1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ግንቦት 20 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 20 2010

በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ወደ ዩክሬን መዲና ኪዬቭ ለመትመም ሲያልሙ በፌሽታ እንደሚመለሱ ሙሉ ተስፋ ሠንቀው ነበር። እንዲህ በእንባ እንደሚራጩ ግን ማንም አልገመተም።

https://p.dw.com/p/2yTSK
Champions League Final - Real Madrid v Liverpool - Niederlage für Liverpool
ምስል Imago/Bildbyran/V. Wivestad Grott

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከ13 ዓመት በኋላ ቡድናቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ ለፍጻሜ መድረሱን በራሱ ልዩ ድል አድርገው ወስደውታል። ለዚህ ታላቅ ቀን እና ክብር ያበቃቸው ደግሞ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ናቸው። እኚህ ጀርመናዊ አሰልጣኝ ከቀድሞ ቡድናቸው ያስመጡት የሀገራቸው ልጅ ግን ጉድ ሠርቷቸዋል። የሎሪስ ካሪዩስ የቀን ቅዥት! የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ እና የሊቨርፑል መሪር ለቅሶ የዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ዐቢይ ማጠንጠኛ ነው። አትሌቲክስ፣ እና የመኪና ሽቅድምድምንም ተመልክተናል።

ላለፉት ሦስት ቀናት ከዩክሬን መዲና ኪዬቭ፣ እስከ ለንደን ጎዳኖች፤ ከጀርመኗ ማይንትስ ከተማ እስከ ፈረንሳዩዋ ፓሪስ፤ መላው አውሮጳ ብሎም ዓለም ስለ አንድ ሰው ያወራል። ይኽ ሰው የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ጀርመናዊው ሎሪስ ካሪየስ ነው። የቅዳሜው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ቅዠት ጀርመናዊውን ለረዥም ጊዜያት እንደሚያድነው አያጠራጥርም። እንቅልፍ አልባ ምሽት ያሳለፈባትን ያቺን ቀን ላለማየት ምነው ከማይንትስ ቡድኔ የወጣሁ ቀን እግሬን በሰበረውም ሳይል አይቀርም። ግን ኾነ። «የፈሰሰ ውኃ አይታፈስ» ኾነና መቼም ከማይመልሳት ከዚያች ምሽት ጋር ተፋጠጠ።  እንዳፈጠጠም ነጋለት፤ ወይንም ነጋበት።

«በእውነት እስካሁን ድረስ እንቅልፍ ባይኔ አልዞረም» አለ ሎሪስ ካሪየስ ቅዳሜ ቡድኑ እንደማይሆን ኾኖ በተሸነፈ ማግስት እሁድ ትዊተር ገጹ ላይ። ቀጠለ፦ «የኾነው ሁሉ አሁንም አሁንም በጭንቅላቴ ይመላለሳል። ለቡድኔ፣ ለእናንተ ለደጋፊዎች፣ እንዲሁም ለሁላችሁም የቡድኑ አባላት መጨረሻ የሌለው ሐዘን ተሰምቶኛል። በእነዚያ ሁለት ስህተቶች ሁሉን ነገር ምስቅልቅሉን ማውጣቴን እና እናንተንም እጅግ ማሳዘኔ ይታወቀኛል» ሲል ለሠራው ጥፋት እጅግ መጸጸቱን ገልጧል።

ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በሪያል ማድሪድ 3 ለ1 ድባቅ ሲመታ ሁለቱን ግቦች ለሪያል ማድሪድ በስጦታ ያበረከተው ይኸው የ24 ዓመቱ ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ ነው። 51ኛው ደቂቃ ላይ ጉድ የኾነው አጠገቡ ካሪም ቤንዜማ እያለ ኳስ ለባላጋራው ለመወርወር መሞከሩ ነበር። ከአጠገቡ እንደተኩላ ያደባው ካሪም ቤንዜማ ቀልጠፍ ብሎ እግሩን በመዘርጋት በቀጥታ ቀዳሚዋን ግብ አስቆጠረ። ግራ የተጋባው ግብ ጠባቂ ሎሪስ ካሪዩስ ግቡ ትክክል አይደለም በሚል ምልክት ሜዳው ላይ ጥቂት ተመላለሰ። ግቧ ግን ጸደቀች። ተቀይሮ የገባው ጋሬት ቤል በ64ኛው ደቂቃ አየር ላይ ተንሳፎ በአክሮባት ያስቆጠራት ግብ ግን ለሎሪስ ካሪዩስ ብቻ ሳይኾን ለማንኛውም ድንቅ ግብ ጠባቂ ሳይቀር ምትሀት አይነት ነበረች።  በ83ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው የዌልስ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ከርቀት እንደነገሩ የላካት ኳስ ከሎሪስ እጅ አፈትልካ መረብ መንካቷ ግብ ጠባቂውን ምን ነካው አስብሏል።

የፍጻሜ ጨዋታውን ለጀርመን ተመልካቾች በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው (ZDF) የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ለግብ ጠባቂው ስህተት ሰበብ ሊሆን ይችላል ያለውን ምስል አሳይቷል። ጣቢያው ሎሪስ ካሪዮስ የመጀመሪያዋ ግብ ከመቆጠሯ ሁለት ደቂቃ በፊት በሪያል ማድሪዱ አምበል ሠርጂዮ ራሞስ ክርን ጭንቅላቱ ተመትቶ መሬት ሲወድቅ ደጋግሞ አሳይቷል። ምናልባትም ይህ ምት ለስህተቶቹ ሰበብ ሳይኾን አይቀርም ተብሏል።

የሪያል ማድሪድ እና የስፔን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች አምበል የኾነው የመሀል ተከላካዩ ሠርጂዮ ራሞስ በቅዳሜው ጨዋታ ተንኮለኛ ኾኖ አምሽቷል ሲሉ የኮነኑት ጥቂቶች አይደሉም። ሊቨርፑሎች እጅግ ተስፋ ጥለውበት የነበረው ግብጻዊ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ 31ኛው ደቂቃ ላይ ትከሻው ታጥፎ በጉዳት ከሜዳ እንዲወጣ ያደረገው ይኸው ስፔናዊ የቀኝ ተመላላሽ ነው ሲሉ ርግማን አውርደውበታል። ሠርጂዮ ራሞስ ሆን ብሎ ይሁን ሳያስበው ለሞሐመድ ሳላህ መጎዳት ግን ሰበብ ኾኗል።  እንደውም አንዳንድ የሊቨርፑል ደጋፊዎች  ሠርጂዮ ራሞስ ጉዳት የፈጸመው ኾን ብሎ ነው ስለዚህ ሊቀጣ ይገባል ሲሉ ፊርማ ማሰባሰብ ይዘዋል። ሠርጂዮ ራሞስ ሞ ሳላህን «ኾን ብሎ በመጉዳቱ» ሊቀጣ ይገባል በሚል የተሰባሰበው ፊርማ ከሩብ ሚሊዮን በልጧል። 

በእርግጥም ሠርጂዮ ራሞስ ግብጻዊው አጥቂ  እያነባ ከሜዳ ሲወጣ ከመጸጸት ይልቅ በቅርብ ርቀት የመስመር ዳኛ አጠገብ ቆሞ ሲስቅ ታይቷል።  ሞ ሳላህን አቅፎ ያጽናናው ለይስሙላ ነው፤ የሊቨርፑል ወሳን ሰው የነበረውን ተጨዋች ኾን ብሎ በተንኮል ጎድቶ ነው ያስወጣው ብለዋል። በተለይ ግብጻውያን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1990 ወዲህ ለዓለምዋንጫ ያለፈው ቡድናቸው ወሳኝ ተጨዋች በመጎዳቱ ሠርጂዮ ራሞስ ላይ የእርግማን መዓት አውርደዋል።  የዓለም ዋንጫ ሩስያ ውስጥ ሊጀመር የቀሩት 17 ቀናት ብቻ ነው። ሞ ከትከሻው  ጉዳት  አገግሞ ለዓለም ዋንጫ ለመሰለፍ ሳምንታት ይወስድበታል ተብሏል። 

Fußball Real Madrid v Liverpool - UEFA Champions League - Finale Foul Ramos an Salah
ምስል picture-alliance/empics/D. Klein

በቅዳሜው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ግጥሚያ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ለግማሽ ሰአት ያህል ድንቅ ጨዋታ እያሳዩ ሜዳውን ተቆጣጥረው የነበሩት ሊቨርፑሎች ነበሩ። ግብጻዊው አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በጉዳት ሲወጣ ግን ጨዋታቸው በአጠቃላይ ውሉ የጠፋበት ኾነ። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቡድናቸው ለረዥም ጊዜ ሲለማመድ የቆየበትን አሰላለፍ እንደገና በፍጥነት ማዋቀር ነበረባቸው።  የመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎችን ግን ቡድናቸው ሊቨርፑል በመከራ ነበር የጨረሰው ማለት ይቻላል።

ከረፍት መልስ ሊቨርፑሎች ጨዋታውን ዳግም ተቆጣጥረውም ነበር። በግብ ጠባቂው ስህተት የመጀመሪያው ግብ ከተቆጠረባቸው ከአራት ደቂቃ በላይም አልቆዩ በሳዲዮ ማኔ ድንቅ ግብ አቻ ለመኾን። ሁለት ለአንድ እየተመሩም ቡድኑ እየታገለ ነበር። ሦስተኛዋ ግብ ግን የሊቨርፑልን እኩል የመውጣት እና ለፍጹም ቅጣት ምት የማቅናት ሕልም ጨርሶ አከሰመችው።  ግብ ጠባቂው ሎሪስ ካሪዩስ ዳግም ጉድ ሠራቸው።

እንቅልፍ ባይኑ ላልዞረው ሎሪስ ካሪዩስ በጨዋታ መሀል ስህተት መፈጸም ያለ መኾኑን በመግለጥ በርካቶች አጽናንተውታል። በዛው መጠን የግድያ ዛቻም የሰነዘሩበት አልጠፉም። በተለያዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሎሪስ ካሪዩስ ላይ የተሰነዘሩ ዛቻዎችን የሊቨርፑል ፖሊስ በቸልታ እንደማያልፋቸው ዐስታውቋል። ንዴት እና ቁጣ የወለዳቸው አንዳንዶቹ ዛቻዎች እንዲሁ በቸልታ የሚታለፉ አይነት አይደሉም። በካንሰር በሽታ እንዲያዝ ከመመኘት ቤተሰቦቹ በአጠቃላይ በሞቱ እስከማለት የደረሱም ነበሩ። «ፍቅረኛህን እገድልልሃለሁ» የሚልም አስተያየት ተሰንዝሯል። ፖሊስ ዛቻ ፈጻሚዎች ላይ በአጠቃላይ ጥልቅ ምርመራ እንደሚያከናውን ገልጧል።

የሎሪስ ካሪዩስ እጣ ልብ ይነካል። የቡድኑ አባላት ሳይቀሩ ፊት ነስተውታል። የሊቨርፑሉ አምበል ጆርዳን አንደርሰን ግን ስህተቱ የግብ ጠባቂው ብቻ ሳይኾን የሁላችንም ነው ብሏል። «የመጀመሪያዋ የካሪም ቤንዜማ ግብ ምን እንደኾነ በእውነቱ ላውቅም። እንዲያ ያለ ግብ ስለመፈቀዱም ዐላውቅም ነበር» ብሏል። አከል አድርጎም፦ «ከዚያ ደግሞ በአየር ላይ ቅልበሳ የተመታችውን ኳስ ምንም ሊያደርጋት አይችልም። ሦስተኛዋ ኳስ ከበድ ያለ እንቅስቃሴ ነበራት» ብሏል።ኃላፊነቱንም ቡድኑ በአጠቃላይ እንደሚወስድ ተናግሯል።

Champions League Final - Real Madrid v Liverpool - Real Madrid gewinnt Finale
ምስል Imago/Bildbyran/V. Wivewstad Grott

የንዴት ቁጣውን ያህል ማጽናናቱ ቢኖርም፤ በእግር ኳሱ ዓለም የሎሪስ ካሪዩስ የወደፊት ተስፋው ግን ከእንግዲህ ብሩኅ አይመስልም።  ከሊቨርፑል ጋር የገቡት ኮንትራታቸው ገና ከአራት ዓመት በኋላ የሚጠናቀቀው ጀርመናዊ አሠልጣኝ የሀገራቸው ልጅ ግብ ጠባቂን ዳግም ዕድል ይሰጡት ይኾን? የቡድኑ የቀድሞ ዋና ግብ ጠባቂ ሚኞሌትን መስዋዕት አድርገው ዕድል የሰጡት ግብ ጠባቂ ጉድ አድርጓቸዋልና፤ አይመስልም።

አትሌቲክስ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገለቴ ቡርቃ በካናዳ ኦታዋ ማራቶን ድል አድርጋለች። 33 ሺህ ታዳሚዎች በተሳተፉበት የማራቶን ሩጫ ፉክክር ገለቴ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 2:22:17 ሮጣ በመግባት ነው። በተመሳሳይ የወንዶች ፉክክክር አንደኛ የወጣው ኢትዮጵያዊው አትሌት የማነ ጸጋዬ ሲኾን፤ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2:08:52  ነው። በሴቶችም በወንዶችም ፉክክር ኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ድል አስመዝግበዋል። በወንዶች ፉክክር በኬንያዊው ሯጭ በ14 ሰከንድ የተቀደመው አዱኛ ታከለ ሦስተኛ ወጥቷል። 2:09:14 የገባበት ሰአት ነው።  በሴቶች ፉክክር ሕይወት ገብረ ኪዳን 2:26:11 በመሮጥ ሁለተኛ ወጥታለች።

በዩናይትድ ስቴትስ ኦሬጋን ግዛት ዩጂን ከተማ በተከናወነው የ5000 ሜትር የሩጫ ውድድር የ1500 ሜትር የዓለም ክብር ወሰን ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ አሸንፋለች። ገንዘቤ የፈጀበት ሰአት 14:26.89 ነው። አራት ሰከንድ ግድም ዘግየት ብላ ገንዘቤን በመከተል ግደይ ለተሰንበት ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። 

China Beijing 2015 IAAF Weltmeisterschaft Genzebe Dibaba
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suki

በካናዳ ኦታዋ ደግሞ የ10 ሺህ ሜትር ፉክክር አንዳምላክ በርታ ቅዳሜ እለት አንደኛ ሲወጣ የገባበት ሰአት 27:48 ነበር። በሴቶች ፉክክር ልምምዷን ኢትዮጵያ ውስጥ የምታከናውነው ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ የዩናይትድ ዓረብ ኤሚሬት ሯጭ አሊያ መሐመድ 31:36 በመሮጥ አሸንፋለች። 

ፎርሙላ አንድ

በሞናኮ የትናንቱ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ዳንኤል ሪካርዶ አሸንፏል። የፌራሪው ሠባስቲያን ፌትል 2ኛ የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሀሚልተን ሦስተኛ ወጥተዋል። እስካሁን በተደረጉ ስድስት ዙር የፎርሙላ አንድ ፉክክር የሦስቱም አሽከርካሪዎች ለሁለት ጊዜያት አሸናፊ መኾን ችለዋል። በአጠቃላይ ነጥብ ድምር ግን 110 ነጥብ የሰበሰበው የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሀሚልተን እየመራ ነው። ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል 96 ነጥብ ይዞ ይከተላል። የአውስትራሊያው አሽከርካሪ ዳንኤል ሪካርዶ በ72 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ