1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች በኢጣልያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2006

የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ ኢጣልያ የሚገቡ ስደተኞች በተለይ በላምፔዱዛ ደሴት የሚፈፀምባቸው ሰብዓዊነት የጎደለው አያያዝ እዚህ አውሮፓ እያነጋገረ ነው ። በኢጣልያ የስደተኞችን መብት የሚጋፉ አያያዝ የመኖሩን ያህል በአንፃሩ ተፈላጊ የሆኑባቸው አካባቢዎችም አሉ ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ያስቃኘናል ።

https://p.dw.com/p/1AgVc
ምስል picture-alliance/ROPI

በሜዲቴራንያን ባህር ላይ የምትገኘው የኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ በቅርብ ጊዜው አሰቃቂ የስደተኞች ሞት ብቻ ሳይሆን በአሳፋሪ የስደተኞች አቀባበልና አያያዝ የምትጠቀስ ደሴት ከሆነች ሰነበተች ። በአንድ የህግ ምሁር ሶሪያዊ ስደተኛ ተቀርጾ በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ቪድዮ በደሴቲቱ የስደተኞች መጠለያ የሚፈፀሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን አጋልጧል ። በኢጣልያ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰራጨው ይኽው ቪድዮ በላምፔዱዛው የስደተኖች መጠለያ የውጭ ዜጎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰልፈው ያሳያል ። ስፍራው የህክምና ባለሞያዎች ለስደተኞች ከተባይ የሚያፀዳ መድኃኒት የሚሰጡበት ቦታ ነው ። በምስሉ ላይ በአዳራሹ ከነበሩት ወንዶች ስደተኞች አንዳንዶቹ ክብረ ነክ በሆነ ሁኔታ ራቁታቸውን እንዲቆሙ ተደርገው ይታያሉ ። በመላው ዓለም የተሰራጨው ይኽው ምስል ባለፈው ሳምንት በታሰበው የዓለም የፈላስያን ቀን በአውሮፓ ትልቅ ቁጣ አስከትሏል ። የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት ድርጊቱን አውግዘው ለኢጣልያ የሚሰጡትን ድጋፍ ወደፊት ሊገቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል ። የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሴሲሊያ ማልምስትሮም ስለ ጉዳዩ ባወጡት መግለጫ የአውሮፓ ህብረት ስደተኞች በብዛት ለሚጎርፉባት የህብረቱ የድንበር ሃገራት አንዷ ለሆነችው ለኢጣልያ እርዳታ ለመስጠት ቃል መግባቱን አስታውሰው ሆኖም አያያዙ ስርዓት ያለው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል ።

Italien Flüchtlingsdrama Lampedusa Flüchtlingsboot
ምስል picture-alliance/ROPI

ማልምስትሮም በመግለጫቸው ኢጣልያ ስደተኞችን እንድታስተናግድ ህብረቱ የሚሰጣት ድጋፍና እርዳታ ሊቀጥል የሚችለው ሃገሪቱ ስደተኞችን የምትቀበለው ሰብዓዊ መብታቸውንና ክብራቸውን ጠብቃ ለመሆኑ ዋስትና የምትሰጥ ከሆነ ብቻ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል ። የኢጣልያ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ድርጊቱን ተቃውመዋል ። የላምፔዱዛ ከንቲባ ጊዩሲ ኒኮሊኒ ያዩትን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በነበሩት የሰዎች ማጎሪያዎች ውስጥ ከሚፈፀሙት ጋር ነው ያነፃጸሩት ። ከንቲባዋ የተሳፈሩባት ጀልባ ላምፔዱዛ አቅራቢያ ሰጥማ ሕይወታቸው ያለፈው ስደተኞች በማስታወስ ከአሁን በኋላ የመሰል ችግሮችን ቀዳዳ መድፈን እንደሚገባ አሳስበዋል ።
« አደጋው ከደረሰ በኋላ ብዙዎቹ እንባቸውን አፍስዋል ። በዚሁ አሰቃቂ አደጋ 366 ሰዎች ህይወታቸውን በማጣታቸው ሁሉም ከልብ አዝነው አለቀሱ ። ከለቅሶው በኋላ አነዚህ ሁሉ ሰዎች ሃላፊነት ይበልጥ ተሰማቸው ። ለነዚህ ሰዎች ሁሉ እልቂት ምክንያት የሆነው አሁኑኑ መለወጥ አለበት ።»
የኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤንሪኮ ሌታ ደግሞ በቅርቡ ይፋ በሆነው ቪድዮ የታየውን ለማጣራትና ተጠያቂዎቹም ለመቅጣት ቃል ገብተዋል ። የደሴቲቱ የህክምና አገልግሎት ሰጥ ሠራተኞች ግን በወቅቱ ስደተኞች ራቁታቸውን የቆሙት ተገደው አለመሆኑ በየተራ ሊያዩዋቸው ያልቻሉትም ብዛት ስለነበራቸው እንደሆነ በመከራከር ተጠያቂ ልንሆን አንችልም ብለዋል ። ይሁንና ላምፔዱዛ ነዋሪ የሆኑት ማርያና ማርዮ ሊቤራቶሬ በደሴቲቱ ስደተኞችን ሊንባከቡ የሚችሉ ሠራተኞች እንዳሉ ነው የሚናገሩት ።

« ስደተኞቹን ማየት የሚገባቸው ሥራቸው ይኽው የሆነ ሐኪሞችና ሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች አሉ ። ሃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው እነርሱ ናቸው ። »
በላምፔዱዛ በስደተኞች ላይ የተፈፀመው በደል በመላው ዓለም ከተሰራጨው በኋላ የመጠለያው ሃላፊና አንዳንድ ሠራተኞች ከሥራ ታግደዋል ። ዜናው ትልቅ መነጋገሪያ በመሆኑም መጠለያው በአፋጣኝ እንዲፀዳም ተደርጓል ። በየዓመቱ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ኢጣልያ ይገባሉ ። አብዛኛዎቹ በሺህዎች የሚቆጠር ዶላር ከፍለው ከግብፅ ከሊቢያ ወይም ከቱርክ የባህር ጠረፎች በሰዎች በተጨናነቁ ጀልባዎች ነው የሚመጡት ።ወደ ኢጣልያ ለሚያቀኑት ለአብዛኛዎቹ ስደተኞች ከኢጣልያ ይልቅ ለቱኒዝያ የምትቀርበው ላምፔዱዛ መሸጋገሪያቸው ናት ።የላምፔዱዛ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል በይፋ እንዲያስተናግድ የተፈቀደለት 260 ስደተኞችን ነው ። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ከ1ሺህ በላይ ስደተኞች ታጭቀውበት ነበር ። በየመኝታ ክፍሉ የነበሩት አልጋዎች አሁን የሉም ። ባለሥልጣናት ለዚህ የሰጡት መልስ ከብረት የተሰራውን አልጋ እንደ መሣሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ምክንያት ነው ። በዚህ የተነሳም ስደተኞች አሁን በቀድሞው ወታደራዊ ሰፈር ውስጥ መሪት የተዘረጋ ፍራሽ ላይ ነው የሚተኙት ። የስደተኞቹ ቁጥር እስከ አንድ ሺህ ሲጠጋ ወደ ማዕከሉ የሚጎርፈው ስደተኛ እየጨመረ በመምጣቱ ብዙዎች ላስቲክ አንጥፈው አውላላ ሜዳ ላይ እያደሩ ወደ ሌሎች መጠለያዎች የሚወሰዱበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ። ይህ የሆነው ባለፈው ጥቅምት በርካታ ስደተኞች ደሴቲቱ አቅራቢያ ሰጥመው ከሞቱና በሕይወት የተረፉትም ወደ መጠለያው ሰፈር እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ነው ። በዚያን ጊዜ ላምፔዱዛ የነበሩት ስደተኞች ቁጥር 1500 ይደርስ ነበር ። የላምፔዱዛ ከንቲባ ስደተኞችን ወደ ተጨናነቁ መጠለያዎች መምጣታቸው መቆም አለበት ይላሉ ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በርሳቸው እምነት የአውሮፓ የስደተኞች አቀባበል ህግ መቀየር አለበት ። ማለትም ስደተኞች ወደ አውሮፓ መግባት ሊፈቀድላቸው ይገባል ። ያም ሆኖ ላምፔዱዛ የሚመጡትም በህጉ መሠረት በ74 ሰዓት ውስጥ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል እንደ ከንቲባዋ ።
ስደተኞች የሚሰቃዩት በላምፔዱዛ ብቻ አይደለም ። ሚኒዮ ሲሲሊ የሚገኘው ማዕከልም ተቃውሞ ተለይቶት አያውቅም ። እዚያ ደግሞ ችግሩ የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች መልስ መዘግየት ነው ። ተገን ጠያቂዎች አንደሚሉት አንድ ማመልከቻ በሂደት ውስጥ እስከሚያልፍ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊወስድ ይችላል ። መጠለያው ሊይዝ የሚችለው ቢበዛ 2ሺህ ስደተኞችን ነው ። አሁን በመጠለያው ያሉት ስደተኞች 4ሺህ ይደርሳሉ ። ናይጀሪያዊው ፒተር ሰንዴይ መጠለያው ከገባ 5 ወር ሆኖታል ። እርሱ እንደሚለው የሚሰጡት ምግብ አልተስማማውም ።
« ኑሮ በሚኖ እጅግ አስቸጋሪ ነው ። ጠዋት የሚሰጠንን መብላት ይቻላል ። ለምሳና ለእራት የሚሰጡን ግን የሚበላ አይደለም ። »
ሰንዴይ ምግቡ ብዙውን ጊዜ ሆዱን እንደሚያመውና የሚሰጠው መድሐኒት ቴትራሳይክሊን ብቻ መሆኑን ነው የሚናገረው ። የስደተኞቹ ማዕከል በዚያ ላውቀመጣቸው ተገን ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው መጠለያ ምግብ እና ህክምና እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ወደ 40 ዩሮ ይሰጠዋል ። በ ስደተኞች ስም በሚሰጠው ገንዘብ በመጠለያው ሰፈር የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ትርፍ በማጋበስ ይወቀሳሉ ። አብዛኛዎቹ ጣሊያኖች ባህር አቋርጠው ወደ ሃገራቸው የሚገቡ ሰዎች ላይ ስጋት እንዳለቸው ይነገራል ። የደቡባዊቷ ኢጣልያዋ ግዛት ካላብሪያ ስደተኞች ወደ ኢጣልያ ከሚገቡባቸው አካባቢዎች አንዷ ናት ። በዚህ ግዛት ስር ካሉት አካባቢዎች በአንዳንዶቹ ስደተኞች ተቀባይነትን ሲያገኙ በተወሰኑት ደግሞ አይፈለጉም ። ለምሳሌ ሮሳርኖ በተባለችው መንደር በነዋሪዎችና ዜግነታቸው የውጭ በሆነ ገበሪዎች መካከል ጠብ ተቀስቅሶ ነበር ። አነዚህን የመሳሰሉ ስጋቶች ባሉበትና በደሎችም በስደተኞች ላይ በሚፈፀሙባት በኢጣልያ ስደተኞች የሚፈለጉባቸው አካባቢዎችም አልጠፉም ። በዚህ ረገድ በኢጣልያዋ የደቡብ የባህር ዳርቻ ካላብርያ ግዛት ውስጥ የምትገኘዋ የሪያቼ መንደር ትጠቀሳለች ። የዶቼቬለው ጆን ላውረንሰን እንደዘገበው ከሺህ ዓመታት በፊት እንደተቆረቆረች ከሚነገርላት ከዚህች መንደር ነዋሪዎች 1700 ው ባህር አቋርጠው የገቡ ስደተኞች ናቸው ። የ32 ዓመቱ ጋናዊው ዳንኤል ከ 5 ዓመት በፊት ነበር ከባለቤቱና ከ2 ወንዶች ልጆቹ ጋር ወደ ኢጣልያ የመጣው ። የመጀመሪያ መድረሻው ላምፔዱዛ ነበረች ። ከዛ ወደ ሪያቼ ሄደ ። ዳንኤል እንደሚለው የመንደሪቱ ነዋሪዎች ስደተኞችን መርዳት ብቻ ሳይሆን ስደተኞቹ እዚያው እንዲቆዩ ይፈልጋሉ ።

Italien EU Flüchtling auf Lampedusa
ስደተኛ በላምፔዱዛምስል Getty Images
EU Cecilia Malmstroem Internet Kriminal
ማልምስትሮምምስል AP
Zwei Blechschilder
ምስል John Laurenson

ካላብርያ እንደ ላውርሰን ዘገባ ከኢጣልያ ግዛቶች በድህነት የምትታወቅ ክፍለ ግዛት ናት ። ማፍያዎች ኤኮኖሚውን በሚቆጣጠሩበት በዚህ ግዛት ወጣቶች አካባቢውን ለቀው የሚወጡበት አጋጣሚ ሲያገኙ ሳያቅማሙ ነው ጥለው የሚሄዱት ። እናም ስደተኞች እነዚህ መንደሪቱን ጥለው የሚሄዱ ነዋሪዎች እየተኩ ነው ። እያነሰ የሄደው የነዋሪዎቿ ቁጥር አሁን እድሜ ለስደተኞች ከፍ ብሏል ። ቀድሞ የተወረረች ትመስል የነበረችው ይህች መንደር አሁን ህንፃዎች እየተገነቡባት ነው ። ህፃናትም እየቦረቁባት ነው ። ልጆች በመኖራቸው አሁን ትምህርት ቤቶችም ከመዘጋት ድነዋል ። ስደተኞች በከተማዋ ህይወት ከመዝራታቸውም በላይ ቻልያኖቹ ሊሰሩባቸው በማይፈልጉ የሥራ መስኮችም ተሰማርተዋል ። አዛውንቶችን ይንከባከባሉ በአካባቢው በሚመረተው የወይራ ፍሪ እርሻ ውስጥም ይሰራሉ ። አንድ ሶማሌ ምግብ ቤት ከፍቷል አራት በአስተርጓሚነት ይሰራሉ ። በሱቆች ውስጥ የሚነግዱም አሉ ። በቀለም ባሸበረቀው የሪያቼ ባሃላዊ የሸክላ ሥራ የተሰማራም ስደተኛ ይገኛል ። ከመንደርዋ ነዋሪዎች አብዛናዎቹ ስደተኞቹ ሰርተው በመኖራቸው ደስተኛ ቢሆኑም ቅር የሚላቸውም አልጠፉም ። ከቀድሞው አሁን ብዙ ሥራ መኖሩን የማናገረው አንዱ ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ የመንደሯ ነዋሪ አሁን የውጭ ዜጎች ከጣሊያኖች የበለጠ ብዙ የሥራ እድል እንዲያገኙ በመደረጉ ቅሪታ አለው ። አንዳንዶች ደግሞ መጤዎችን ባህሉን በመበረዝ ይወቅሷቸዋል ። የሪያቺ ልማት በአመዛኙ ከመንግሥትና ከአውሮፓ ህብረት በሚገኝ የእርdta ገንዘብ ጥገኛ ነው ። በሌላ በኩል መንደሪቷ ከስደተኞች ተጠቃሚም ሆናለች ። አስተዳዳሪዋ ለምርጫ ሲወዳደሩ የሚደጋግሙት መፈክር ከዓለም ድሃዎቹ ህዝቦች ሪያቺን ያድኗታል እኛ ደግሞ እነርሱን እንታደጋለን የምል ነበር ። በዚህች መንደር ስደተኞች በነፃነት እየሰሩ የቤተሰቦቻቸውንም ሕይውት እየለወጡ መኖር ቢችሉም በሌሎቹ የኢጣልያ የባህር ዳርቻዎች የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች ግን መሰቃየታቸው እንደቀጠለ ነው ።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ