ከኔ ቀድሞ የተመረቁ ተማሪዎች} ነበሩና፤ ከነሱ አኳያ ብነግርህ፣ ሳይመረቁ, ትምህርት ለመጭረስ አንድ ወር { } ሲቀራቸው የተለያዩ {መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች} እዚህ መጥተው {አመልክተው} የወሰዷቸው። የተማርነው ነገር ነው {የበለጠ} ተፈላጊዎች ያደረገን ነገር።»

ከሐረሩ የእርሻ ቴክኖሎጂና ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር ለሚሰሩት የትብብር ሥራ ከቦን ራይን ዚግ ሽልማት ያገኙት ፕሮፌሰር ኤልቪራ ጃንኮቪስኪና ማንፍሬድ ብሬትዝ ወደ ፊት የጀመሩትን ሥራ ጠንክረው እንደሚቀጥሉበት ይናገራሉ፣

«ከተማሪዎቹና መምህራኑ ጋር ሌሎች ፕሮጀክቶችን የምንስራበት መንገዶችን መፈለጋችንን እንቀጥልበታለን። የኛን እና የእርሻ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ሥራዎችን እንዲደግፉ በዚህ ባከባቢያችን የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትዎችን ማነጋገራችንን እንቀጥልበታለን። የጀመርነውን የማስተማር ሥራም እንዲሁ።

የእርሻ ኮሌጁ የበላይ አመራር ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ጀርመን በመምጣት ተማሪዎችን ለምርምር ማሰራት የሚፈልጉ የተለያዩ እንዱስትሪ ተወካዮችን በማነጋገር ልምድ ቀስመው ተመልሰዋል። በቅርቡ አንድ የቦን ራይን ዚግ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለኢንጂነሪንግ የልምምድ ሥራ ወደ ሐረር ተጉዟል። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሌሎች ሁለት ተማሪዎች ደግሞ የመመረቂያ ስራዎቻቸውን ለመስራት ወደ ኮሌጁ ይጓዛሉ። ፕሮፈሰር ጃንኮቪስክና ብሬቲዝ የቦን ራይን ዚግ ሽልማት የዚህ ዓመት ተሸላሚዎች የሆኑት ለዚህ ዓይነቱ የልምድ ልውውጥ ሐሳብ ነው።

ገመቹ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ



ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ