ስፖርት፤ ሐምሌ 9 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:53 ደቂቃ
16.07.2018

ዋንጫው ፈረንሳይ ገብቷል

በፈረንሳይ የዋንጫ ድል ሩስያ ውስጥ የተቋጨው የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በተረጋጋ ኹኔታ የተካሄደ፣ ኹከት ያልነበረበት እንደነበር ተገለጠ። የፈረንሳይ ተጨዋቾች ከጨዋታው በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለደጋፊዎቻቸው ያካፈሉትን የቪዲዮ መልእክት እንዲሁም በመዲናይቱ ፓሪስ ከድል በኋላ የነበረውን ድባብ በዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን አካተናል።

እግር ኳስ

በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ የተጠበቀው ቀርቶ ያልተጠበቁ ክስተቶች ተስተውለዋል። ታላላቅ የሚባሉ ሃገራት በጊዜ በተሰናበቱበት የሩስያው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ፍልሚያ ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ2 በኾነ ውጤት ድል አድርጋ ዋንጫውን ወደ ሀገሯ ወስዳለች። አጠቃላይ ውድድሩ ብዙዎች ከጠበቁት ውጪ ነው የኾነው። የቀድሞው የዶይቸ ቬለ የስፖርት አዘጋጅ መስፍን መኮንን ተመሳሳይ ሐሳብ አለው። መጀመሪያ አካባቢ ላይ በብርቱ ስትተች የነበረችው ሩስያ ዘንድሮ የዓለም ዋንጫን በተሳካ መልኩ ማከናወኗም በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላታል።

የፈረንሳይ ቡድን የዋንጫው ባለቤት በመኾኑ በሀገሪቱ ለወታደራዊ ክፍሉ እና ለሲቪሉ ማኅበረሰብ የሚሰጠውን ከፍተኛ ማዕረግ እንደሚሸለም የፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ጽ/ቤት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ምሽት ላይ ተጨዋቾቹ በኤሊዜ ቤተመንግሥት ተጋብዘዋል።

Frankreich Paris feiert den Fussball-Weltmeistertitel

ፈረንሳይ ክሮሺያን ድል ካደረገች በኋላ ተጨዋቾች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው መልእክታቸውን ለደጋፊዎቻቸው አድርሰዋል። በተለይ አማካዩ ፖል ፖግባ በኢንስታግራም ገጹ ላይ የቀጥታ ሥርጭት ያደረገ ሲኾን፤ የእንግሊዝ ቡድን ላይ ተሳልቋል።  ምሽት ላይ ፓል ፖግባ ዋንጫውን ይዞ በላከው የቪዲዮ መልእክት፦ «ወደ ቤት መጥቷል» እያለ በዜማ ነበር የቀለደው። የእንግሊዝ ቡድን እና ጋዜጠኞች ቡድናቸው የዓለም ዋንጫን ወደ ቤት ማለትም ወደ እንግሊዝ ይዞ እንደሚመጣ ሲፎክሩ ነበር። ያን ይዞ ነው ፖል ፖግባ የተሳለቀው። በእንግሊዝ ለማንቸስተር ዩናይትድ ተሰልፎ የሚጫወተው ፖል ፖግባ እዛው ቪዲዮ ላይ እንግሊዝ ላይ የተሳለቀው የምር ሳይኾን ለቀልድ መኾኑን  ግን በተደጋጋሚ ገልጧል።

በዓለም ዋንጫ ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ የክሮሺያው አማካይ ሉካ ሞድሪች የዘንድሮ ምርጥ ተጨዋች በሚል የአዲዳስ ወርቃማው ዋንጫ ተሸላሚ ኾኗል። የቤልጂየሙ አጥቂ ኤደን ሐዛርድ የብር እንዲሁም የፈረንሳዩ አጥቂ አንቶኒ ግሪዝማን የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። 

Russland WM 2018 Frankreich gegen Kroatien

አትሌቲክ

ካለፈው ማክሰኞ እስከ ትናንት እሁድ ድረስ ፊንላንድ ታምፔሬ ውስጥ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኮኑ አትሌቶች ባደረጉት ግጥሚያ ኢትዮጵያ በአራተኛነት አጠናቃለች። በአጠቃላይ ውድድሩ ጎረቤት ኬንያ 6 የወርቅ፤4 የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ወጥታለች። 4 የወርቅ፣ 5 የብር እና 3 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጃማይካ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። በሦስተኛነት ያጠናቀቀችው ዩናይትድ ስቴትስ 3 የወርቅ፣ 8 የብር እንዲሁም 7 የነሐስ በአጠቃላይ 18 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች።ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎች በማግኘት ነው በአራተኛነት ያጠናቀቀችው። 2 የወርቅ እና 2 የነሐስ ማለትም 4 ሜዳሊያዎችን ብቻ ያገኘችው ጀርመን በ9ኛ ደረጃ ጨርሳለች። ሜክሲኮ 2 ወርቅ አግኝታ በ10ኛ ደረጃ አጠናቃለች።  በዚህ ውድድር የተሳታፊዎች የእድሜ ጉዳይ እጅግ መነጋገሪያ ኾኖ ነበር።

Symbolbild Selbstläufer

ቡጢ

በዓለም የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ የብሪታንያው አንቶኒ ጆሹዋ የሩስያው አሌክሳንደር ፖቬቲክን መስከረም 12 ቀን ሊገጥም ቀጠሮ ተይዞለታል። ሁለቱ የዓለማችን ኃያላን የቡጢ ተፋላሚዎች ይጋጠማሉ የተባለው በዌምብልደን ስታዲየም ነው። የ28 ዓመቱ ብሪታንያዊ አንቶኒ ጆሹዋ ባለፈው መጋቢት ወር ካርዲፍ ውስጥ ከኒውዚላንዱ ቡጢኛ ጆሴፍ ፓርከር ጋር ባደረገው ፍልሚያ በዳኞቹ የማያዳግም ውሳኔ ድል መቀዳጀቱ ይታወሳል።

Boxen Anthony Joshua vs Joseph Parker

አንቶኒ ጆሹዋ፦ በዓለም የቡጢማኅበር (WBA)፣ በዓለም አቀፍ የቡጢ ፌዴሬሽን (IBF)፣ እንዲሁም በዓለም የቡጢ ድርጅት (WBO) ቀበቶዎችን ሰብስቧል።  እስካሁን 21 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎችን በድል ያጠናቀቀው አንቶኒ ጆሹዋ አሁን የሚፋለመው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2011-2013 ድረስ አሸናፊ ከነበረው የ38 ዓመቱ ሩስያዊ ፖቨትኪን ጋር ነው። በሁለቱ የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚዎች ጋር የሚከናወነው ግጥሚያ በበርካታ የቡጢ ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ