1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሳዴክ» እና የ25 ዓመቱ ስራው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 2009

የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ፣ በምህጻሩ «ሳዴክ» ከተመሰረተ በዚህ በያዝነው ሳምንት 25 ዓመት ሆነው። መንበሩን በቦትስዋና መዲና ጋቦሮን ያደረገው ይኸው ድርጅት በ15ቱ አባል ሀገራት መካከል ማህበራዊ ኤኮኖሚያ ትብብርን፣ እንዲሁም፣ ፖለቲካዊ  ውኅደትን እና የፀጥታ ትብብርን የመፍጠር ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ነው።

https://p.dw.com/p/2iTwb
Logo von SADC

«ሳዴክ» ሲመሰረት ያስቀመጠውን ዓላማ ማሳካቱን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

በውሁዳኑ ነጮች አገዛዝ፣ በአፓርታይድ  ስር በነበረችው ጠንካራ የኤኮኖሚ ኃያል መንግሥት ደቡብ አፍሪቃ አንፃር  በጎርጎሪዮሳዊው 1980 ዓም በስድስት የአካባቢው ሀገራት፣ ማለትም ፣  በአንጎላ፣ቦትስዋና፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛንያ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ  የተቋቋመውን እና አሳሪ ባህርይ ያልነበረውን  የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ትብብር ጉባዔ፣ በምህጻሩ « ኤስ ኤ ዲ ሲ ሲ»ን ተክቷል። የ«ኤስ ዲ ሲ ሲ» መስራች ሀገራት በዚያን ጊዜ ዓላማቸው በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ ላይ  ብዙም ጥገኛ ላለመሆን እና በአገሮቻቸውም ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት ለማስፈን ነበር። አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ፣ ስዋዚላንድ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ፣ ሞሪሽየስ፣ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር ፣ ሴይሸልስ፣ ታንዛንያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ ፣ ደቡብ አፍሪቃን በአባልነት በመያዝ ነሀሴ፣ 1992 ዓም በአዲስ መልክ ተቀናጅቶ የተመሰረተው «ሳዴክ» 25ኛውን የምሥረታ ዓመት ባከበረበት በአሁኑ ጊዜ አካባቢውን  አዘውትሮ የሚያጠቃውን ድርቅ እና በዚያም የሚታየውን ድህነት ለመታገል ተጨባጭ ርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።
በያመቱ በአባል ሀገራት መካከል የሚዘዋወረው የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ ሊቀ መንበርነት ስልጣን ደቡብ አፍሪቃ  በዛሬው ዕለት በፕሪቶርያ ከተማ በተካሄደው ዓመታዊው የ«ሳዴክ» ጉባዔ  ላይ ከስዋዚላንድ ንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳይ ተረክባለች። ትንሾቹ የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት የድርጅቱን ዓላማ በማሳካቱ ረገድ  ከትልቋ ደቡብ አፍሪቃ ሊቀ መንበርነት ስልጣን ብዙ ይጠብቃሉ፣ ግን፣ ይህን ሚና መጫወቱ ለደቡብ አፍሪቃ ቀላል እንደማይሆን የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ባልደረባ የሆኑት ደቡብ አፍሪቃዊቷ ታሊታ ቤርትልስማን ስኮት ገልጸዋል።
«   ደቡብ አፍሪቃ ለአካባቢው  ሀገራት ሁሌም አንድም የትልቅ ወንድምነትን፣ የመሪነትን ሚና ስትጫወት ቆይታለች  ወይም ሌሎች በተለይም ከ«ሳዴክ» በፊት በነበረው ድርጅት ውስጥ መሪነቱን ይዘው የቆዩትን ሀገራትን ላለማስቀየም እያለች ቁጥብነትን መርጣለች። ከዚህ ሌላም፣ ደቡብ አፍሪቃ በአካባቢው የንግድ ውኅደት እንዲፈጠር ለጋሽ ሀገራት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ሀሳብ ደጋፊ አልነበረችም።  እንደሚታወቀው፣ ደቡብ አፍሪቃ ከአራት የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት፣ ማለትም፣ ከስዋዚላንድ፣ ቦትስዋና፣ ሌሶቶ እና ናሚቢያ ጋር ነፃ የንግድ ዘጠና አቋቁማለች። »
የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት ከግብ ለማድረሱ ያስቀመጡትን በአካባቢያቸው በኤኮኖሚያዊ ልማት የሚደገፍ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና መልካም አስተዳደር የመፍጠር ዓላማ እውን ማድረጉ ቀላል አይሆንም። የ«ሳዴክ አባል ሀራት በጎርጎሪዮሳዊው 2008 ዓም ነፃ የንግድ ስምምነት ውል ተፈራርመዋል። ያም ቢሆን ግን፣ እንደ ቤርትልስማን ስኮት አስተያየት፣ በኤኮኖሚያዊው ውኅደት አኳያ ያን ያህል መሻሻል እንዳልታየ እና አንዳንድ ሀገራት አሁንም በተናጠል ነው የሚሰሩት። ይህ ሁኔታም በደቡብ አፍሪቃ የድርጅቱ ፕሬዚደንትነት ስልጣን ዘመንም የሚለወጥ አይሆንም።
« «ሳዴክ» በቅርቡ አንድ ነፃ የንግድ ቀጠና ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፣ በዚህ ሀሳብ ላይ ስምምነት የለም። ከኤኮኖሚያዊው ውኅደት በፊት በአካባቢው ኢንዱስትሪያዊነት እና መሰረተ ልማቱ ሊስፋፋ  ይገባል በሚለው ሀሳብ ላይ ግን ስምምነት አለ። »
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥትም በ«ሳዴክ» ፕሬዚደንትነት ዘመኑ በተለይ ትኩረቱን በአካባቢው ኢንዱስትሪያዊነት እና መሰረተ ልማቱ ሊስፋፋ  ይገባል የሚለውን ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየሩ ላይ ለማሳረፍ ይፈልጋል። ማዕድን፣ የመድሀኒት ምርት ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት መስጫን ለመሳሰሉ ድንበር ባሻገር ዘርፎች ገባለሀብቶችን ለመሳብ ለመስራት አቅዷል። የጋራ የኮሬንቲ ገበያ ከተቋቋመ ሰንበት ብሏል። «ፓወር ፑል» በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የጋራው የኤሌክትሪክ  ኃይል ገበያ አማካኝነት የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት የኃይል ምንጭ ልውውጥ ያደርጋሉ። በግዙፎቹ የዱር አራዊት ፓርኮች መካከል የነበረው ድንበርም የተነሳ ሲሆን፣ ለፓርኮቹ ጎብኚዎች አንድ ዓይነት ቪዛ መስጠት ተጀምሯል።  
ይሁን እንጂ፣ በንግዱ ዘርፍ በ«ሳዴክ» አባል ሀገራት መካከል ግንኙነቱ ንዑስ መሆኑ በአካባቢው ላይ ችግር እንደደቀነ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ተንታኝ ወይዘሮ ታሊታ ቤርትልስማን ስኮት በማስረዳት፣ አባል ሀገራት  በጋራ ሊደርሱት ስለሚፈልጉት ጉዳይ በጥሞና እንዲያስቡበት ሀሳብ አቅርበዋል። የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት መንግሥታት ከውህደቱ በፊት በዚሁ ረገድ ብዙ ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።
« ኤኮኖሚያዊው ውኅደት ከመፈጠሩ በፊትም አባል ሀገራት በመካከላቸው ንግዱን ማሳደግ መቻል አለባቸው። መዘርዝሮች እንደሚያሳዩት፣ አባል ሀገራት እርስ በርስ የሚያካሂዱት ንግድ ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው። ብዙዎቹ  ከቻይና፣ ከብሪክስ ሀገራት ወይም ከቀድሞ ቅኝ ገዢ ሀገራት ጋር ነው ንግዱን የሚያካሂዱት። የእርስ በርሱ ንግድ ግን በጣም ችግር ይታይበታል። » 
የጀርመናውያኑ የደቡባዊ አፍሪቃ የኢንዱስትሪ እና ንግድ ምክር ቤት ኃላፊ ማቲያስ ቦድንበርግ እንደሚሉት፣ በአባል ሀገራት መካከል የሚኖረውን ትብብር በተመለከተ አሳሪ ባህርይ ይዞ የተቋቋመው «ሳዴክ» ከአንድ ሩብ ምዕተ ዓመት በፊት ይዞት የተነሳውን ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውኅደት ገና እውን አላደረገም።
« እርግጥ፣ «ሳዴክ» ባጠቃላይ እንደ እያንዳንዷ አባል ሀገሩ አድጓል። ግን፣ ያስቀመጠው ዓላማ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ለአባል ሀገራት ፈታኝ ሆኗል። »
በ«ሳዴክ» አባል ሀገራት መካከል ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም፣ በአባል ሀገራት መካከል እና ከአውሮጳ ህብረት  ጋር በ2016 ዓም የተፈረመው የንግድ ስምምነቱ ጭምር  ተጠናክሯል። ይሁንና፣ የፖለቲካ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ አስማሚ ሀሳብ ላይ መድረስ ለአባል ሀገራቱ አዳጋች መሆኑን ነው ቦድንበርግ የገለጹት። ይህ በተለይ በዚምባብዌ  ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ የረጅም ዓመታት የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ለማግባባት ብዙ ጊዜ የተደረጉ ሙከራዎች በከሸፉበት ድርጊት ታይቷል። ይህም የ «ሳዴክ»ን ደካማነት የሚጠቁም ነው በሚል አንዳንዶች ቢተቹም፣ ቦድንበርግ ግን ይህን አስተሳሰብ እንደማይጋሩት ነው የሚናገሩት።
« «ሳዴክ» አቅም የሌለው ድርጅት ነው አልልም። ከ«ሳዴክ» በፊት የነበረውን ድርጅት መስራች ሀገራት ፍላጎትን /ጥቅምን የሚያስቀድም ነው።  ለምሳሌ፣ ዚምባብዌ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ አንፃር የተጫወተችው ሚና  በድርጅቱ ውስጥ ሁሌ ትልቅ ቦታ እንደያዘ ይገኛል። ይህም በዚችው ሀገር አኳያ በሚከተለው ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል። »
የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት  ን በሚመለከት የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት የሽምግልና ጥረቶች የተሳኩ ነበሩ። ለምሳሌ፣ በንዑሷ ሌሶቶ በ2014 ዓም የተሞከረ መፈንቅለ መንግሥት እንዳይካሄድ አከላክሏል። በማዳጋስካር የቀድሞው ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና በ2009 ዓም በጦር ኃይሉ እና በተቃዋሚው ቡድን መሪ አንድሬይ ራዦሊን በኃይል ከስልጣናቸው እንዲለቁ በተገደዱበት ጊዜ ድርጅቱ ለተወሰነ ጊዜ ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም። 
የሰብዓዊ መብት ጉዳይን በተመለከተ «ሳዴክ» ሊያደርገው የሚገባ ብዙ ነገር እንዳለ ያመለከቱት ቦድንበርግ የድርጅቱ ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ሚናው እጅግ ንዑስ መሆኑን ገልጸዋል። የፍርድ ቤቱ ስልጣን በ2014 ዓም ለውጥ ከተደረገበት ወዲህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ ሊያቀርቡ የሚችሉት የአባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር ወይም መራሕያነ መንግሥት ብቻ ናቸው። ይህ የአካባቢውን መረጋጋት እና ሰላም ስጋት ላይ የሚጥል ነው በሚል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዜጎችም በፍርድ ቤቱ ክስ ማቅረብ ይችሉበት የነበረው አሰራር እንዲመለስ መጠየቃቸውን ይዘዋል።
አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺኮቭስኪ

Simbabwe SADC Gipfel in Harare - Robert Mugabe
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi
Jacob Zuma
ምስል AFP/Getty Images

ልደት አበበ