1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች በግሪክ-መቄዶኒያ ድንበር

Merga Yonas Bulaማክሰኞ፣ ኅዳር 21 2008

ከተለያዩ ሃገራት ወደሰሜን የአዉሮጳ ሃገራት ለመግባት ባለፈዉ ዓመት ማለቂያ ቁጥራቸዉ እጅግ በርካታ የሆነ ስደተኞች በግሪክና ሜቄዶኒያ ድንበር አካባቢ ተከማችተዉ ቆይተዋል።

https://p.dw.com/p/1HFXa
Flüchtlinge an der greichisch-mazedonischen Grenze
ምስል DW/D. Cupolo

[No title]

ባለፈዉ የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት በሜቄዶኒያ የድንበር አካባቢ የተፈጠረዉ የስደተኞች ትርምስ የቀዉስ አይነተኛ ማሳያ ሆኖ ሰንብቷል። በአስር እና በሽዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በተፈጠረዉ ግርግር ዉጥረት ከበዛባቸዉ ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ጋር ሲገጣጠሙ የሚከተላቸዉ አስለቃሽ ጋዝ እና የጠመንጃ ሰደፍ ነበር። አሁን በአካባቢዉ ጊዜያዊ አዲስ የመሸጋገርያ ማዕከል በመቋቋሙ ሁኔታዉን አሻሽሎታል።


አፍጋኒስታናዊ ወጣት ነዉ፤ በሜቄዶንያ ጌቭጌሊጃ በተባለችዉ የድንበር ከተማ በሚገኘዉ አደስ የመሸጋገርያ ማዕከል ዉስጥ ሆኖ ጉዞዉን ለመቀጠል ይጠባበቃል። እንደ አብዛኛዉ 7000 የሚገመት ስደተኛ የዚህ ወጣት ዓላማም ወደ ጀርመን መጓዝ ነዉ። ሀገሩን ጥሎ ከመሰደዱ በፊት ሬዛዕ የጀርመን ሠራዊት ከአፍጋኒስኗ ኩንዱዝ ክፍለ ሀገር ለቆ እስኪወጣ ድረስ በአስተርጓሚነት ሢሠራ ቆይቷል። የጀርመን ወታደሮች ያን አካባቢ ሲለቅቁና ታሊባኖች ሲቆጣጠሩት የተፈጠረዉን ባርጋላይ ሬዛዕ እንዲህ ያስረዳል፤ <<በታሊባኖች ማስፈራራትና ስጋት ስር ነበርኩ። ቤተሰቦቼ በማይታወቅ ቦታ ስለሆኑ እነሱንም ወደ ጀርመን ማምጣት አለብኝ። ምክኒያቱም እነሱም ነፃነትን ይፈልጋሉ። ሁሉም ሰዉ በነፃነት መኖርን ይፈልጋል። ሆኖም ግን እንደምታዉቀዉ አፍጋኒስታን ዉስጥ ላለፉት ለ30 ዓመታት ከአልቃይዳ፤ ታሊባን፤ ዳይሽ ጋር ጦርነት፤ ጦርነት፤ ጦርነት ብቻ ነዉ። ኣሁን የሚሰደደዉ ሰዉ ቁጥርም በየቀኑ ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶዋል።>>
ምንም እንኳን ሬዛዕ ወደዚህ ቢመጣም በጀርመንም እንዲሁ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ገና ረጂም መንገድ ይጠብቀዋል። እንዲያም ሆኖ ከሁለት ወር የፍርሃት፣ የመሳቀቅ እና የሽሽት ስደት በኋላ ለባርጋይ ሬዛዕ በሜቄዶኒያ ግዛት ነገሮች እስኪገርመዉ ድረስ ጥሩ መስመር ይዘዉለታል። እዚያ እንደደረሰ በመጀመርያ ተመዘገበ እና ምግብ፣ ከዚያም አልፎ ገላዉን የሚታጠብበት የሞቀ ዉኃም አገኘ። ከዚያም ወደመሸጋገሪያዉ ማዕከል ለመሄድ ድንበር ጠቃቢ ፖሊሶች በትናንሽ ቡድን ከፋፍለዋቸዉ በሁለተኛዉ መስመር ላይ ተራዉን ያዘ። ከዚህ ስፍራ በኮሮኮንች መንገዱ መጨረሻ ላይ ወደምትገኘዉ ጊዜያዊ የተሽከርካሪዎች መነኻሪያ እና መቆጣጠሪያ ኬላ ይጓዛሉ። በዚህ ስፍራ የሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ታክሲዎች፣ 40 አዉቶቡሶች እና አምስት ለዚህ የተመደቡ ባቡሮች ስደተኞቹን በሴሜን የሀገሪቱ ድንበር አድርገዉ ወደ ሴርቢያ ያጓጉዛሉ።

የሜቄዶንያ ድንበር ጠባቂዉ ፖሊስ ጆኮ ላዛሬቭ በአካባቢዉ የሚገኘዉ መሸጋገሪያ ምዕከል ተጠሪ ነዉ። ለበርካታ ሳምንታት በአካባቢዉ ሥርዓት እና ሕግ የማስከበሩ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል። ባለፈዉ የሰሜን አትላንቲክ የበጋ ወራት የጌቭጌሊጃ አካባቢ በዓለም የተለየ መልክ ይዛ ነበር። በዛን ወቅት የድንበር ቁጥጥሩ ከአቅም በላይ የሆነባቸዉ ፖሊሶቹ ከሶርያ፣ ከኢራቅ ወይም ከአፍጋኒስታን የምመጡ ስደተኞችን ይመቱ ነበር። ኃይለኛዉ የሙቀት ሞገድም ያለዉን ችግር አባብሶት ነበር። አስፈላጊ መሠረታዊ ነገሮች ባልተሟሉባት ሜቄዶኒያ አብዛኛዉ ግዜ 10,000 የሚሆኑ ስድተኞች በአንድ ጊዙ ይመጣሉ።

በመስከረም ወር የትናንሽ ድንኳኖች መንደር ከአረንጓዴዉ ድንበር አካባቢ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘዉ ገላጣ ሜዳ ላይ ተተከለ። <<ጊዜያዊ መሸጋገሪያ ማዕከል>> በሚባለዉ ዉስጥ 1500 የሚሆኑ ስደተኞች ተመዝግበዉ አስፈላጊዉ ነገር እየቀረበላቸዉ ወደሚቀጥለዉ ስፍራ እስኪላኩ ድረስ ይጠባበቃሉ። ሂደቱ አሰልቺ ቢመስልም እያንዳንዱ ስደተኛ በዚህ ቅድመ ሁኔታ ዉስጥ ማለፉ አስፈላጊ መሆኑን ላዛሬቭ ይናገራሉ።
ሜቄዶኒያ የሕግ ለዉጥ ማድረጓ ስደቶኞች በሕጋዊ መንገድ እዚያ እንድቆዩ አድርጓል። በዚህም መሠረት ስደተኞች በሀገሪቱ ሥርዓትና ቁጥጥር ሂደት አልፈዉ በሜቄዶኒያ በኩል ወደሌላ ለመሻገር ወይም ጥገኝነት ለመጠየቅ 72 ሰዓታት አለቸዉ። እስካሁን ግን አንድም ሰዉ ይህን አላደረገም። የስደተኞቹ መስተንገዶ መሻሻል እንዳኮራቸዉ ካነጋገራቸዉ የሚታየዉ ላዛሬቪ፣ «ስደተኞች በአማካይ፣ ከእኛ ጋር ለሶስት ሰዓት ያህል ይቆያሉ።>>
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR ባልደረባ የሆኑት አሌክሳንድራ ክራዉዘ ላዛሬቭ ባሉት ይስማማሉ። የጀርመን ተወላጇ በድንበሩ አካባቢ በማስተናበሩ ተግባር የተሰለፉት ክራዉዘ ድንበር ጠባቂዎቹ ፖሊሶች ስደተኞችን በተቻላቸዉ ሁሉ በአግባቡ ለማስተናገድ ከእነሱ አንዳንድ የአረብኛ ቃላትን ተምረዉ ለመግባባት እንደሚሞክሩ ነዉ የሚናገሩት።
ችግር የሚያጋጥማቸዉ በተለይ ከአፍጋኒስታን ከመጡ ስድተኞች ጋር ሲገናኙ ነዉ፤ ምክንያቱም በመሸጋገሪያ ማዕከሉ ከሚገኙት 10 አስተርጓምዎች ከእነሱ ጋር መግባባት የቻለዉ አንዱ ብቻ ነዉ። «አፍጋኒስታኖች ወይም የሌላ ሃገራት ዜጎች ሶርያዉያነን ስለሚሉ አብዛኛዉን ጊዜ ሶርያዉያን ይናደዳሉ። ምክንያቱም ሶርያዊ ሳይሆኑ ነን በማለት የእነሱን ስቃይ ሌሎች መጠቀሚያ አድርገዉታል ብለዉ ያስባሉ። እናም አብዛኛዉን ጊዜ እየተናደዱ እነዚህ ሲያስመስሉ ነዉ እንጂ ሶርያዉያን አይደሉም በማለት ይናገራሉ። እናም በዚህ በጣም ይበሳጫሉ።»
59 በተሰኘዉ የድንበር ምልክት ድንጋይ ጋር ሲደርሱ ከየአቅጣጫዉ የመጡት ስደተኞ ትግስት ሊኖራቸዉ ግድ ነዉ። ይህ የድንበር ምልክት የሆነዉ ድንጋይ ወደ 600 ሜትር ከአዲሱ የመሸጋገሪያ ማዕከል ራቅ ብሎ የሚገኘዉ የግርክ እና ሜቄዶኒያ የሚጋሩትን አካባቢ ይለየዋል። በዚህ ቀን ወደ 50 የሚጠጉ ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ከአገልግሎት ዉጭ የሆነዉ የባቡር ሀዲድ የሰዉ ግድግዳ በመስራት ቆመዋል። በእነሱና በግርክ ድንበር በኩል መሬት ላይ በተቀመጡ ስደተኞች መካከል የተወጠረ እሾሃማ ሽቦ ተዘርግቷል። ሰማያዊ ሰደሪያ የለበሱ የተባበሩት መንግስታት የረድኤት ሠራተኞች ከመሸጋገሪያ ማዕከሉ 50 ሰዎች እስኪወጡ ድረስ በትዕግስት ቀሪዎቹ ስደተኞች እንዲጠብቁ ይማፀናሉ። በቀስተዳመና አምሳል የተዥጎረጎረ የብርድ መከላከያ ጃኬት የለበሰ ትንሽ ወንድ ልጅ ከዓይኑ ላይ ደስታዉ ይነበባል። «እሺ እሺ» እያለ ተስፋና ደስታዉን ይገልፃል።
ወደ 2000 የሚሆኑ ሰዎች ዛሬ በዚያ ስፍራ ተሰብስበዋል፣ ይላሉ የተባበሩት መንግስታት ድርርጅ የርዳታ ሠራተኛ። ከዚያ በፊት በነበሩት ቀናት ከ8,000 የሚበልጡ እዚያ እንደነበሩም አክለዉ ገለጹ። የሜቄዶኒያ ድንበር ጠባቂዉ ፖሊስ ጆኮ ላዛሬቭ በዚያን ዕለት ማታ ገባ ብዙ ስደተኛ እንደሚመጡ ይጠብቃሉ። ያን ግን የግሪክ ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች በሚወስዱት ርምጃ ላይ የተመረኮዘ ነዉ። አልፎ አልፎ በድንበር ጠባቂ ፖሊሶቹ መካከል ግጭቶች መኖራቸዉን በመግለፅም የአዉሮጳ ኅብረት ድንበሮቹን ማስጠበቅ እንዳለበት ላዛሬቭ ያሳስባሉ፤ <<የአዉሮፓ ህብረት ድንበሩን ማስጠበቅ አለበት፣ ድንበሩ እዚህ አይደለም፣ በቱርክ እና ግሪክ መካከል ነዉ። እነዚህ ሰዎች እዚያ ላይ እንዲቆሙ ቢደረግ ኖሮ እዚህ አይደርሱም ነበር።>>

አሁንም ስደተኞች መምጣታቸዉ አላቋረጠም። የሚመጡበት ሀገር ግን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ መቀየሩን የUNHCR ባልደረባ የሆኑት አሌክሳንድራ ክራዉዘ ይናገራሉ። ካለፈዉ ሰኔ ወር ማለቂያ አካባቢ እሳቸዉ እንደሚሉት ከሆነ 80 በመቶ የሚሆኑ ስደተኞች ከሶርያ በጣም ጥቂቱ ማለትም ሰባት በመቶ የሚሆኑ ደግሞ ከአፍጋኒስታን ወደጌቭጌልያ ከተማ መጥተዋል። አሁን ግን ሁኔታዉ ተለዉጦ የአፍጋኒስታን ስደተኞች እንደሚበዙም ገልጸዋል። ይህም በስደተኞቹ መካከል ከፍተኛ ዉጥረት ፈጥሯል። የ25 ዓመቱ ፋይስል ከቤተሰቡ ጋር በመሆን በደቡብ ምሥራቅ ሶርያ ከምትገኘዉ ደራ ከተማ ነዉ የተሰደደዉ። በኤኮኖሚ ምክንያት ተሰደዉ ሳለ የሶሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት በምክንያትነት በሚያቀርቡ ወገኖች ድርጊት እጅግ መናደዱ በግልፅ ይታያል። አብረዉት ካሉት ስደተኞች አብዛኞቹ ከኢራን፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከአልጄርያ እና ከሞሮኮ መሆናቸዉን ያምናል። እናም ጦርነት ከሌለበት አካባቢ ሰዎች መሰደዳቸዉን እንዲህ ይተቻል። <<ጦርነት በአገራቸዉዉስጥ ካለ መሰደድ ይችላሉ። ግን እስቲ አልጀርርያ ዉስጥ የት አለ ጦርነት? ሞሮኮስ ጦርነት የት ነዉ ያለዉ?>>

Flüchtlinge an der greichisch-mazedonischen Grenze
ምስል DW/D. Cupolo
Flüchtlinge an der greichisch-mazedonischen Grenze
ምስል DW/D. Cupolo

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ