1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2009

ኢትዮጵያ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጽ/ቤትን ከግብጽ መዲና ካይሮ ለማስመጣት የማግባባት ሥራ ላይ ናት በሚል የተሰራጨው ዜና ሐሰት መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለዶይቸቬለ ዛሬ ተናግረዋል።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ አርሰናል በሰፋ ልዩነት ትናንት አሸንፏል።

https://p.dw.com/p/2TOoE
Champions League 2016/17 5. Spieltag FC Arsenal vs. Paris Saint Germain PSG
ምስል Imago/PanoramiC

ስፖርት ህዳር 21፣ 2009 ዓም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለግማሽ ምዕተ ዓመት መቀመጫውን ግብጽ መዲና ካይሮ ያደረገውን የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ወደ አዲስ አበባ ለማስመጣት እየተንቀሳቀሰ ነው የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ተገለጠ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለዶይቸ ቬለ ዛሬ እንደተናገሩት «ካይሮ ላይ ይደረግ የነበረው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ እንጂ» ጽ/ቤቱ ወደ አዲስ አበባ አልመጣም፥ «የማስመጣትም ዓላማ የለንም» ብለዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያ አርሰናል ቀንቶት አምሽቷል። ከቦርመስ ጋር ባደረገው ፍልሚያ አርሰናል ትናንት በሰፊ ልዩነት 3 ለ1 ሲያሸንፍ አሌክሲስ ሳንቼዝ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። ቴዎ ዋልኮትም አንድ ግብ በማስቆጠሩ አርሰናል በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ለመሆን ችሏል። የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር ቡድናቸው ላይ ፍጹም ቅጣት ምት በመሰጠቱ የመሀል ዳኛውን ወቅሰዋል።

Fußball UEFA Europa League Feyenoord Rotterdam - Manchester United
ከሜዳ የተሰናበቱት አሠልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆምስል Getty Images/D. Mouhtaropoulos

ቅዳሜ ዕለት ቶትንሀም ሆትስፐርን 2 ለ1 የረታው ቸልሲ ፕሬሚየር ሊጉን በ31 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ 30 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ልዩነት 2ኛ እና 3ኛ ናቸው። ሊቨርፑል ሰንደርላንድን 2 ለ0 ሲረታ፤ ትናንት ነጥብ የጣለው ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶትንሀም ሆትስፐር በ4 ነጥብ ተበልጦ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በርንሌይን 2 ለ1 ረትቷል።

ለእንግሊዝ የሊግ ዋንጫ  አምስተኛ ዙር የእግር ኳስ ግጥሚያ  ነገ ሁል ሲቲ ከኒውካስል ዩናይትድ እንዲሁም፤ ሊቨርፑል ከሊድስ ዩናይስትድ ጋር ይገጥማሉ። ከነገ በስትያ  ረቡዕ አርሰናል ሳውዝ ሐምፕተንን እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ዌስት ሀም ዩናይትድን ይፋለማሉ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ1 በማሸነፍ ከመሪው ላይፕትሲክ ጋር ያለውን ነጥብ በ3 አጥብቧል። ላይፕቲስክ 30 ነጥብ አለው። በሚሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ግብር ባለመክፈል እስር ቤት የቆዩት የባየር ሙይንሽን የቀድሞ ኃላፊ ዑሊ ሆኔስ ዳግም የቡድኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። 

Jahreshauptversammlung FC Bayern München Uli Hoeness
የባየር ሙይንሽን ፕሬዚዳንት ዑሊ ሆኔስምስል Getty Images/Bongarts/M. Mueller

"የግብር ዕዳዬን ከነወለዱ እና የወለድ ወለድ እንዲሁም የቤተክርስቲያን ግብር ዕዳ የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍያልሁ። በእስር ቤት ያሳየሁት ጠባይ አንድ እስረኛ ማሳየት ከሚጠበቅበት በላይ ነው። ያም በመሆኑ የላንድስቤርግ እስር ቤት ኃላፊዋ በመወሰናቸው ገሚሱ ቅጣቴ ተነስቶልኛል። ገሚሱ ቅጣት መስፈርቱ እጅግ ከፍትኛ ነበር። እና ደግሞ የዚህን ገሚስ ቅጣት ዕድል ለማግኘት መስፈርቱን መቶ በመቶ ማሙዋላት ያሻል። ያ ተሳክቶለኛል።»

የባየር ሙይንሽን የምንጊዜም ተቀናቃኝ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት በአይንትራኅት ፍራንክፉርት 2 ለ1 ተረትቷል። መሪው ላይፕትሲክ ፍራይቡርግን ዐርብ ዕለት 4 ለ1 በማንኮታኮት ነበር ነጥቡን ወደ 30 ከፍ ያደረገው።  የባየር ሙይንሽን ዳግም ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዑሊ ሆኔስ ቡድናቸው ለቦሩስያ ዶርትሙንድ እንደማይተኛ ተናግረዋል። ለዚያ ደግሞ በጀርመን እግር ኳስ ስመ-ገናናው ካርል ኃይንትስ ሮመኒገ አብሯቸው መሥራቱ እንደሚረዳቸው ገልጠዋል።

«ከካርል ኃይንዝ ሮመኒገ ጋር አብሬ ስለምሠራ ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም እኛ ሁለታችን ከእዚህ ድንድቅ የአመራር አና የበላይ ጠባቂ ቦርድ፣ እንዲሁም አስተዳደር እና የአስተዳደር ቦርድ ጋር በጋራ ስንቆም ያኔ ሌሎች እኛን ለማሸነፍ አታብቂኝ ውስጥ ይገባሉ። እዚህ ላይ አንድ ነገር ላክልላችሁ እሻለሁ፦ላይፕትሲክ ፬ ለ ፩ አሸንፚል። ከሁለተኛ ተቀናቃኛችን ዶርትርሙንድ ጎን ነው የተሰለፍነው። እነሱን አሁን በስተመጨረሻ መፋለም እንችላለን።»

Formel 1 | Grand Prix Abu Dhabi | Weltmeister Nico Rosberg
የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊው ኒኮ ርዝበርግ ከዋነኛ ተፎካካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ጋርምስል Getty Images/C. Mason

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ከሪያል ሶሴዳድ ጋር አንድ እኩል በውጣት ከመሪው ሪያል ማድሪድ በ6 ነጥብ ርቋል። ሪያል ማድሪድ ስፖርቲንግን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 33 አድርሷል።  ሴቪላ በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዛሬ ማታ ላፓልማ ከአትሌቲኮ ቢልባዎ ይጫወታሉ።

የመኪና ሽቅድምድም

አቡዳቢ ውስጥ በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የፍጻሜ ፍልሚያ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ የልጅነት ሕልሙ ሰምሮለታል። ዋነኛ ተቀናቃኙ ሌዊስ ሐሚልተንን በ5 ነጥብ ቀድሞ በዘንድሮ ውድድሮች አጠቃላይ 385 ነጥብ በመሰብሰብ አሸናፊ መሆን ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን በትናንትናው ዕለት የቡድኑ የመርሴዲስ አባል ኒኮን ነጥብ ለማስጣል ያደረገው ሙከራ በአጠቃላይ ከሽፎበታል። በአቡዳቢው ውድድር የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን አንደኛ ቢወጣም በጠቅላላ ድምር ግን ድሉ ለኒኮ ሮዝበርግ ኾኗል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ