1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች ዛሬም ወደ አዉሮጳ እየጎረፉ ነዉ

ዓርብ፣ መስከረም 7 2008

የምሥራቅ አዉሮጳ መንግሥታት ሥደተኛ እንዳይገባበቸዉ ድንበራቸዉን መዝጋታቸዉን እንዲያቆሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተማፀነ።የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽነር«UNHCR»እንዳስታወቀዉ ድንበርን መዝጋት የስደተኛዉን ችግር ከማባባስ ባለፍ የሚተክረዉ የለም። ሐንጋሪ ድንበሯን ከአጥር አልፋ በጦር ሐይል እያስጠበቀች ነዉ።ስሎቬንያም

https://p.dw.com/p/1GYui
Ungarn Serbien Flüchtlinge Grenze
ምስል Getty Images/AFP/E. Barukcic

ደቡብና ምሥራቅ አዉሮጳን አቋርጠዉ ወደ ምዕራብና ሰሜን አዉሮጳ የሚገቡ ስደተኞች የሚያልፉባት ሐንጋሪ ድንበሯን ከአጥር አልፋ በጦር ሐይል እያስጠበቀች ነዉ። ስሎቬንያም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች። ከሰርቢያ ከገባ በኋላ ወደ ሰሜን መተላለፊያ የተዘጋበት ስደተኛ ገሚሱ ወደ ክሮኤሽያ ሲያመራ የተቀረዉ እዚያ ሰርቡያ ድንበር አዉላላ ሜዳ ላይ ፈስሷል።
«ዛሬ ከሜቄዶኒያ ነዉ የመጣሁት።ሜቄዶኒያ፤ ሰርቢያ ከዚያ ወደ ጀርመን ወይም ወደሆነዉ ሐገር «መሔድ እፈልጋለሁ» ።ስደተኞቹ መተላለፊያ በማጣታቸዉ ከሰላሳ ዴግሪ ሴልሲየስ በሚበልጠዉ ሙቀት ሜዳ ላይ ተኮልኩለዉ መዋል ግዳቸዉ ነዉ።አንዳድ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለስደተኞቹ መጠነኛ እርዳታ እየሰጡ ነዉ።«እዚሕ የምገኘዉ ከቀይ መስቀል ጋር በመሆን የታሸጉ ምግቦች ለማደል ነዉ።»ሐንጋሪ ድንበሯን ከዘጋች በኋላ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ክሮኤሽያ እየገቡ ነዉ።በሁለት ቀናት ዉስጥ ከ14ሺሕ በላይ ስደተኞች ክሮኤሽያ ገብተዋል።በስደተኛዉ ብዛት የተደናገጡት የክሮኤሽያ ጠቅላይ ሚንስትር ዞራን ሚላኖቪች ስደተኛዉ ክሮኤሽያን አቋርጦ እንዲሔድ ዛሬ መክረዋል።
ሃንጋሪ ድንበርዋን ለስደተኞች ከዘጋች በኋላ ወደ ክሮሽያ እየገባ ያለዉ ስደተኛ ቁጥር መንግሥት ከጠበቀዉ ቁጥር በላይ መሆኑ ትናንት ተዘግቦ ነበር። እስካሁን ክሮሽያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ወደ 6200 መድረሱን የሀገሪቱ የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር ገልፆአል። ከመዲና ዛግሪብ የሚያሰራጭ የመንግሥት ቴሌቭዥን ጣብያ እንደዘገበዉ ወደ ሀገሪቱ ሌሎች 4000 ስደተኞች ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዞራን ሚሎኖቪች በካቢኔያቸው ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ስደተኞቹ ምቾትን እንዲያገኙ በተቀላጠፈና በተባበረ መንገድ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነዉ። ክሮሽያ በሰርብያ በኩል ወደ ሃገርዋ የገቡትን እነዚህን ስደተኞች በሙሉ ወደ ጀርመንና ስካንዴኒቪያን ሃገራት እንዲያመሩ እየለቀቀች መሆኑም ተዘግቧል። ሃንጋሪ ድንበርዋን ለስደተኞች በመዝጋትዋ ከአንድ ቀን በፊት ሃንጋሪና ሰርብያ ድንበር ላይ ከፍተኛ ዉጥረት ተቀስቅሶ ነበር። በሃንጋሪ ሮዚክ በተሰኘዉ አካባቢ ወደ ሰርብያ የሚያመራዉን የድንበር አጥር ለማለፍ ተቃዉሞ በማንሳት ድንጋይ በወረወሩ በመቶዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ላይ ወታደሮች አስለቃሽ ጋዝና ዉሃ መርጨታቸው ይታወቃል።

Kroatien Slowenien Flüchtlinge bei Senkovec
ምስል Reuters/S. Zivulovic
Ungarn Grenze Polizeieinsatz gegen Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/dpa/S. Ujvari


ነጋሽ መሃመድ
አዜብ ታደሰ