1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 9 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ መጋቢት 9 2011

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል መሪነቱን ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ ተረክቧል። በሻምፒዮንስ ሊጉ የሞት ሽረት ፍልሚያ በሊቨርፑል የተቀጣው ባየር ሙይንሽን እልሁን በጀርመን ቡድንደስ ሊጋ ማይንትስ ላይ ተወጥቷል። በላሊጋው ሊዮኔል ሜሲ ሔትሪክ ሠርቶ ደጋፊዎቹን ከመቀመጫቸው በማስነሳት  አስጨብጭቧል።

https://p.dw.com/p/3FGea
Tennis BNP Paribas Open Indian Wells Bianca Andreescu
ምስል Reuters/USA Today Sports/J. Kamin-Oncea

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል መሪነቱን ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ ተረክቧል። በሻምፒዮንስ ሊጉ የሞት ሽረት ፍልሚያ በሊቨርፑል የተቀጣው ባየር ሙይንሽን እልሁን በጀርመን ቡድንደስ ሊጋ ማይንትስ ላይ ተወጥቷል። በላሊጋው ሊዮኔል ሜሲ ሔትሪክ ሠርቶ ደጋፊዎቹን ከመቀመጫቸው በማስነሳት  አስጨብጭቧል። በሜዳ ቴኒስ የ18 ዓመቷ ወጣት ካናዳዊት ጀርመናዊቷን ዝነኛ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ አሸንፋለች። በፎርሙላ አንድ የመጀመሪያ ዙር ሽቅድምድም የሜርሴዲስ ቡድን ድል ቀንቶታል። 14ኛው የብስክሌት ግልቢያ ፉክክር በባሕርዳር አሁንም ቀጥሏል። እስካሁን የነበረውን የውድድር ይዘት የሚመለከት ዘገባ ከባሕር ዳር አካተናል። ለአፍሪቃ የእጅ ኳስ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ያለፈው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን በበጀት እጥረት የተነሳ በውድድሩ አይሳተፍም ተብሏል።  

ከሁለት ሳምንት በኋላ በአፍሪቃ የእጅ ኳስ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ለሁለተኛ ጊዜ ተፎካካሪ ለመኾን አልፎ የነበረው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን በበጀት እጥረት ላይሳተፍ እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል ። ምናልባትም ዘንድሮ በ35ኛው የአፍሪቃ የእጅ ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የመቀሌ ቡድን ብቻ ይኾናል ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ዘገባችን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን አሰልጣኝን ባነጋገርንበት ወቅት ቡድናቸው ከኢትዮጵያ አንደኛ በመውጣቱ ለአፍሪቃ ውድድር ማለፉን በደስታ ገልጠውልን ነበር። ከኮትዲቯር መዲና አቢጃን ይፋ የኾነው መረጃም ከ13 ሃገራት የተውጣጡ 22 ቡድኖች መደልደላቸውን ያመለክታል።

ከአፍሪቃ ሃገራት ቡድኖች መካከልም ቂርቆስ ክፍለ-ከተማ እና መቀሌ 70 የእጅ ኳስ ቡድኖች ኢትዮጵያን ወክለው መደልደላቸውን ያሳያል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሙሉጌታ ግርማ፦ «እጅ ኳስ በኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የስፖርት አይነቶች ተገቢውን ትኩረት አላገኘም» ብለው ነበር ባለፈው ሳምንት ቃለ መጠይቅ ስናደርግላቸው። ቡድናቸው በበጀት እጥረት ምክንያት ከውድድር ውጪ መኾኑን በተመለከተ ያለፈው ሳምንት ንግግራቸው ውሎ ሳያድር በተግባር መታየቱን በቊጭት ተሞልተው  «ያው ያልኩት በእውነት መረጋገጡን ዐታየውም?» ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ገና በማደግ ላይ ያሉ እንደ እጅ ኳስ አይነት የስፖርት ዘርፎች ተገቢውን ትኩረት እና ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል እንላለን ተናግረዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በ81ኛ ደቂቃ ላይ በተገኘ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪነቱን ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ መረከብ ችሏል። ትናንት ሊቨርፑል ፉልሀምን 2 ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያዋን ግብ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ሳዲዮ ማኔ ነው። ፉልሀም 74ኛው ደቂቃ ላይ በሪያን ባቤል አማካኝነት አቻ የምታደርገውን ግብ ቢያስቆጥርም፤ በአቻነቱ የዘለቀው እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ነበር። ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ላይ በተፈጸመው ጥፋት የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ጄምስ ሚልነር ከመረብ በማሳረፍ የፉልሀምን የአቻ ተስፋ አምክኖታል።

Liverpool v Manchester United - Premier League - Anfield
ምስል picture-alliance/Newscom/A. Yates

ሳዲዮ ማኔ የትናንትና ግቡ  11ኛ ኾና ተመዝግባለታለች። የአፍሪቃ የዓመቱ ኮከብ፤ ግብጻዊው ሞ ሣላህ በትናንትናውም ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ጨዋታው ተጠናቋል። ሞ ሳላህ ምንም እንኳን ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን በማመቻቸት አሁንም ወሳኝ እንቅስቃሴ ቢያደርግም፤ እንደባለፈው የጨዋታ ዘመን ግን ድንቅ ግብ አግቢነቱን መመለስ አልቻለም።

የትናንቱ በኤቨርተን 2 ለ0 ሽንፈት ቸልሲ ባለፉት አምስት ተከታታትይ ጨዋታዎች ለአራተኛ ጊዜ ነጥብ የጣለበት ተጨማሪ ድክመቱ ነበር። ታች 12ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው በርመስ 4 ለ0 ከባድ ሽንፈት በደረሰበት ጊዜ አሰልጣኙ ማውሪትሲዮ ሳሪ ከጨዋታው መልስ ተጨዋቾቻቸውን መልበሻ ክፍል ውስጥ ለአንድ ሰአት ያህል ለሽንፈታቸው መልስ እንዲሰጡ ሲወተውቱ ነበር። የባሰውን አታምጣ እንዲሉ በማንቸስተር ሲቲ የ6 ለ0 ሌላ ከባድ ሽንፈት ገጠማቸው። ትናንት ደግሞ በኤቨርተን ሌላ የ2 ለ0 ሽንፈት።

በፕሬሚየር ሊጉ የማንቸስተር ሲቲው ግብ አዳኝ አጉዌሮ እስካሁን ድረስ 18 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ብዙ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ኾኗል። የአርሰናሉ አውባሜያንግ፤ የቶትንሀሙ ሐሪ ኬን፤ የሊቨርፑሉ ሳዲዮ ማኔ እና ሞ ሣላህ እያንዳንዳቸው 17 ግቦችን በማስቆጠር ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የማንቸስተር ሲቲው ስተርሊንግ 15 ግቦች አሉት፤ ሦስተኛ ነው። 

ቡንደስሊጋ

በሻምፒዮንስ ሊጉ የሞት ሽረት ፍልሚያ ባለፈው ሳምንት በሊቨርፑል የተቀጣው ባየር ሙይንሽን እልሁን በጀርመን ቡድንደስሊጋ ማይንትስ ላይ ተወጥቷል። በትናንቱ ጨዋታ ጄምስ ሮደሪጌዝ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። ቀዳሚዋን ግብ ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ግን ፖላንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ነው። ኪንግስ ኮማን በ39ኛው ደቂቃ ላይ አምስተኛ ግብ ለባየር ሙይንሽን ሲያስቆጥር፤ የማሳረጊያዋን ግብ በ70ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፍው ትውልደ-ላይቤሪያዊ ካናዳዊው የ18 ዓመት ወጣት አልፎንሶ ዳቪስ ነው። በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ግቡ ኾናለታለች። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ እድሉ በሊቨርፑል ድል ተጨናግፎበታል። በቡንደስሊጋው ያለፉትን አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግን ማሸነፍ ችሏል።  በጄምስ ሮደሪጌስ ሔትትሪክ፤ በሮበርት ሌቫንዶቭስኪ እና ኪንግስሌይ ኮማን 6 ግቦች ባላጋራው ማይንትስን በዜሮ የሸኘው ባየር ሙይንሽን በደረጃ ሠንጠረዡ መሪነቱን በመያዙ አሁን ሊጽናና ይችላል። የባየር ሙይንሽን ቡድን ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔይስ ግን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በሊቨርፑል የ3 ለ1 ሽንፈት ከሻምፒዮንስ ሊግ የመሰናበታቸው ቊጭት «ገና ከሆዴ አልወጣም» ባይ ናቸው።

Fußball Bundesliga FC Bayern München - Mainz 05
ምስል Reuters/M. Dalder

በእርግጥ ባየር ሙይንሽን የነጥብ ልዩነት ባይኖረውም በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ተረክቧል። ካለፉት አምስት ተከታታይ ግጥሚያዎች አንድ ሽንፈት እና አቻ መውጣት የገጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ተመሳሳይ 60 ነጥብ ቢኖረውም በሰባት ግብ ልዩነት መሪነቱን አስረክቧል። በቡንደስሊጋው ቀሪ 8 ጨዋታዎች ባየርሙይንሽን የሚገጥማቸው ቡድኖች ከዶርትሙንድ ጋር ሲወዳደር የሚያሰጉ አይደሉም። ባየር ሙይንሽን በቀጣይ ከሚጋጠማቸው ስምንቱ ቡድኖች መካከል፦ በቡንደስሊጋው የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኑርንበርግ እና ሀኖቨር 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

በስፔን ላሊጋ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲ ሔትሪክ ሠርቶ መላ የስታዲየሙ ታዳሚን ከመቀመጫው አስነስቶ አስጨብጭቧል። የባርሴሎናው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ሦስተኛዋን ግብ ሲያስቆጥር ደጋፊዎቹ ብቻ አልነበሩም የፈነጠዙት፦ የተቃራኒው ቡድን ደጋፊዎችም ከመቀመጫቸው ተነስተው ሞቅ ባለ ጭብጨባ አወድሰውታል። 4 ለ1 የተሸነፉት ሪያል ቤቲስ ደጋፊዎች ሳይቀሩ የቤኒቶ ቪላማሪኝ ስታዲየም ከጥግ እስከ ጥግ «ሜሲ! ሜሲ !ሜሲ!» በሚል ድምፅ አስተጋብቷል። አርጀንቲናዊው ድንቅ በጨዋታ ዘመኑ 51ኛውን ሔትሪክ መሥራቱ ነበር መላ ስታዲየሙን ያስጮኸው። የእለቱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ከተቃራኒ ወገን እንዲህ ያለ ሞቅ ያለ ድጋፍ አግኝቶ እንደማያውቅ አልሸሸገም።

የሜዳ ቴኒስ

በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የ18 ዓመቷ ወጣት ካናዳዊት ቢያንካ አንድሪስኩ ጀርመናዊቷ ዝነኛ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ አንጀሊክ ኬርቤርን ትናንት አሸንፋለች። በኢንዲያን ዌልሱ የትናንቱ ግጥሚያ ቢያንካ አንጄሊክን የረታችው፦6-4፤ 3-6 እና  6-4 በኾነ ውጤት ነው።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመጀመሪያ ዙር የመኪና ሽቅድምድም የሜርሴዲስ ቡድን ድል ቀንቶታል። በትናንቱ የሜልቦርን ሽቅድምድም የመርሴዲሱ ቫልተሪ ቦታስ አሸናፊ ኾኖ 25 ነጥብ አግኝቷል። የቡድኑ አባል ያለፈው የውድድር ዘመን ባለድል ሌዊስ ሐሚልተን ኹለተኛ በመውጣት የመጀመሪያውን 18 ነጥብ ይዟል። የሬድ ቡሉ ማክስ ቨርሽታፐን ሦስተኛ፤ ያለፈው የውድድር ዘመን ዋነኛ ተፎካካሪ ሰባስቲያን ፌትል አራተኛ ወጥተዋል። አድማጮች አሁን ደግሞ ከባሕርዳር የደረሰንን ዘገባ እናስከትላለን። 14ኛው የብስክሌት ግልቢያ ፉክክር በባሕርዳር አሁንም ቀጥሏል። እስካሁን የነበረውን የውድድር ይዘት የሚመለከት ዘገባ ዓለምነው መኮንን ከባሕር ዳር ልኮልናል።  

Australien Grand Prix Siegerehrung Bottas
ምስል Reuters/J. Smith

ብስክሌት

14ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በባህር ዳር ተጀምሯል፡፡ኢትዮጵያ እስከ ትናንትና 7 ወርቅ በማምጣት ውድድርን እየመራች ነው፡፡ ውድድሩን አስመልክቶ ባለፈው አርብ የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌደሬሽንና የኢትዮጰያ ስፖርት ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ መግለጫ የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ፕረዚደንትና የዓለም አቀፉ ብስክሌት ፌደሬሽን ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር መሐመድ ዋጊሀ አዛም የዘንድሮው ውድድር የሴቶች ቁጥር የበዛትና የድብልቅ ቅብብሎሽ ውድድር ለመጀመሪ ጊዜ የሚካሄድበት መሆኑ ልዩ እንደሚደርገው አመልክተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የተወዳዳሪ ሴቶች ቁጥር 43 መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ ብዙም ታሪክ የላትም ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልል ብስክሌት ፌደሬሽን ስፖርቱን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ሌሎች ክልሎችም ከትግራይ ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በተጀመረው ውድድር ሁለት ጋላቢዎች ብቻ በተሳተፉበት የ15 ኪሎ ሜትር ታዳጊ ሴቶች ወድድር ኢትዮጵያ ወርቅ ስታገኝ ኤርትራ ደግሞ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች፡፡ በዚሁ እለት በ30 ኪሎ ሜትር ታዳጊ ወንዶች የቡድን እሽቅድምድም ኢትዮጵያ ወርቅ፣ ኤርትራ ብርና ሩዋንዳ የነሀስ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በ30 ኪሎ ሜትር ከ23 ዓመት እደሜ በታች ሴቶች የቡድን ውድድር ኢትዮጵያ ወርቅ፣ ኤርትራ ብርና ደቡብ አፍሪካ የነሀስ ሜዳሊያ አጥልቀዋል፡፡

ኤርትራ የመጀመሪያ ወርቅ ባገኘችበት የ46 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ከ23 ዓመት እድሜ በታች ወንዶች የቡድን የብሰክሌት ሩጫ ደግሞ ሩዋንዳና ኢትዮጵያ እንደቅደም ተከተላቸው የብርና የነሐስ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

በ14ኛው የአፍሪካ የብስክሌት ወድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው እሁድ በተካሄደው የድብልቅ ቅብብሎሽ ወድድር ኤርትራ፣ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወድድራቸውን አጠናቀው እንደቅደም ተከተላቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ አሸናፊ ናቸው፡፡

Äthiopien 14. Afrikanische Radsportmeisterschaft in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

ትናንት በተደረጉ 6 ውድድሮች ደግሞ ኢትዮጵያ 4 ወርቅ በማሸነፍ መሪነቷን አጠናክራለች፡፡ በዚህም መሰረት በ15 ኪሎ ሜትር ታዳጊ በግል የሴቶች እሽቅድምድም ትርሀስ ተ/ሀይማት ከኢትዮጵያ ወርቅ፣ ዳናዊት ጸጋይና ብርክቲ ፍሰሀዬ ከኤርትራ ብርና ነሐስ ወስደዋል፡፡ በ30 ኪሎ ሜትር ታዳጊ ወንዶች በግል ሀጎስ በላይና ብዙዓሁ ተስፉ ከኢትዮጵያ ወርቅና ነሐስ፣ መተከል ምስጉን ከኤርትራ የብር ሜዳሊያ አሸንፈዋል፡፡

በ30 ኪሎ ሜትር ከ23 ዓመት እድሜ በታች ሴቶች በግል በተደረገ ውድድር ደግሞ ሰላም አምሀ ከኢትዮጵያ ወርቅ ስትወስድ ደሴት ኪዳኔ ከኤርትራ ብር፣ ጃኩሊን ኩሽሜ ከሩዋንዳ የነሐስ ባለቤት ሆናለች፡፡

በ30 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ሰላም አምሀ በድጋሜ ከኢትዮጵያ ወርቅ ስታሸንፍ፣ኢየሩስ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ብር፣ደሴት ኪዳኔ ከኤርትራ ነሀስ አሸንፋለች፡፡

በ46  ኪሎ ሜትር ከ23 ዓመት እድሜ በታች ወንዶች በግል ሙሳ ሙራጅ የመጀመሪያ ወርቅ ለሩዋንዳ ሲያጠልቅ፣ ሬድዋን ኢብራሂም ለኢትዮጵያ ብር አስገኝቷል፡ ኢስላም ማንሱሪ ደግሞ ለአልጀሪያ ነሀስ አስመዝግቧል፡፡ በ46  ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ስቲቨን ዲቮድና ራይም ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ ወርቅና ነሐስ ሲያሸንፉ፣ ኤርትራ በሲራክ ተስፉ አማካኝነት ብር አጥልቃለች፡፡

እስከ ትናንት በተደረጉ ውድድሮች ኢትዮጵያ 7 ወርቅ፣ 3 ብር፣ 2 ነሀስ፣ ኤርትራ 2 ወርቅ፣ 7 ብር፣ 2 ነሀስ፣ ሩዋንዳ ደግሞ 1 ወርቅ፣ 1 ብር፣ 3 ነሐስ በመያዝ ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ውድድሩ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ