1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውሳኔ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9 2009

በበጎ ተግባራቸው ሲመሰገኑ የነበሩት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሌላ ስም ተሰጥቷቸዋል። ህገ ወጥ ስደትን የሚያደፋፍሩ እና የህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ሸሪኮች እየተባሉ ነው።ኢጣልያ ስደተኞችን ሊረዱ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚገድብ የስነ ምግባር ደንብ ያወጣች ሲሆን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ደግሞ እየዛቱባቸው ነው።

https://p.dw.com/p/2iHdg
Italien Flüchtlinge werden von Hilfsorganisation Sea-Eye gerettet
ምስል picture alliance/dpa/NurPhoto/C. Marquardt

ስደተኞች እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውሳኔ

ዋና ዋና ከሚባሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አንዳንዶቹ በሜዴትራንያን ባህር የሚያካሂዱትን የነፍስ አድን ሥራ ለማቆም መወሰናቸውን እያሳወቁ ነው። ድርጅቶቹ እንደሚሉት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ስደተኞችን ከሞት ለመታደግ በሜዴትራንያን ባህር ያሰማሯቸው መርከቦች ሊቢያ ወደ ባህር ዳርቻዋ እንዳይገቡ በመከልከልዋና የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችዋም ለመርከቦቹ ደህንነት ዋስትና እንደማይሰጡ በማስጠንቀቃቸው ነው። ስደተኞችን ጭነው ከሊቢያ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ጉዞ የሚጀምሩ ደካማ ጀልባዎች በሙሉ ካሰቡበት ላይደርሱ ይችላሉ። በዚህን መሰሉ አደገኛ የባህር ጉዞ ጀልባቸው አቅጣጫ ስቶ ባህር ላይ ለቀናት እና ለሳምንታት የተንከራተቱ ገና ሲነሱ ወይም፣ ግባቸው ሳይቃረቡ ባጋጠሟቸው የተለያዩ ችግሮች የሰጠሙ እና ሌሎችም የተለያዩ አደጋዎች የደረሱባቸው ስደተኞች ጥቂት አይደሉም። በጎርጎሮሳዊው 2013 በርካታ ስደተኞችን አሳፍሮ ወደ ኢጣልያዋ የባህር ዳርቻ ሲሲሊ በመቃረብ ላይ የነበረ አንድ ጀልባ በደረሰበት አደጋ በርካታ ስደተኞች ካለቁ በኋላ አደገኛው የባህር ጉዞ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። በዚህ አደጋ ፣ ጀልባው በእሳት ሲያያዝ የድረሱልን ጥሪያቸው ሰሚ ያጣ በአመዛኙ ኤርትራውያን መሆናቸው የተነገረ 366 ስደተኞች አውሮጳ ደጃፍ ማለቃቸው ብዙ ሲያወዛግብ ከርሟል ። ይህ እና ከዚያ በኋላም በተከታታይ  የደረሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የሞቱባቸው ተመሳሳይ አሰቃቂ አደጋዎች በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሜዴትራንያን ባህር የስደተኞችን ሞት ለማስቀረት የነፍስ አድን መርከቦችን እንዲያሰማሩ ምክንያት ሆነዋል።  በዚህን መሰሉ የነፍስ አድን ሥራ ከተሰማሩት መካከል የፈረንሳዩ ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን በምህጻሩ ኤም ኤስ ኤፍ፣ የብሪታንያው የህጻናት አድን ድርጅት፣ እና ዩገንድ ሬቱንግ እና ሲ-አይ የተባሉት የጀርመናውያን ድርጅቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

Mittelmeer Rettung von Flüchtlingen
ምስል picture alliance/AP Photo/E. Morenatti

ኢጣልያ የአውሮጳ ህብረት እና እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሜዲቴራንያን  ባህር የነፍስ አድን መርከቦቻቸውን ካሰመሩ በኋላ ስደተኞች በባህር ጉዞ መሞታቸው ባይቀርም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩትን ህይወት ማትረፍ ተችሏል። በዚህ የበጎ አድራጎት ተግባራቸው ሲመሰገኑ የነበሩት እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሌላ ስም ተሰጥቷቸዋል። ህገ ወጥ ስደትን የሚያደፋፍሩ እና የህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ሸሪኮች  እየተባሉ ነው።ከዚህ ሌላ ኢጣልያ ስደተኞችን ሊረዱ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚገድብ የስነ ምግባር ደንብ ያወጣች ሲሆን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ደግሞ እየዛቱባቸው ነው። በዚህ ሰበብ ዋና ዋና የሚባሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሜዴትራኒያን ባህር ሲያከናውኑ የቆዩትን የነፍስ አድን ዘመቻ ለማቆም መወሰናቸውን እያሳወቁ ነው። ከመካከላቸው አንዱ ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን በምህጻሩ ኤም ኤስ ኤፍ ነው።«ስደተኞችን የመታደጉን ሥራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው ያቆምነው። የሊቢያ ድንበር ጠባቂዎች በተለያዩ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ ዛቻዎችን ስለሰነዘሩብን ነው።በነርሱ ቁጥጥር ስር ባለ አካባቢ ለመርከቦቻችን ደህንነት ዋስት እንደማይሰጡ አሳውቀውናል። ስለዚህ በዚያ ለተሰማሩ የኛ ሰዎች አደጋው እጅግ ከፍ ያለ ነው ብለን ስላሰብን ነው ሥራውን ያቆምነው። እኛ እና ሌሎች ድርጅቶች በዚህ አካባቢ አልተፈለግንም።»

የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን የስዊዘርላንድ ቢሮ ሃላፊ ብሩኖ ጃካሙ ነበሩ ድርጅታቸው ስደተኞችን መታደግ ለማቆም የወሰነበትን ምክንያት የነገሩን። ድርጅቶቹ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ «ህገ ወጥ ስደትን ታበረታታላችሁ ከህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ጋርም ትተባበራላችሁ» መባላቸው በእጅጉ አሳዝኗቸዋል። ጃካሙ ኤም ኤስ ኤፍ እስካሁን ክስ አልቀረበበትም ይላሉ። ሆኖም ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን አንዳንድ ዘገባዎች ጠቁመዋል። ዩገንድ ሬተት የተባለው በጎርጎሮሳዊው 2016 ስደተኞችን ከሜዴትራንያን ባህር መታደግ  የጀመረው የጀርመናውያን ግብረ ሰናይ ድርጅት መርከብ ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዲመጡ በማደፋፈር ተጠርጥሮ ባለፈው ሰሞን በኢጣልያ አቃቤ ህግ ተከሶ ነበር። ሉቬንታ የተባለው ይኽው መርከብ አደጋ ላይ የሚገኙ ስደተኞችን ከመታደግ ይልቅ ህገ ወጥ ሰው አሻጋሪዎች ከሊቢያ የሚልኳቸውን ስደተኞች መቀበል ነው ተግባሩ ተብሎ ነበር የተከሰሰው። በድርጅቱ መርከብ ላይ የሚካሄደው ምርመራ ቀጥሏል።የድርጅቱ ባልደረባ ዩልያን ፓልከ ለዶቼቬለ እንዳሉት የድርጅታቸው መርከብ የነፍስ አድን ሥራውን የሚያከናውነው በአስቸጋሪ ሁኔታ ነው። በርሳቸው አባባል ከቀደሙት ጊዜያት አንስቶ የሊቢያ ባለ ሞተር ጀልባ አሣ አጥማጆች በነፍስ አድን መርከባቸው ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።«ለኛ ሁኔታው በአጠቃላይ አስቸጋሪ ነው። በተለይ ለመርከባችን ሠራተኞች፤ምክንያቱም ባለሞተር ጀልባ አሳ አጥማጆች ይደነፉብናል። መሣሪያ ይኑራቸው አይኑራቸው አናውቅም። ባለፈው ዓመት አንዲት የስደተኞች ጀልባ ለመውሰድ በኛ መርከብ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢጣልያ ድንበር ጠባቂ መርከብ ላይ ሳይቀር ጥቃት አድርሰዋል። ይህ ሁኔታው ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ያሳያል። »

Rettungsaktion von Ärzte ohne Grenzen Mittelmeer
ምስል DW/K. Zurutuza

ድንበር የለሹ የሐኪሞች ድርጅት ኤም ኤስ ኤፍ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስደተኞችን ከሜዴትራንያን ባህር መታደግ የጀመረው በጎርጎሮሳዊው 2015 ነው። ዓላማውም በአደገኛው የባህር ጉዞ የሚደርሰውን ሞት ለመቀነስ እና ከአደጋ ለሚተርፉትም አስቸኳይ እርዳታ መስጠት ነው። ይሁን እና በባህር ላይ ህግ መሠረት እናከናውነዋለን የሚሉት ይህ መልካም ተግባር ማስከሰሱ እና ማስወቀሱ ድርጅቱን አስደንግጧል እንደ ኤም ኤስ ኤፍ የስዊዘርላንድ ቢሮ ሃላፊ ብሩኖ ጃካሙ። ክሶች ፍጹም ሀሰት እና እውነታውን ያላገናዘቡ የተሳሳተ መረጃን መነሻ ያደረጉ ናቸው ሲሉ ያጣጣሏቸው ጃካሙ ድርጅታቸው በዚህ ተግባር ውስጥ እንደሌለበት ተናግረዋል። ጃካሙ ህግን የሚጻረረው የነፍስ አድን ሥራን ማስቆም ነው ይላሉ። «ኤም ኤስ ኤፍ ከህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችም ጋር ሆነ በሜዴትራንያን ባህር መሰል ሥራ ከሚያከናውኑ ድርጅቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም ሥራችንን የምናካሂደው ከኢጣልያ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር ነው። ህጉን መሠረት አድርገን ነው የምንሠራው ። ህጉም ምንድነው የሚለው በባህር ላይ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን መታደግ ይገባል ነው የሚለው። ይህ ግዴታም ነው። አደጋ ውስጥ የወደቁ ሰዎችን የሚታደጉትን የሚከለክሉ ራሳቸው ህጉን እየጣሱ ነው። »የኢጣልያ መንግሥት በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስደተኞችን ለመርዳት የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሊያሟሉ ይገባል ያለቻቸውን 13 መመሪያዎችን ያካተተውን የስነ ምግባር ደንብ በቅርቡ አውጥታለች። ከመመሪያው አንዱ በሊቢያ ባህር ላይ ስደተኞች በተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እስካልሆኑ ድረስ እርዳታ እንዳይሰጣቸው ወይም እንዳይታደጓቸው ይከለክላል። የዩገንድ ሬተቱ ባልደረባ ዩልያን ፓልከም ይህን በጥብቅ ይቃወማሉ።

Italien Cap Anamur Flüchtlinge Sudan Sudanesische Einwanderer Flash Galerie
ምስል AP

«በባህር ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል መወሰድ ያለበትን እርምጃ የሚመለከተው ህግ አንድ ጀልባ ብቻውን ራሱን ከአደጋ ማዳን ካልቻለ እንደ ባህር ላይ አደጋ ነው የሚቆጠረው። ይህ ደግሞ ከሊቢያ የሚነሳ ጀልባ ሁሉ የሚያጋጥመው ነው። ጀልባዎች በቂ ነዳጅ፣ አይኖራቸውም። ለተሳፋሪዎቹ ምግብ ውሐ አይዙም። መርሳት የሌለብን ነገር 150 ሰዎችን ጭነው ከአስከሬኖች ጋር የሚጓዙ ጀልባዎቹ ሳይቀር  እናገኛለን። ይህ በተደጋጋሚ የሚሆን ነገር ነው።»በ2016 ዓም በርካታ ስደተኞች ወደ አውሮጳ የተሻገሩበት የባልካን መስመር ከተዘጋ በኋላ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከሊቢያ ተነስተው በሜዴትራንያን ባህር አድርገው ወደ ኢጣልያ አቅንተዋል። ከመካከላቸው ተሳክቶላቸው አውሮጳ የሚደርሱ ቢኖሩም በጉዞ ላይ ህይወታቸው ያለፈም በርካቶች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ ቁጥራቸው ከ700 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ስደተኞች እንዳሉ ይገመታል። የአብዛኛዎቹ ዓላማም በባህር ወደ አውሮጳ መሰደድ ነው። ይሁንና የኢጣልያ እና የሊቢያ መንግሥታት ከሊቢያ ባህር የሚነሱ የጀልባ ስደተኞችን ለማስቆም በደረሱበት ስምምነት መሠረት ቁጥጥሩን አጠናቅረዋል። የMSF የስዊትዘርላንድ ቢሮ ሃላፊ ብሩኖ ጃካሙ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች መርከቦች ላይ ጫና ያደረጉት የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች እና ኢጣልያ ግባቸው ግልጽ ነው ይላሉ።

Mittelmeer Rettung von Flüchtlingen
ምስል picture-alliance/dpa/SOS MEDITERRANEE/L. Schmid

«እነዚህ ወገኖች በበየትኛውም መንገድ ግባቸውን አልደበቁም ሰዎችን አሁንም ወደ ሊቢያ መልሶ መውሰድ ነው ግባቸው። በሚቀጥሉት ሳምንታት ባህር ላይ የሚሆነውን የሚያዩ የሚመሰክሩ ነፃ ድርጅቶች እንዲኖሩ ምንም ዓይነት ፍላጎት የላቸውም። እኛ እንደ ነጻ ሰብዓዊ ድርጅት ሁሌም የምናስበው ሰዎች ጥቃት ወደ ሚደርስባቸው እና ወደ ሚሰቃዩበት ቦታ መመለስ አይቻልም ብለን ነው የምናስበው።  እናም በመሠረቱ አሁን ሰዎቹ ጥበቃ ላለማግኘታቸው እና የመፍትሄ ፍለጋው ሃላፊነት የሚወድቀው በአውሮጳ መንግሥታት እና በሊቢያ ባለሥልጣናት ላይ ነው።»የአውሮጳ መንግሥታት የሚመጡባቸውን ስደተኞች ለመግታት ያለውን ቀዳዳ ሁሉ ለመድፈን እየሞከሩ ነው። ስደተኞችን እጅግ የከፋ አያያዝ ወደ ሚጠብቃቸው ወደ ሊቢያ መልሶ ለመላክ የደረሱበት ውሳኔ ግን በሐገሪቱ ሰብዓዊው ቀውስ እንዲባባስ የሚያደርግ እርምጃ ነው ሲሉ ኤም ኤስ ኤፍን የመሳሰሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አሁንም ተቃውሞአቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ