1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመሀንነታቸው የሚገለሉ ኬንያውያን

ዓርብ፣ የካቲት 30 2010

ስራ ለማግኘት ብላ የአሸባብን ቡድን የተቀላቀለች አንዲት ወጣት የደረሰባትን በደል እና ልጅ ባለመውለዳቸው ከማህበረሰቡ የሚገለሉ ኬንያዉያን ሴቶች...

https://p.dw.com/p/2sKz4
Afrika Symbolbild junge Frau mit Kind Masai Frau mit Kind
ምስል Fotolia/Jenja

 

በመሀንነታቸው የሚገለሉ ኬንያውያን

ጀዲሱ ሳው ዛሬ 39 ዓመቷ ነው። ለወላጆቿ ብቸኛ ልጅ ነች። ወላጆቿ በሞት ሲለይዋት ህይወቷን ለማስተዳደር በአንድ ሆቴል ውስጥ ተቀጥራ መስራት ነበረባት።  በ14 ዓመቷ ትዳር ብትመሰርትም መሀንነቷ ካገባች ብዙም ሳትቆይ ፈተና ሆኗታል። « እንደተጋባን ባለቤቴም ሆነ ወላጆቹ ይወዱኝ ነበር። ከተጋባን ከሁለት ዓመታት በኋላ ባለቤቴ ልጅ እፈልጋለሁ ይለኝ ጀመር። ችግሩ ብዙ ጊዜ ማህፀኔ ጋር ያመኝ ነበር። ርዳታም እንዳገኝ የምነግረው ሰው አልነበረኝም። ሌሊት ጠጥቶ ሲገባ ይቀሰቅሰኝኛ ልጅ እፈልጋለሁ ይለኝ ነበር። ወላጆቹም ልጃቸው ፍሬያማ ካልሆነች ሴት ጋር እንዲኖር እንደማይፈልጉ ይናገሩ ጀመር። እንደዛም ሆኖ ባለቤቴ መሬት ላይ ቤት ለመስራት ፍየሎች እና ከብቶችን ለማርባት ወሰንኩ። ወላጅ አልባ ስለሆንኩ እዛው ብቆይ እና ብሞት ይሻለኛል ብዬ ወሰንኩ።
ይሁንና የጀዲሳ ችግር በዚህ አላበቃም። የባለቤቷ ወላጆች ሁለቱም ከልጃቸው ጋር እንድትለያይ ጫና ያደርጉባት ጀመር።  « በትዳር ሶስት አመት ተኩል እንደቆየሁ የባለበቴ እናት ችግር ይፈጥሩ ጀመር። እድሜሽ ገፍቷል ይሉኝ ነበር። እና በእድሜ የምትመጥነውን እንዲያገባ ቦታ እንድለቅ ይነግሩኝ ጀመር። ለመንኳቸው ግን አልተቀበሉኝም። በባህላችን ፍፁም የማይባሉ ነገሮችን ይሉኝ ጀመር። በየምሽቱ የእኔን ስሜት የሚነኩ ዘፈኞች ያንጎራጉሩ ጀመር። መጥፎ መንፈስ እንዳለብኝ እና ቤታቸው መቆየት እንደማልችል።»
በጎርጎሮሳዊው 2004ዓም የጀዲሳ ባለቤት ሁለተኛ ሚስት አገባ። እሷም ወዲያው አርግዛ ወለደች። « ሁለተኛ ባለቤቱ ስታረግዝ የባለቤቴ ቤተሰቦች ለቅቄ እንድሄድ አሳሰቡኝ። እሷም የስድስት ወር እርጉዝ እንዳለች በሰፈር ሽማግሌሎች እሷ በሰላም እንድትገላገል መተቴን እንድተው ነገሩኝ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እሷ አልጋዬ ላይ እየተኛች ነው። በ 2005 ወለደች። እኔ ግን ልጁን በአይኔ እንዳይ አልተፈቀደልኝም። በመጥፎ መንፈስ ትገይዋለሽ በሚል። የዛን ሌሊት ባለቤቴ ደበደበኝ። በማጭድ አንገቴን ቆረጠኝ። ድረሱልኝ የምለው አባት ወንድም እህት አልነበረኝም። አንገቴ ላይ በማጭዱ የተጎዳሁት ትልቅ ጠባሳ አሁንም አለ።» 
ጀዲሱ ብቸኛዋ ሴት አይደለችም። እሷ አሁን ምትኖርበት የሴቶች ተቋም 30 ሴቶች ይኖሯሉ። ተቋሙ የተመሰረተው በ2003 ዓም ነው።  ዳርላን ሩኪ ሚራንጋ ሚሽን የተሰኘውን ይህን ተቋም የመሰረቱት ዳርላን ሩኪ፣ ሴቶቹ ተመልሰው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲዋኃዱ እና አነስተኛ ንግድ እንዲጀምሩ ያበረታታሉ። 
« የተለያየ ችግር ያለቸው ብዙ ሰዎች እኔ ጋር ይመጡ ነበር። ያኔ ይህንን ተቋም ለመመስረት ወሰንኩ፤ የሚቆዩበት ፤ የሚኖሩበት እነሱን ማማከር የምችልበት እድል የማገኝበት። ምንም እንኳን መከራን ቢያሳልፉም ህይወት መቀጠል አለበት። እዚህ ሲመጡ ህይወት ተስፋ ቢስ ነበር አሁን ግን ጤነኛ እና የተባረኩ ናቸው።»
የኬንያ ኪሱሙ ናድጎ የድሆች መኖሪያ ሰፈር ውስጥ ጄን አቲኖ ይኖራሉ። ዛሬ 59 ዓመታቸው ነው። ባለቤታቸው በህይወት የሉም። እሳቸውም እንደ ጀዲሳ መሀን ነበሩ። የሳቸው ታሪክ ግን ለየት ይላል። ባለቤታቸው ከትዳራቸው አላባረሯቸውም ወይም ሌላ ሴት አላገቡም። የባላቸውም ወላጆች አላገለሏቸውም ይሁንና ሰፊው ማህበረሰብ እና አንዳንድ የባለቤታቸው ዘመዶች ያገሏቸው ነበር።  « ሰዎች የሚጠብቁትን ካላሟላሽ ሁል ጊዜ ይጨቁኑሻል። ብዙ መጥፎ ነገሮች መስማት ነበረብኝ። ደካማ ከሆንሽ ጥለሽ ትሸሺያለሽ ጠንካራ ከሆንሽ ግን እግዚያንሔርን እያመሰገንሽ ለመቆየት አቅሙ ይኖርሻል።ባለቤቴ ሲያርፍ ሌላ ማግባት አልፈለኩም። ብቻዬን መሆን እና ማርጀት ነው የወሰንኩት።»
ጄን ያማቸው ነበር ይሁንና መሀን መሆን አለመሆናቸውን ተመርምረው አያውቁም። ዶክተር ቻርለስ ሞምባሳ ውስጥ የስነ ልቦና ሀኪም ናቸው። መሀንነት የወንዱም ችግር ሊሆን እንደሚችል በመግለፅ የምክር አገልግሎት ይለግሳሉ። « አብዛኛውን ጊዜ ምርመራ ስናካሄድ ሴቶቹ ፍቃደኞች ናቸው። ወንዶቹ ግን አስቸጋሪ ናቸው። ምክንያቱም ሴቷ ፍሬያማ ሆና ችግሩ ከወንዱ ሊሆን ይችላል። ያንን መቀበል ደግሞ ከጣም ከባድ ነው።» 
የመውለድ ችግር የሚገጥማቸው ሰዎች በዘመናዊ መንገድ የሚታገዙበት መንገዶች አሉ። ዶክተር ጆን ቻሚያ የማህፀን ሀኪም ናቸው። « ሞምባሳ ውስጥ መሀኖች ከ 15 እስከ 20 ከመቶ ያክል ናቸው። ከነዚህም ሴቶቹ 35 ከመቶ ቢሆኑ ነው። ወንዶቹ ደግሞ 25 ከመቶ ናቸው። ሞምባሳ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ችግር የማህፀን ቧንቧ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መዘጋት ነው። ሌላው ደግሞ የሆርሞን ችግር ነው። » ህክምናው ግን በኬንያ ገጠሩ ክፍል ለሚገኙ ሰዎች ሩቅ እና ውድ ነው። 

Symbolbild Samenspende
ምስል picture-alliance/dpa
Silhouette eines Toposa-Jungen, Toposa boy, silhouette
ምስል picture alliance/dpa/blickwinkel/W. Dolder

 

 ስራ ለማግኘት ብላ የአሸባብን ቡድን የተቀላቀለችው ወጣት

 

ራዲያ ማምቦ 27 ዓመቷ ነው። አሸባብ ጋር እያለች ትለብሰው በነበረው ጥቁር ቡርቃ ፋንታ ዛሬ አበባ ያለበት ድሪዓ ለብሳለች። ከሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ አምልጣ ወደ ኬንያ ከተመለሰች ገና ሁለት ወሯ ነው። ኬንያ እስክትገባ  ድረስ ረጅም መንገድ በእግሯ መጓዝ ነበረባት።  ራዲያ ከአምስት ዓመት በፊት ቡድኑን የተቀላቀለችው፤ ሀገሯ ስራ ባለማግኘቷ ነበር።
« አባቴን የሚያውቁ ሰው ናቸው ወደእዛ የወሰደኝ። አብረሽን ወደ ሶማሊያ ሂጂ እዛ ስራ አለ አሉኝ። እኔም በምግብ አብሳይነት ለመስራት ተስማማሁ። ይሁንና እዛ ስደርስ  ረዥም ጢም ያላቸው አረቦች ነበር የጠበቁኝ። እዛ እንደደረስኩ ማምለጥ እንዳልችል አድርገው በሩን ዘገቡኝ።»

Somalia Al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/F. A. Warsameh


ራዲያ ከደረሰባት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሌላ  ገለዋ ላይ ያለው ጠባሳ የደረሰባትን ድብደባ መስካሪ ነው። ለአምስት ዓመታት የተደፈረችው ወጣት ሞምባሳ ከገባች በኋላ ባደረገችው የጤና ምርመራ የ HIV ቫይረስ በደሟ እንደሚገኝ አውቃለች።« የወሰዱኝ ሰዎች ጥሩ ሰዎች አልነበሩም። ደብድበውኛል፣ አስፈራርተውኛል። 60 000 የኬንያ ሺሊንግ ደሞዝ እንደሚከፈለኝ ነበር የነገሩኝ። በመጨረሻ ግን አንድም ሳንቲም አልሰጡኝም።  የወሲብ ባርያ ነበር ያደረጉኝ። የፈለገ ሁሉ ከእኔ ጋር ካለኮንዶም ወሲብ ይፈፅም ነበር። ይገርፉኝ ነበር። ከዛ ሳመልጥ ሰውነቴ ሁሉ ቁስል ነበር። ለማምለጥ የቻልኩት አንድ ቀን ለበርካታ እንግዶች በር የመክፈት እድል ባገኘሁበት ጊዜ ነበር። ያኔ ሮጬ ወደ ጫካ ጠፋሁ። እዛ ተሸሽጌ ከቆየሁ በኋላ ወደቤት የሚወስደኝ መንገድ የትኛው እንደሆነ የሚያሳየኝ ሰው አገኘሁ።  


ራዲያ ብቻዋን አይደለችም። በርካታ ወጣት ሴቶች እና ልጃገረዶች በሶማሊያው አማፂ ቡድን ተደብድበዋል፣ ስራ ወይም ትዳር እናገኛለን ብለው ተታለዋል። የኬንያ ብሔራዊ የፀረ ሽብር ኃላፊ ማርቲን ኪማኒ እንደ ራዲያ አይነት ታሪክ በመበራከቱ የሀገራቸው መንግሥት ሁኔታውን ለመቀየር እየሰራ እንደሆነ ይናገራሉ።« የኬንያ መንግሥት በአሸባብ ታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን ቀንሷል። ነገር ግን አሸባብን ተቀላቅለው የነበሩ ኬንያውያን ካመለጡ፣ ወይም ጠፍተው ከተመለሱትም በኋላ አንድ አንድ ጊዜ የአሸባሪው ቡድን የጥቃት ሰለባ ይሆናሉ። እነዚህ ተመላሾችን መልሰው ከማህበረሰባቸው ጋር ተቀላቅለው መኖር እንዲችሉ እንተባበራቸዋለን። አንዳንዶች ደግሞ ወደ ኬንያ የሚመለሱት የሽብር ጥቃት አቅደው ነው። ይህንን ከደረስንበት ደግሞ ምህረት አናደርግላቸውም።»
በ2015 ዓም የኬንያ መንግሥት የሽብር ቡድኑን ተቀላቅለው ለነበሩ በርካታ ወጣቶች ምህረት አድርጎ ከማህበረሰቡ ጋር አቀላቅሏል። ነገር ግን በርካታ ተመላሾች መመለሳቸውን ለባለስልጣናት አያስታውቁም። ይህም ቡድኑ ኬንያ ውስጥ ባለው መረብ ተጠቂ ያደርጋናል ብለው ስለሚሰጉ ነው።
ምንም እንኳን በአሁን ሰዓት ምን ያህል ሴቶች ወይም ልጃ ገረዶች የአሸባብን ቡድን ተቀላቅለው እንደሚገኙ በትክክል የሚገልፅ አሀዝ ባይኖርም ሞምባሳ  እንደ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ቡድን ገለፃ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ነው። «ታጣቂ ቡድኑ ሞምባሳ ውስጥ ባለፉት አስር አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። አንዳንድ ተቀጣሪዎች ሲሞቱ ሌሎች እድል ብሏቸው ተመልሰው ወደዚህ መጥተዋል። ብሔራዊ መንግስታችን ለተመላሾቹ ይቅርታ አድርጓል። አንዳንዶች ግን በሚስጥር ስለተመለሱ ትክክለኛ የሆነ ቁጥር የለንም። አብዛኞቹ ጥናቶቻችን የተመረኮዙት በዓይን እማኞች እና ልጆቻቸው ሲጠፉባቸው ባሳወቁን ወላጆች መረጃ ላይ ተመርኩዞ ነው። ስለሆነም ከ 10 000 በላይ ወጣቶች ሚሊሺያውን ተቀላቅለዋል ብለን እንገምታለን። ከሞምባሳ ብቻ ከ 2000 በላይ ወጣቶች በዚህ ምክንያት ሳናጣ አንቀርም።» ይላሉ የኬንያ ማህበረሰብ ርዳታ ማዕከል ዋና ዳሬክተር ፊሊስ ሙአማ።
 

Kenia - Muslime in Mombasa
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gebert

ዲያና ዋንዮኒ/ ልደት አበበ 
ሂሩት መለሰ