1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ከአሜን ባሻገር-ከበዕውቀቱ ስዩም ጋር

እሑድ፣ ጥር 29 2008

«ሰዎችን ታሪክ ተንተርሰን ልንጨቁናቸው ወይም ደግሞ የሚገባቸውን መብት ልንነጥቃቸው፤ልናስፈራራቸው ወይም ደግሞ ስልጣንን ለመጨበጥ ታሪክ መነሻ አድርገን ወደ የማይገባ የፖለቲካ ውሳኔ መሔድ አይገባንም።» በዕውቀቱ ስዩም

https://p.dw.com/p/1HqOk
Ein Stapel Bücher aus Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele

ስለ ከአሜን ባሻገር-ከበዕውቀቱ ስዩም ጋር

ይህ 'የጥንት አልቃሽ' እንጉርጎሮ በአዲሱ የበዕውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር መጽሀፍ የተጠቀሰ ነው። ገጣሚ እና ጸሃፊው በዕውቀቱ 'የመጨረሻው ምሳ' በተሰኘው ጽሁፉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተዳኘበትን ችሎት እና ከመታሰሩ በፊት የአብሮነት ውሏቸውን ያስቃኛል። ከአሰልቺው ችሎት የምናብ ሽሽት 'በዘፈቀደ' ከገለጠው የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ 'ባህረ ኃሳብ' የተሰኘ መጽሀፍ የነገስታቱን ዘመቻዎች እና የፍርድ አፈጻጸሞች በጥቂት መስመሮች ያስነብባል። በአስር ገጽ በቀረበው የመጨረሻው ምሳ ጽሁፍ የፍትህ መጓደልን ወደ ፊት እና ወደ ኋላ እየተመላለሰ ይተርካል። አብዛኞቹ በከአሜን ባሻገር የተካተቱ መጣጥፎች ግን ከዘመናት በፊት የተፈጸሙ ታሪካዊ ኩነቶችን ይፈትሻልሉ፣ይሞግታሉ።የተመረጡት ርዕሰ ጉዳዮች፤ዘመናት ፤ነገስታት እና የጦር መሪዎች አወዛጋቢነት በወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትርክት የጎላ ሚና ያላቸው ናቸው። በዕውቀቱ ስዩም ከታሪክ ለመዘዘው ሙግት በኢትዮጵያውያንና ታሪካዊ ኩነቱ በተፈጸመባቸው ዘመናት ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ አገር አሳሾች፤የሐይማኖት መምህራን እና የተለያዩ ግለሰቦች በግዕዝ፤ፈረንሳይኛ፤ጣልያንኛ እና እንግሊዘኛ የጻፏቸውን ጽሁፎች በማመሳከሪያነት ተጠቅሟል።

ከአሜን ባሻገር

አዲስ አበባ ላይ ለገበያ በቀረበ በጥቂት ቀናት 20,000 ኮፒ የተሸጠው እና ከተተመነለት 70 ብር ወደ 200 ብር ያሻቀበው ከአሜን ባሻገር አስራ ዘጠኝ ፖለቲካ እና ታሪክ ቀመስ ጽሁፎችን ያካተተ ነው። በአጻጻፍ ስልቱም ይሁን በትኩረት ማዕከሉ ከቀደሙት የበዕውቀቱ ሥራዎች የተለየ ነው። «ታሪክን ለመዘገብ አይደለም። አላማዬ» የሚል በእውቀቱ «በተለያየ የፖለቲካ ዓላማ ምክንያት የሚያጋንኑትን፤የሚያጣምሙትን ወይም የሚፈበረኩትን (አውዳሚ አሳብ ልትለው ትችላለህ) ለማቃናት ወይም ደግሞ ለመሞገት» የተጻፉ መጣጥፎች እንደተካተቱበት ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

በከአሜን ባሻገር ውስጥ የተካተቱት መጣጥፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምረው አሁን በሚገኝበት በዩናይትድ ስቴትስ የብራውን ዩኒቨርሲቲ በተደረጉ ጥናትና ምርምሮ የበለጸጉ መሆናቸውን አስረድቷል። «የአባቶቻችን ስኬቶችም ውድቀቶችም የጋራችን ናቸው።» የሚለው በዕውቀቱ ስዩም «እርስ በራሳችን ላለን ግንኙነት ማሰብ አለብን።» ሲል ይሞግታል። «ሰዎችን ታሪክ ተንተርሰን ልንጨቁናቸው ወይም ደግሞ የሚገባቸውን መብት ልንነጥቃቸው፤ልናስፈራራቸው ወይም ደግሞ ስልጣንን ለመጨበጥ ታሪክ መነሻ አድርገን ወደ የማይገባ የፖለቲካ ውሳኔ መሔድ አይገባንም።» ሲልም ያክላል።

በዕውቀቱ ስዩም በግጥም ሥራዎቹ፤ አጫጭር እና ረጅም ልቦለዶቹ በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ስም እና ተቀባይነቱን ከፍ አድርጎ ማስቀመጥ ችሏል። ቀደም ካሉ ዘመናት ጸሃፊያን በተለየ ሳቅ እና ፈገግታ የሚያጭሩ ግን ደግሞ አብዝተው ማሰላሰልን የሚጠይቁ ሥራዎቹን በግል መጽሔት እና ጋዜጦች በማቅረብ ወደ ውይይት እና ክርክር አደባባዩ መቅረብ ችሏል። በራሱ ድምጽ የተረካቸው ሥራዎቹ በማህበራዊ ድረ-ገጽ መገናኛዎች እንደልብ የሚገኙ በብዛት የሚደመጡም ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ