1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12 2006

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። ድርጅቱ አያይዞም በጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም 65 በመቶ የሚሆኑ የካንሰር ታማሚ በአዳጊና በማደግ ላይ በሚገኙ ሃገራት እንደሚገኝ ከወዲሁ ጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/1A4dw
ምስል Fotolia/Forgiss

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ዉስጥ የካንሰር ህሙማንን ቁጥር በበቂ ሁኔታ የመዘገበ መረጃ ባይገኝም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ዉስጥ የካንሰር ህሙማን ቁጥር ከወትሮዉ እየጨመረ መሄዱን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማቲዎስ አሰፋ፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በተቋቋመ የካንሰር ምዝገባ ስልት አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኙ ህሙማንን ለመመዝገብ መሞከሩን ያስረዳሉ። ከተመዘገቡት ታማሚዎች ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ሴቶች አንድ ሶስተኛዉ ደግሞ ወንዶች መሆናቸዉን ዶክተር ማቲዎስ ገልጸዉልናል። የሴቶቹ ቁጥር የበረከተበት ምክንያትም አብዛኞቹ የጡት፤ ገሚሱም የማህጸን ጫፍ ካንሰር ተጠቂዎች በመሆናቸዉ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለካንሰር የሚዳርጉ ምክንያቶች በዉል ይህ ነዉ ተብለዉ ባይገደቡም በተለያዩ መንስኤዎች ተያያዥነት ሊከሰት እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ይስማማሉ። የጡት ካንሰርን በሚመለከት በተለይ ለሴቶች ግን ዋነኛ መነሻ ምክንያት አለ።

የጡት መያዢያዎችም ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ መሆናቸዉን አንዳንድ ጤናነክ ጽሑፎች ይጠቁማሉ ስል የጠየኳቸዉ ዶክተር ማቲዎስ የጡት ካንሰር መንስኤ ከዚህ ጋ ስለመገናኘቱ የሚያረጋግጥ መረጃ እንደሌለ አመልክተዋል።

Gentest zu Brustkrebs bei Myriad Genetics Inc
ምስል AP

የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር በፊት ከነበረዉ እየጨመረ መሄዱ እንዳለ ሆኖ የህክምናዉ ሁኔታ ግን አለመስፋፋቱ ነዉ የሚገለጸዉ። ህመሙን ለማወቅ የሚረዱ የምርመራ መሳሪዎች በአብዛኛዉ የሀገሪቱ ክፍል እንደሌሉምም ዶክተር ማቲዎስ ገልጸዋል። ህክምናዉም ያለዉ የማስተማር ተግባር የሚያከናዉኑ ትላልቅ የሆስፒታል ተቋማት በሚገኙባቸዉ አካባቢዎች ብቻ ነዉ። በሽታቸዉ ካንሰር መሆኑ ታዉቆ የጨረር ህክምና የሚያስፈልጋቸዉ ወገኖች ለወራት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።

በየጊዜዉ ከሥራ ተሞክሮ ከሚገጥማቸዉ አኳያ ዶክተር ማቲዎስ አሰፋ ያስተዋሉት በአብዛኛዉ ስለበሽታዉ ያለዉ ግንዛቤ እጅግ ዉሱን መሆኑን ነዉ። ከዚህም ሌላ ህክምናዉን ያገኙ ወገኖች በቦታ ርቀትና የመሳሰሉ ምክንያቶች ተመልሰዉ ሁኔታዉን ለመከታተል ወደሃኪም አለመሄዳቸዉም ተጨማሪ ችግር መሆኑን ነዉ ባለሙያዉ ያመለከቱት።

እንደዶክተር ማቲዎስ ያሉትን የህክምና ባለሙያዎች ቢጠየቁልን የምትሏቸዉ ጥያቄዎች አሏችሁ? ጤናንና የአካባቢ ጥበቃን የሚመለከት አስተያየት ለዝግጅት ክፍላችን በኢሜል፤ በSMSም ሆነ በደብዳቤ መላክ፤ እንዲሁም በፌስ ቡክ ገጻችን ላይ ማስፈር ትችላላችሁ። እናስተናግዳለን፤

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ