1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 25 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ ኅዳር 25 2010

በወልድያ ከተማ በደጋፊዎች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት፤ ስለእንግሊዝ ፕሬሚር ሊግ እና ጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎችን የምንለው ይኖረናል። የሴካፋ ውድድር ትናንት ተጀምሯል። ሩስያ ከፒዮንግያንጉ የክረምት ኦሎምፒክ ውድድር ሙሉ ለሙሉ ልትታገድ ትችላለች። ነገ ውሳኔ ይሰጣል።

https://p.dw.com/p/2okUZ
Russland Fußballweltmeisterschaft Moskau 2018 - Fussball
ምስል Reuters/M. Shemetov

ስፖርት፤ ኅዳር 25 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

በወልድያ ከተማ እና መቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል ወልድያ ከተማ ውስጥ ትናንት በተፈጠረ ግጭት በሰዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጧል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ሊደርግ የነበረው ጨዋታም ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሳምንት ወሳኝ ጨዋታ አከናውኖ አራተኛ ደረጃን ተቆናጦ የነበረው አርሰናል በድጋሚ ደረጃውን አስረክቧል። የአርሰናልን ደረጃ የተረከውበው በግብ የተንበሸበሸው ሊቨርፑል ነው።  በጀርመን  ቡንደስሊጋ  የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊ ወንድም ኬቪን ቦአቴንግ ፍራንክፉርትን የማታ ማታ ከጉድ አውጥቶታል። የትውልድ ከተማው ቡድን ደጋፊዎችን አንገት ግን አስደፍቷል።  በሩስያ ስፖርተኞች አበረታች ንጥረ ነገር ሲጠቀሙ መንግሥት እጁ ነበረበት ስለሚለው ክስ  ነገ ውሳኔ ይሰጣል።  ሩስያ በደቡብ ኮሪያ የክረምት ኦሎምፒክ ሙሉ ለሙሉ ልትታገድም  ትችላለች። 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር ትናንት ወልድያ ከተማ ውስጥ ሊከናወን የነበረው ግጥሚያ ሳይካሄድ ቀርቷል። ውድድሩ ሳይከናወን የቀረው በወልድያ ከተማ እና በመቀሌ ከተማ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት ነው። በግጭቱ የተነሳ በሰዎች እና በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተለያዩ ዘገባዎች በተለይም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ወጥተዋል ። 

የእግር ኳስ ደጋፊዎች ግጭት በየትኛውም ዓለም የሚከሰት ኩነት ነው። ኾኖም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ግን ከሌሎቹ ለየት ያለ ይመስላል። ከጊዜ ወደ ጊዜም የእግር ኳስ ደጋፊዎች በብሔር ተኮር ግጭቶች ሲሳተፉ መመልከት ተደጋግሟል። ችግሩ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ከመሻገሩ በፊትም የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን የሚያደራጁ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው እንላለን። 

ሴካፋ

የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር ምክር ቤት (Cecafa) የእግር ኳስ ግጥሚያን ዘንድሮ ያስተናገደችው ኬንያ ትናንት በመክፈቻው ሩዋንዳን 2 ለ0 አሸንፋለች።  ሊቢያ ከታንዛኒያ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ዛሬ ቡሩንዲ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ኡጋንዳ ከዚምባብዌ ሊጫወቱ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። ሆኖም ዚምባብዌ ከውድሩ በመውጣቷ የዛሬ ግጥሚያ በኡጋንዳ እና ቡሩንዲ መካከል መሆኑ ተገልጧል። ከተጀመረ 91 ዓመታት ያስቆጠረው የሴካፋ ውድድር  በአፍሪቃ አንጋፋ ውድድርነቱ ይጠቀሳል። 

CECAFA Fussball-Cup
ምስል EBRAHIM HAMID/AFP/Getty Images

ሴካፋ የተዋቀረው በ11 የአፍሪቃ ሃገራት ቡድኖች  አባልነት ነው። ቡድኖቹም፦ የውድድሩን እርሾ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1926 ጎሳጌ ግጥሚያ ብለው የጠነሰሱት ኬንያና ኡጋንዳን ጨምሮ፤ ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ፤ ጅቡቲ፤ ሶማሊያ፤ ሩዋንዳ፤ ቡሩንዲ፤ ሱዳን እና ታንዛኒያ ናቸው። ዛንዚባር በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) የማኅበርነት ዕውቅና ለማግኘት ትግል ላይ ናት። ሊቢያ እና ዚምባብዌ የዘንድሮ የሴካፋ ውድድር ተጋባዥ ቡድኖች ሲሆኑ፤ ዚምባብዌ ከውድድሩ ወጥታለች። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ዌስትሀምን 2 ለ1 ድል ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው። ከተከታዩ ማንቸስተር ዩናይትድ በስምንት ነጥብ በልጦ በያዘው 43 ነጥቡ ደረጃውን እየመራ ይገኛል።   ቅዳሜ እለት አርሰናልን 3 ለ1 ድል ያደረገው የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ አንደር ሔሬራ መሪው ማንቸስተር ሲቲ የያዘውን ደረጃ ለመንጠቅ በቀጣይ ጨዋታዎች እንደሚፋለሙ ተናግሯል። ማንቸስተር ዩናይትድ ለጄሴ ሊንጋርድ እና አንቶኒዮ ቫሌንሲያ ግቦች እንዲህም ግብ ጠባቂው ዴቪድ ደ ጊያ ብቃት ምስጋና ይግባቸውና በተከታታይ አራት ውድድሮች ማሸነፍ ችሏል። 

የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በበኩላቸው ምንም እንኳን ቡድናቸው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ  በ15 ነጥብ ርቀት ላይ ቢገኝም፤ ዘንድሮ ዋንጫ የማግኘት ዕድላቸው አለመምከኑን ገልጠዋል።  በአንጻሩ ቅዳሜ እለት ከዋትፎርድ ጋር አንድ እኩል የተለያየው የቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ግን ቡድናቸው ዋንጫ የማግኘት ህልሙ መምከኑን አስታውቀዋል። 

በነገራችን ላይ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ሆትስፐር ከአርሰናል የሚበለጠው በ3 ነጥብ ብቻ ነው። አርሰናል በሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ተበልጦ 29 ነጥቦች አሉት።

ባለፈው ቅዳሜ ቢርግቶንን 5 ለ1 ያንኮታኮተው ሊቨርፑል ተከላካይ ጆዌል ማቲፕ ጡንቻው ላይ ከደረሰበት አደጋ በቅርቡ ሽሎት እንደሚመለስ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ተናግረዋል። ከስፓርታክ ሞስኮው ጋር የፊታችን ረቡዕ ለሚኖረው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ጆዌል ተሽሎት ሊሰለፍ እንደሚችልም አሰልጣኙ አክለው ተናግረዋል። ጆዌል በሌለበት የቅዳሜው ግጥሚያ የሊቨርፑሎቹ ተከላካዮች ኤምሬ ቻን እና አማካዩ ጊኒ ዊጅናልዱም ብቃታቸውን አሳይተዋል። 

Fußball Premier League Arsenal - Crystal Palace
ምስል picture-alliance/empics/A. Davy

የቸልሲው አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ደግሞ የቡድናቸው ወሳኝ ተጨዋች የሆነው ኤደን ሐዛርድ ብቃቱ ጫፍ ላይ አልደረሰም ብለዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 ቸልሲን ከተቀላቀለበት ጊዜው አንስቶ ብቃቱን ያስመሰከረው  ሐዛርድ  በቅዳሜው የኒውካስል ግጥሚያ ቡድኑ 3 ለ1 ሲያሸንፍ ሁለቱን ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ዘንድሮ እስካሁን በተደረጉ 18 ጨዋታዎችም ኤደን ሐዛርድ 8 ግቦች ሲኖሩት፤  6 ከመረፍ ያረፉ ኳሶችን ለቡድኑ አባላት አመቻችቶ መስጠት ችሏል።  

ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን  ቅዳሜ እለት ሐኖቨርን 3 ለ1 በመርታት ነጥቡን 32 አድርሷል። ቬርደር ብሬመን ሽቱትጋርትን 1 ለ0 ቢያሸንፍም በ11 ነጥቡ ከደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ግርጌ ከሚገኘው ኮሎኝ በ8 ነጥብ ከፍ ብሎ ይቃትታል። 18ኛ ደረጃ ላይ ተዘርግቶ የሚገኘው ኮሎኝ እስካሁን በተደረጉ 14 ግጥሚያዎች ያገኘው 3 ነጥብ ብቻ ነው። አንዷም ነጥብ ብትሆን ኮሎኝ ትናንት ከሻልከ ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል በመውጣት ያገኛት ናት። አውስቡርግ ማይንትስን ትናንት 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፤  አይንትራኅት ፍራንክፉርት ቤርሊንን 2 ለ1 ድል አድርጓል። በ22 ነጥቡ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የአይንትራኅት ፍራንክፉርት አሠልጣኝ ኒኮኮቫች ምንም እንኳን ቡድናቸው የማታ ማታ ቢያሸንፍም አቻ ሆኖ የቆየውን ሔርታ ቤርሊንን አወድሰዋል። 

«ሔርታዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ተጫውተዋል። እነሱ እንዲያ ጥሩ በተጫወቱበት ልክ የእኛ አቋም መጥፎ ነበር። ፈጽሞ ከጨዋታው ቅኝት ውጪ ነበርን ማለት ይቻላል። በሁሉም አቅጣጫ ተበልጠናል። በሚገባ ማጥቃት አልቻልንም። አንድ እኩል አቻ ከወጣን በኋላ በእግርጥ በጣም ጥሩ ነበርን።»

አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ22 ነጥቡ ከአውስቡርግ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሚበለጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሆፍንሀይም በበኩሉ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው። ሌላው ትናንት ድል የቀናው ቮልስፍስቡርግ ነው።  አሰልጣኙ ዳንኤል ዲቫዲ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ከቡድናቸው ገና ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

Deutschland VfL Wolfsburg v Borussia Moenchengladbach - Bundesliga | Daniel Didavi
ምስል Getty Images/Bongarts/S. Franklin

«እንዳልኩት ያን ሁሌም የምናገረው ነው። ለወራጅነት ከታጩት መካከል መሆን አይገባንም። ብዙ ድንቅ ብቃቶች አሉን። ያን ብቃታችን ማስመስከር ብቻ ነው የቀረን። አሁን ያን ማድረግ ችለናል። እንግዲህ  የቀረው ያን ዘላቂ ማድረግ ብቻ ነው። ያን ደግሞ ከሳምንታት በኋላ መስመር ስናስይ ያኔ ሌላ ቡድን ለመሆን አፍታም አይፈጅብን።»
ቮልፍስቡርግ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን ትናንት 3 ለ0 ድል አድርጎ ነጥቡን 17 ማድረስ ችሏል፤ ደረጃውን ደግሞ 11። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይፕትሲሽ ከሻልከ በአንድ ነጥብ በልጦ ሁለተኛ ነው። 

ሩስያና ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር

ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) የቦርድ አባላት ሩስያን በተመለከተ ብይን ለመስጠት ነገ ዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኝበት ላውዛኔ ስዊዘርላንድ ውስጥ ይሰበሰባል። ኮሚቴው በነገው እለት ውሳኔ የሚሰጠው የሩስያ መንግሥት በሩስያውያን ዕውቅ ስፖርተኞች የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር በስፋት ሲወሰድ መንግሥት እጁ ከጀርባ አለበት በሚለው ክስ ላይ ነው። ይህን ክስ የተከታተለው እና በ2016 ዝርዝር ሰነድ ያቀረበው፦ ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ (WADA) ነው። ሠነዱ በካናዳዊው ጠበቃ ሪቻርድ ማክላረን ይፋ ሲደረግ መላ ዓለም ጉድ ብሎ ነበር። 

ሩስያ በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ስፖርት ውድድሮች ላይ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና ጋር በመፎካከር ቀዳሚ መስመር ላይ ስትሰለፍ ቆይታለች። በዚህ የስፖርት ቅሌት የሩስያ መንግሥት እጁ እንዳለበት ከተረጋገጠ ሩስያ ከሚቀጥለው የፒዮንግያንጉ የክረምት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሙሉ ለሙሉ ልትታገድ ትችላለች። ደቡብ ኮሪያ ፒዮንግያንግ ውስጥ የሚከናወነው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ግጥሚያ ከሦስት ወራት ግድም በኋላ ከየካቲት 2 እስከ የካቲት 18 የሚዘልቅ ነው። ለሁሉም የነገውን ውሳኔ መጠበቅ ነው። 

ማተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ