1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ኖቤል ሽልማቱ ኤርትራዊያን ምን አሉ?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2012

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ መሆናቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን ሁሉ አቀፍ ግንኙነት ከተቀዛቀዘበት አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምደዋል የሚል እምነት እንዳላቸው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/3Ui9y
Äthiopien President Somalia Mohammed Abdulahi, Eritreas Präsident Isayas Afeworki, Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ስለ ዐቢይ ሽልማት የኤርትራውያን አስተያየት

የኖቤል ሽልማቱ ዐቢይ አህመድ በሀገራቸው እና በሌሎች የጎረቤት ሃገራት ላከናወኑት ተግባር እውቅና በመስጠቱ እንደሚስማሙ ሆኖም ግን ከኤርትራ ጋር ሰላም በመምጣቱ የሚል መካተቱ ተገቢ አይደለም ይላሉ በእንግሊዝ የኤርትራዊያን የሰብአዊ መብት ተሟጋች። በጀርመን የኤርትራ ኤምባሲ ደግሞ የኖቤል ሽልማቱ «የአስመራ አዋጅ» ተብሎ የሚታወቀውን የኤርትራ እና የኢትዮጵያን ስምምነት ከነበረበት አንድ እርምጃ ወደ ፊት በማራመድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚያስችል እምነቱ መሆኑን አስታውቋል። 

ለዓመታት ኑሯቸውን በአዲስ አበባ አድርገዋል፤ በኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ የነበረውን ውጣ ውረድ ሁሉ እንደሚያስታውሱም ይናገራሉ። ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት መካከል ሰላም ለማውረድ ሲደረጉ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች በንቃት ሲከታተሉ እንደነበረም ያትታሉ፤ ኤርትራዊው አቶ የማነህ ተከስተ። እርሳቸው እንደሚሉት በእርግጥ የኖቤል ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መሰጠቱ ከእርሳቸው አልፎ በጦርነት ለሚታወቁት የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት በሙሉ ደስታ እንደሚሆን እምነታቸው ነው።

Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/dpa/NTB scanpix/H. M. Larsen

«ሁላችንም ኤርትራዊያን ብቻ ሳንሆን አጠቃላይ አለም በሙሉ ደስተኛ ሊሆኑበት እንደሚችሉ አምናለሁ።» ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ገብተው በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት ንብረታቸው ተወርሶባቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ቢንያም ብርሃነ የተባሉ ሌላው ኤርትራዊ ደግሞ የሁለቱ ሃገራት ወደ ሰላም መምጣት እና አዲስ ግንኙነት መጀመር በተጨባጭ ለውጥ አልታየም ባይ ናቸው። አቶ ቢንያም የተወረሰባቸውን ንብረት ለማስመለስ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም መፍትሄ አለማግኘታቸውን በምሬት ይናገራሉ።
«ምንም የመጣ ለውጥ የለም ሌላ ኮሚቴ ስለሚመጣ ጠብቅ እያሉኝ ተሳቢ ተሽከርካሪዬን እስካሁን አልሰጠኝም።»

ዶ/ር ዐቢይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ሰላም ስለወረደ የኖቤል ሽልማት ተሸለሙ በሚለው ሀሳብ እንደማይስማሙ የተናገሩት ደግሞ በእንግሊዝ ሎንዶን የሚኖሩት የኤርትራዊያን ሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ሰላም ኪዳነ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ እና በሌሎች ጎረቤት ሃገራት ላከናወኗቸው የለውጥ እና የሰላም ተግባራት ሽልማቱ ቢገባቸውም ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ግን ባልመጣ ለውጥ መሸለማቸውን አላምንበትም ብለዋል።

«ጥሩ ጅማሬ ያለበት ስለሆነ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየመጣ ያለውን ታሳቢ አድርጎ ቢሸለሙ መልካም ነው ነገር ግን ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ግን የተቀየረ  ነገር ባለመኖሩ ሰላም አለ ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።» 

Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/AP Photo/NTB scanpix/H. M. Larsen

የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ሰላም ኪዳነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ስም ደጋግመው መጥራታቸው ፕሬዚዳንቱ በኤርትራዊያን ላይ እያደረሱ ነው ላሉት አፈና እውቅን እንደመስጠት ነው ባይ ናቸው። «ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የበዳያችንን ስም ደጋግሞ መጥራታቸው እና የጠበቀ ግንኙነት መፍጠራቸው እናን አያስደስተንም።»
የኖቤል ሽልማቱ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የሰላም እና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች መጎልበት አስተዋጽዖ እንደሚኖረው በጀርመን የኤርትራ ኤምባሲ አስታውቋል። በኤምባሲው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና ሚዲያ ኃላፊው አቶ ተክሉ ለባሲ እንዳሉት ሽልማቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት በጋራ የወሰዱት ነው።

«ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው እንኳን ደስ ያልዎት ማለት እወዳለሁ። ሽልማቱ ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በሙሉ መሆኑ ነው።» በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ተጀምሮ በመሀል እንደቆመ የሚነገርለት የየብስ ግንኙነትን ጨምሮ ሌሎች ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ጉዳዮችን ለመፍታት «የአስመራ አዋጅ» ተብሎ የሚታወቀውን የኤርትራ እና የኢትዮጵያን ስምምነት ትኩረት ሰጥቶ መተግበር ተገቢ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ዛሬ ወደ ሀገር ሲመለሱ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ