1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞን መቀበል የከበዳት ኩየት

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2008

ኩየት የሶርያ ስደተኞችን የሰብዓዊ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲቻል ግማሽ ቢሊየን ዶላር ሰጥታለች። ሆኖም ይህቺዉ ለጋሥ ሀገር እንደሌሎቹ የባህረ ሰላጤዉ ሃገራት ስደተኞችን በግዛቷ ተቀብላ ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆኗ ነዉ የሚነገረዉ።

https://p.dw.com/p/1JC3s
Kuwait City Skykine Wirtschaft Business Finanzsektor Architektur Wolkenkratzer
ምስል picture alliance/Robert Harding

[No title]

የተዋቡ አዉራ ጎዳናዎች፣ ሰማይ ጠቀስ እና አንጸባራቂ ሕንፃዎች ያሏት ኩየት ላለፉት አስርት ዓመታት ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ሠራተኞችን የምትስብ ማግኔት ሆና ቆይታለች። በንጉሥ የምትተዳደረዋ ሀገር ሥራም ሆነ አዲስ የመኖሪያ ሥፍራ በሚፈልጉ ተመራጭ ነበረች። ሆኖም ይህ ገፅታዋ ከደበዘዘ ሰነበተ። አሁን ኩየት የተወሰኑ ሰዎችን ነዉ ወደግዛቷ እንዲገቡ የምትፈቅደዉ፤ ስደተኛ ግን መሆን የለበትም። ጦርነት የሚሸሸዉ የሶርያ ስደተኛ ግን የ29 ዓመቱ የኩየት ዜጋ አብደላ እንደሚለዉ ምንም ቢሆን ወደ አዉሮጳ መምጣት ነዉ የሚሻዉ።

«ምክንያቱም ከአረቡ ዓለም የተሻለ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። ይህ ነዉ አጠቃላይ ግምቱ። ግን በአጎራባችነት የሚገኙት ሃገራት ስደተኛ አልቀበልም በማለታቸዉ ወደ አዉሮጳ ለመሰደድ መገደዳቸዉ ያስገርማል።»

ግጭት ጦርነቱ ሀገራቸዉ ዉስጥ ከተጀመረ አንስቶ በጣም ጥቂት ሶርያዉያን ናቸዉ ወደ ኩየት የገቡት። እነሱንም ከሌላ ሀገር ለሥራ እንደመጣ ሰዉ እንደምታስተናግድ ነዉ የፖለቲካ ተንታኙ ሻፊቅ ጋህብራ የሚናገሩት።

«ወደዚህ መምጣት የቻሉት የሥራ ዉል ያላቸዉ ሶርያዉያን ብቻ ናቸዉ። ተዋዉለዉ ሥራ ያላቸዉ ናቸዉ የሚመጡት። ወይም ደግሞ በሥራ ዉል ምክንያት ኩየት ዉስጥ የሚኖር ሶርያዊ ቤተሰቦች ናቸዉ።»

Karte Naher Osten Englisch

ይህን የምታደርገዉ ኩየት ብቻም አይደለችም ሌሎቹም የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት ስደተኞችን መቀበሉ ከብዷቸዋል። ለዚህም ሻፊቅ ጋህብራ እንደሚሉት መልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡ መዋቅርም ለዚህ አሉታዊ ሚና ይጫወታል።

«ኩየት ከሶርያ ጋር በድንበር አትገናኝም በዚህም ምክንያት የስደተኞች ዒላማ ባለመሆኗ በዚህ ጉዳይ ከመቸገር ተርፋለች። በዚያም ላይ መዘንጋት የሌለበት ኩየቶች ራሳቸዉ ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 40 በመቶ ብቻ ሲሆኑ የተቀረዉ በጥገኝነት የሚኖርባት መሆኗን ያዉቃሉ።»

ኩየት ስደተኞችን በመቀበል ፈንታ በርከት ያለ የገንዘብ እርዳታ ነዉ የሰጠችዉ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ብቻም ግማሽ ቢሊየን ዩሮ ገደማ ለግሳለች። ለልግሥናዋም ቀደም ሲል በተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊሙን ተመስግናለች። የኩየቱ ራኢ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ሂንዲ ፍራንስ ግን ለሰዎች ተገን የመስጠት ፈቃደኝነቱ ከገንዘብ በላይ ነዉ ሲሉ ይተቻሉ።

«እኔ እንደማምነዉ፤ ሰዎች በፍጥነት የሚፈልጉት የሚጠጉበት ስፍራ እንጂ ገንዘብ አይደለም። ሰዎች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር እንደ ሰዉ አዲስ ሕይወት የሚጀምሩበት ዕድል ማግኘት ይፈልጋሉ። የባህረ ሰላጤዉ ሃገራት በርካታ ስደተኞችን መቀበል ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፤ ያንን ማድረግም ይችላሉ።»

Kuwait City
ምስል Yasser Al-Zayyat/AFP/Getty Images

ኩየት፣ ኳታር፣ ባህሪን፣ ኦማን፣ የተባበረዉ አረብ ኤሜሬቶች እንዲሁም ስዑድ አረቢያ ስደተኞችን የሚመለከተዉን የተመድ ድንጋጌ ያልፈረሙ ሃገራት ናቸዉ። ራሳቸዉንም እንደ ስደተኛ አስተናጋጅ ሀገር አድርገዉ አይቆጥሩም። ለምሳሌ የፖለቲካ ተንታኙ ሂንድ ፍራንስ ሊባኖሳዉያን ከሆኑት ወላጆቻቸዉ እዚያዉ ኩየት ዉስጥ ቢወለዱም፤ የኩየት ዜግነት የላቸዉም። በሌላ በኩል ለሥራ ወደ ኩየት መጥተዉ ፈቃዳቸዉ ያለቀ ሶርያዉያንም ዕጣ ፈንታ አይታወቅም። የኩየት ዜጋ የሆነዉ አብደላ በዚህ አካሄድ አይስማማም። ሀገሩ ለዘብ ያለ የስደተኛ አስተዳደር መመሪያ ቢኖራት ይመኛል።

«ስደተኞችን ተቀብለን በሥርዓታችን ዉስጥ ማካተት ይኖርብናል ባይ ነኝ። ኩየት በርከታ ስደተኞችን በማስተናገድ ትታወቃለች። ምናልባት ስደተኞች ልላቸዉ ላይገባኝ ይችላል ግን በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ግሩም ሥራየሚያከናዉኑ ፍልስጤማዉያን እዚህ ይኖራሉ።»

አነ አልመሊንግ/ ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ